በደቡብ ኦሞ ዞን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በግብርና ኢንቨስትመንት ተሰማርተዋል

አዲስ አበባ፤ ጥር 03 2004 /ዋኢማ/ -በደቡብ ኦሞ ዞን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በግብርና ኢንቨስትመንት መሰማራታቸው ተገለጸ።
በ2004 በጀት ዓመት ከስድስት ሺ በላይ አርብቶ አደሮች የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡና የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖሩ በኦሞ ወንዝ አካባቢ ለማስፈር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር አስታውቋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሎኮ ውብነህ እንደገለጹት፣ በዞኑ 13 ባለሀብቶች ጥጥ፣ ሰሊጥ፣ ፍራፍሬና የፓልም ዘይት ተክል እያለሙ ነው። ይህም ለዞኑ ሕዝብ የሥራ ዕድልና አርብቶ አደሮችም ወደ እርሻ ሥራ እንዲሠማሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

በዞኑ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የተናገሩት አቶ ሞሎኮ እስካሁን በዞኑ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከ30 በላይ ባለሀብቶች የግብርና የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህ ውስጥ 13 ባለሀብቶች ተግባራዊ ሥራ ጀምረዋል።

ሙሉ በሙሉና በከፊል እርሻ የጀመሩት ባለሀብቶችም ከሁለት ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቅሰው፣ ባለሀብቶቹ ለመስኖ የሚሆን ውሃ ለአካባቢው ሕዝብ በማቅረብም አርብቶ አደሮቹን የእርሻ ሥራ በማለማመድ  ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጋቸውን አብራርተዋል። ለአብነትም በየዓመቱ በዕርዳታ እህል ኑሮአቸውን ይገፉ የነበሩት የፀማይ ብሔረሰብ አባላት የሆኑት የቱማ፣ የእንጨቂና ኪሰማ ቀበሌ ነዋሪዎች የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በአንፃሩ 30ሺ እና 40ሺ ሄክታር መሬት ወስደው እስካሁን ድረስ አንድም ሄክታር ያላለሙ ባለሀብቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ከእነዚህ ባለሀብቶች መካከል ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው እንዲሁም መሬት የተቀነሰባቸው እንዳሉም አመልክተዋል።

በተመሳሳይ በደቡብ ኦሞ ዞን ስድስት ሺ የሚሆኑ አርብቶ አደሮች የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡና የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖሩ በኦሞ ወንዝ አካባቢ ለማስፈር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከእንስሳት እርባታ ወደ ግብርና በሚሸጋገሩበት ወቅትም ችግር እንዳያጋጥማቸው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ከወዲሁ እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት ስድስት የስኳር ፋብሪካዎች እንደሚገነቡ የገለጹት አቶ ሞሎኮ በዞኑ 150ሺ ሄክታር መሬት ላይ የስኳር ልማት ይካሄዳል ብለዋል።
ከስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ጋር ተያይዞም ሁለት ሺ 250 የሚሆኑ የሙርሲና የቦዴ አርብቶ አደሮችን በስኳር ልማት ፕሮጀክቱ አካባቢ ለማስፈር አስፈላጊው የመሠረተ ልማት እየተዘረጋ መሆኑን አስረድተዋል።
አርብቶ አደሮቹ በሚሰፍሩበት አካባቢ መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ኬላዎችና የውሃ መሥመሮች በመገንባት ላይ ሲሆኑ፤ አርብቶ አደሮቹ ራሳቸው አርሰው በምግብ ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስም 37 ሚሊዮን ያህል ብር በጀት መያዙን የዘገበው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።