የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን 184 አባላቱን አሰናበተ

አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከተቋሙ ተልኮ በተፃረረ መልኩ በተለያዩ  የወንጀል ድርጊት የተሳተፉ እና የስነ-ምግባር ችግር ያለባቸውን 184 የፖሊስ አባላትን ከሰራዊቱ ማሰናበቱን ገለፀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአገር አቀፍ ብሎም በከተማዋ ተግባራዊ የሆነውን ለውጥ ተከትሎ ከዚህ ቀደም በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማስተካከል ለከተማችንን የሚመጥን ፖሊሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ልዩ ልዩ የለውጥና የመልሶ ማደራጀት ወይም የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።

ኮሚሽኑ ከህብረተሰቡ የተሰጡ ጥቆማዎች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የደረሱትን መረጃዎች መነሻ በማድረግ መላው የፖሊስ አባላትን ያሳተፈ ግምገማ ከማእከል እስከ ፖሊስ ጣቢያ ባለው መዋቅር የአጥርቶ ማጥራት ስራ በመስራት ከኮሚሽኑ ተልዕኮ ተፃራሪ በመሆን በልዩ ልዩ ከባድ ወንጀል ላይ የተሳተፉ እንዲሁም ከፖሊሳዊ ስነ-ምግባር ውጭ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 184 የፖሊስ አባላት ከሰራዊቱ ማሰናበቱን ነው ያስታወቀው።

በልዩ ልዩ የወንጀል ድርጊት ውስጥ ገብተው የተገኙ የፖሊስ አባለት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑንም ኮሚሽኑ ገልጿል።

የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና ተቋሙ ህዝብና መንግስት የጣሉበትን ከፍተኛ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ቀጣይነት ያለው የማጥራት ስራዎችን አጠናክሮ  የሚቀጥል መሆኑን በመግለፅ፥ በቅርብ ጊዜ መላውን አባልና አመራር ያሳተፈ ስልጠናዊ ግምገማ ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል።

በመጨረሻም ለኮሚሽኑ ስራ መሳካት ህብረተሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እያደረጉለት ላለው ቀና ትብብር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምስጋናውን አቅርቦ ነዋሪው በአገልገሎት አሰጣጥ ይሁን የስነ-ምግባር ችግር ያለባቸውን የፖሊስ አባለት ሲያጋጥሙት በየአካባቢው በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ፖሊስ መምሪያዎች እና ፖሊስ ኮሚሽን ድረስ በአካል በመቅረብ እንዲሁም በነፃ የስልክ መስመር 991 ወይም 01-11-11-01-11 ጥቆማ መስጠት እንደሚቻል ገልጿል። (ምንጭ፡- አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን)