የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ጉዳዮች ላይ መወያየት አስፈላጊ መሆኑን ተስማሙ

አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ጉዳዮች ላይ መወያየት፣መከራከርና መደራደር አስፈላጊ መሆኑን ከስምምነት መድረሳቸውን የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ ፡፡

የኢህአዴግ ጽሕፈትቤት የህዝብና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ዛሬ በተለይም ለዋልታ በሰጡት መግለጫ  ዛሬ ገዢው ፓርቲ ጨምሮ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት በሀገር  እና ህዝብ ጉዳዮች ላይ መወያየት ፣መክርክርና መደራደር አስፈላጊት ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተግባብተው የወጡበት መድረክ እንደነበር አስታውቀዋል ፡፡

በመንግስት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ የተካሄደው ስብሰባ መጀመሪያ በሀገር ጉዳይ ላይ መወያየት፣ መከራከርና መደራደር አስፈላጊ ነው ወይስ አይደለም በሚል መነጋገራቸውን ነው ያመለከቱት  ፡፡

እንደዚሁም ኢህአዴግ በተነሳሽነት በጠራው ላይ አስፈላጊ ነው ወይስ አስፈላጊ አይደለም በሚሉ ነገሮች ላይ መወያየታቸውን ጠቁመዋል ፡፡

ከዚህ በኋላም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በአራት ነጥቦች ላይ መነጋራቸውን ነው ኃላፊው ያመለከቱት ፡፡

በዚሁም  መሰረት 1ኛ የስብሰባ ስነ ስርዓቱ ምን መሆን አለበት ፤2ኛ የመድረክ መሪነት እንዴት መካሄድ እንዳለባቸው፣ 3ኛ የፕሬስ መግለጫ  አሰጣጥ በተመለከተና 4ኛ በታዛቢዎች ሁኔታ ላይ ሃሳብ ተዘርግቶ ውይይት መደረጉን  ገልጸዋል ፡፡

በመጨረሻም  እስከ ጥር 25 ባለው ጊዜ ውስጥ በአገር አቀፍ የተመዘገቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን በመድረኩ ላይ የተሳተፉት ያላቸውን አቋም እንዴት እንቀጥል በሚል ዙሪያ ላይ ሃሳባቸውን እንዲሰጡ መግባባታቸውን አስታውቀዋል ፡፡

ይህም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡዋቸው ሃሳቦች የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ጽሕፈት ቤት እንዲያስተባብረው መስማማታቸውንም ጠቁመዋል ፡፡

 ኢህዴግን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ  ያላቸውን ሃሳብ ካስገቡ በኋላ በመንግስት ተጠሪ ጽሕፈትቤት ያላቸውን ሃሳብ በጽሑፍ እንዲያስረክቡ መግባባታቸውንም እንዲሁ ፡፡

ይህ ከሆነ በኋላ በሚቀጥለው ስብሰባ መቼ ይሁን የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲዎች በጽሑፍ ካስገቡ በኋላ ኢህአዴግ እንዲጠራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሙሉ በሙሉ ተስማምተው ነው የወጡት ብለዋል ፡፡

ቀጣይ የስብሰባ ስነ- ስርዓታቸው እንዴት ይሁን ፣የፕረስ መግለጫዎቻቸው በሚሰጡት ላይ፣ በሚደረጉ ክርክሮችና ድርድሮች ምን ዓይነት አግባብ ይኑረው ፤መድረኩ እንዴት ብንመራው ይሻላል ፣በዙር ቢሆን ወይስ ከየፓርቲው የተውጣጣ አካል ቢመራው ወይስ ፤በገለልተኛ አካል ቢመራው ይሻላል የሚል የተለያዩ ሃሳቦች የቀረቡበት መሆኑን ያብራሩት አቶ ፍቃዱ፤እንዚህም ወደፊት የሚታዩ መሆናቸውን አመልክተዋል  ፡፡

የዛሬ ስብሰባ መድረክ መደራደር አይደለም ፤ክርክርና አጀንዳዎች ተቀርጸው እዛ ላይ ውይይት ማድረግ አልበረም ያሉት ኃላፊው በውይይቱ አስፈላጊነት እና እንዴት እንቀጥል የሚለውን ነገር ሆኖ ሁሉም የተሳተፉት አወንታዊ የሆነ አስተያየት የሰጡበት ሁኔታ እንደነበረም ገልጸዋል  ፡፡

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ በወሰነው መሰረትና ለሚድያም በግልጽ በተሰጠው መግለጫ መሰረት ኢህአዴግ ሰላማዊ ሆነው ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣  እና ከስቪክ ማህበራትና በዚህች አገር ላይ ያገባናል ከሚሉ አካላት ጋር ለመወያየት ዝግጁ እንደሆነ ማስታወቁን አስታውሰዋል  ፡፡