የግብፅ የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

አዲስ አባባ፤ጥር 04 2004 /ዋኢማ/ – የግብፅ የኮሚዩኒኬሽን እና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ዶ/ር ሞሐመድ ሳሌም እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው።

የግብፅ መንግስት የመረጃ አገልግሎት /ኢ ኤስ አይ ኤስ/ እንደዘገበው ዶ/ር ሞሐመድ ሳሌም ኢትዮጵያን የሚጎበኙት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተውጣጡ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ልዑካንን በመምራት ነው።

ከግብፅ የኮሚዩኒኬሽን እና ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር የደረሰውን መግለጫ ጠቅሶ የግብፅ መንግስት የመረጃ አገልግሎት እንደዘገበው ሚኒስትሩ አዲስ አባባ የሚገቡት የፊታችን ረቡእ ጥር 09 2004 ዓ.ም ነው።

የጉብኝቱ አላማ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር የታሰበ ሲሆን በግብፅ እና ኢትዮጵያ የጋራ ትብብር መድረክ አማካይነት በቴሌኮሚዩኒኬሽንና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ያሉትን ትብብሮች የበለጠ ለማጠናከር ሁለቱ አገሮች የስምምነት ፊርማ እንደሚፈራረሙም ይጠበቃል።

ጉብኝቱ ግብፅ ከአፍሪካ ህብረት እና ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር የነበራትን አጋርነት ለማደስ እንደሚረዳትም የግብፅ መንግስት የመረጃ አገልግሎት ዘገባ ያመለክታል።