በዩኒቨርሲቲዎች አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና የተረጋጋ የመማርና መሰተማር እንዲኖር ማስቻሉን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ዛሬ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ፤መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀበት ጊዜ በኋላ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት በመስፈኑ የመጀመሪያውን የትምህርት አጋማሽ በመልካም የመማር ማስተማር መንፈስ ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡
ይህም ቀደም ሲል ባንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት በመማር ማስተማሩ ላይ እንቅፋት ይሆናል የሚል ስጋት እንዲወገድ ማድረጉን ነው ያስረዱት፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ማሕበረሰቡ ሰላማቸው የተናጋባቸው የዓለም ክፍሎችን ተጨባጭ ሁኔታዎች በማስገንዘብ የሰላምን ዋጋ ይበልጥ ማስገንዘብ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
እንደ ዶክተር ሳሙኤል ገለፃ የትምክህት፣ የጠባብነትና የኃይማኖት አክራሪነትን ኋላቀር አስተሳሰቦች በመታገል የከፍተኛ ትምህርቱ ማህበረሰብ እንዲጠየፋቸው በመስራት የሰላምን ዘላቂ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል ፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ማሕበረሰብ ሰላምን የሚያውኩ ኃይሎችን በመለየት፣ የችግሮቹን ምክንያትና ውጤቱ ሐሳብን በማፍለቅ በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት መፍታት የሚቻልባቸውን ልምዶች ምሁራዊ ትንታኔ መስጠት ይጠበቅበታልም ነው ያሉት ፡፡
ይህን ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል የትምህርቱን ማህበረሰብ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ማስቻል እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኢታው አመልክተዋል ፡፡