መከላከያ ሠራዊቱ በምዕራብ አማራ ገንዳኋንና ኮኮሊት አካባቢዎችሕግን ያልተከተለ ጣልቃ ገብነት መፈጸሙን አብን ገለጸ

የመከላከያ ሠራዊቱ ሰሞኑን በምዕራብ አማራ ገንደኋንና ኮኮሊት አካባቢዎች  የፈጸመው  ጣልቃ ገብነት  ሕግን ያልተከተለ መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ( አብን) በዛሬው ዕለት ገለጸ  ።

አብን በዛሬው ዕለት  ለመገናኛ ብዙሃን በሠጠው መገለጫ እንደገለጸው ሰሞኑን በአማራ ክልል ምዕራብ አካባቢ ገንደኋንና ኮኮሊት በተባሉ ሥፍራዎች የመከላከያ ሠራዊት ጣልቃ  በመግባት የፈጸመው   ተግባር  ህግን ያልተከለተ፣  ህዝብን ያስከፋና አመኔታን ያሳጣ ነው ብሏል ።  

በአካባቢዎቹ በተከሰቱት ችግሮች በየደረጃው ያሉ የክልል  የፀጥታ ኃይል  ከአቅማችን በላይ ነው ሳይሉና የመንግሥትን እገዛ  ባልጠየቁበት  ሁኔታ  የመከላከያ ሠራዊት ጣልቃ መግባቱ  ተቀባይነት  እንደሌለው  በመግለጫው ገልጿል።

የመከላከያ ምክትል ኤታማዦር ጉዳዩን አስመልክቶ የሠጡት መግለጫ ህዝብን  ለበለጠ  ቁጣ የሚያነሳሳ ፣ ተንኳሽ  እንደሆነ መግለጫው  አትቷል ።

መንግሥት ህግን ማስከበር  ካልቻለና ካቃተውም የአማራ ሕዝብ ህልውናውን የማስከበር መብቱን ለመጠቀም የሚገደድ መሆኑንም  በመግለጫው ጠቁሟል ።

አብን ባወጣው መግለጫ በተፈጠረው ጉዳይ ላይ  ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ የመከላከያ ሚንስትርና ኤታማዦር ሹሙ  ማብራሪያ እንዲሠጥ፤  ለደረሰው ጉዳት ይቅርታ  እንዲጠየቅና  ለተጎጂዎችም  ካሳ  እንዲከፈል ጠይቋል ።

በመጨረሻም መግለጫው በክልሉ  በተፈጠረው  ችግር ምክንያት  ለተጎዱት  ቤተሰቦች  መጽናናትን ተመኝቷል ።