ሀዋሳ ፤ ታህሳስ 17 2004/ዋኢማ/ – በደቡብ ክልል የቤተሰብ ምጣኔ አገልገሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ::
በክልሉ ከሁለት ዓመታት በፊት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እናቶች ቁጥር አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን እንደነበረ ያስታወሰዉ ቢሮዉ በተያዘው ዓመት ሁለት ሚሊዮን 129 ሺህ መድረሱን አሰታዉቋል::
በውጤቱም በክልሉ በ 2002 ዓ.ም 57 በመቶ የነበረውን አጠቃላይ የቤተሰብ ምጣኔ አገልገሎት ሽፋን ወደ 65 በመቶ ለማሳደግ ማስቻሉን የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ያለው አባተ ገልጸዋል::
በክልሉ የቤተሰብ ምጣኔ አገልገሎት ሽፋን ተጠቃሚዎች ቁጥር ሊጨምር የቻለው ቢሮው በገጠርና በከተሞች የተቀናጀ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ተግባራዊ በማድረጉ መሆኑን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አስረድተዋል::
ቢሮው በቀጣይ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ጨምሮ በመከላከል ላይ ያተኮሩ የጤና ፓኬጆችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ ነድፎ እየሠራ እንደሚገኝ ባለሙያው ገልጸዋል::
ዕቅዱን ለማሳካትም በየደረጃው የሚገኙ የጤና አመራሮች እና በገጠርና በከተሞች የተሠማሩ ሰባት ሺህ 353 የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተዉ እየሠሩ እንደሚገኙ ባለሙያው አመልክተዋል::
በተጨማሪም ሞዴል የጤና አባዎራዎችን በማቀናጀት ሠፊ የጤና ሠራዊት ለመገንባት ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ከባለሙያው ገለጻ ለመረዳት ትችሏል ::