ጣሊያን በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉትን የፓለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ታደንቃለች- ጠቅላይ ሚንስትር ጁሴፔ ኮንቴ

ጣሊያን በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉትን የፓለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ጣሊያን  እንደምታደንቅ ጠቅላይ ሚንስትር  ጁሴፔ ኮንቴ ገለጹ።

ኢትዮጵያና ጣሊያን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፓለቲካ ዘርፍ ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራና ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ዛሬ በብሄራዊ ቤተመንግስት የራት ግብዣ አድርገዋል ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ጋር በዛሬው እለት ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል ፡፡

በጣሊያን እና ኢትዮጵያ መካከል በኢንቨስትመንት ፣ ንግድ ፣ በመሰረተ ልማት እንዲሁም በስደት ዙሪያ ያለውን ትስስር ለማጠናከር መስማማታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

ጣሊያን የኢትዮጵያ የልማት ትብብር ቀዳሚ አጋር ከሆኑ ሀገራት መካካል አንዷ መሆኗን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትብብሩ የበለጠ መጠናከር እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

በቀጠናው ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ጣሊያን ያላትን ድጋፍ አድንቀው ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ጁሴፔ ኮንቴ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጣሊያን ታሪካዊና ሁለገብ ትስስር እንዳለቸው አውስተው ይህ ትብብርም ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር በቁርጠኝነት ለመስራት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ከመግባባት መደረሳቸውን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያና እየተካሄዱ ያሉትን የፓለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችንና ለውጡን የሚመራውን መንግሥት አድንቀው ጣሊያን የለውጡን እንቅስቃሴ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን አንስተዋል፡፡

ጁሴፔ ኮንቴ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረውን የጦርነት ሁኔታ በአዲስ የሰላምና የወዳጅነት ምዕራፍ መተካቱ በሳል እርምጃ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም የሰላም ሂደቱ ከሁለቱ ሀገራት አልፎ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት አዲስ በር የከፈተ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ጣሊያን ለሰላም ሂደቱ መጎልበትና ዘላቂነት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል ፡፡

ኢትየጵያ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም መልህቅ ናትም ብለዋል ፡፡

ጁሴፔ ኮንቴ በሁለትዮሸና በባለብዙ ወገን መድረኮች ሁለቱ ሀገራት ያላቸው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል ፡፡(ኤፍቢሲ)