የሀገር ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ

የሀገር ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችን ማህበረሰባዊ እሴትን በማጎልበት ረገድ የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ፡፡

የሀገር ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ከዚህ ቀደም ግጭቶች ሲከሰቱ ሰላምን ለማምጣት ይጠቀሙበት የነበረውን ማህበረሰባዊ እሴት በማጎልበት ለሀገር ሰላም ጉልህ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ የሰላም ሚንስትፘ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ጥሪ አቀረቡ፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች “ለሀገር ሰላም” በሚል መሪ ቃል ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚንስትሯ ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል ሀገር የተገነባችው በትውልድ ቅብብሎሽ እንደመሆኑ መጠን አባቶች ከትላንት የተረከባችሁትን ትውልድ በማህበረሰባዊ እሴት የማነፅ ልምድ ተጠቅማችሁ ሀገርን ካለችበት አስቸጋሪ ወቅት ልትታደጓት በሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሯ አክለውም የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ወ/ሮ ሙፈርያት አያይዘው በሀገር ሽማግሌዎች ስም የሚነግዱና ሀገር ሰላም እንድትሆን የማይፈልጉ አንዳንድ የሀገር ሽማግሌዎችን ስምና ምግባር የሚያጎድፍ አሉ እነሱን በመታደግ አባቶች ለሰላም እንጂ ለብጥብጥ እንደማይቆሙ በማሳየትና በማስተማር ኃላፊታቸውን እንዲወጡ አደራም ብለዋል፡፡

በሰላም ሚንስቴር የሰላም ግንባታ ሚንስትር ዲኤታ የሆኑት ወይዘሮ አልማዝ መኮነን በበኩላቸው ሚንስትር መስሪያ ቤቱ ከተቋቋመ ገና 3 ወራትን ያስቆጠረ ቢሆንም በሀገሪቱ ሰላምን ለማስፈን እየሰራ እንደሚገኝና የሰላም ባለቤት የሆኑት የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ በታሪክ ተመራማሪ ምሁራን ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን በውይይቱ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በሠጡት አስተያየት ትላንት የነበረውን አገራዊ አንድነት በማማጣት በጎሳና በብሄር መከፋፈል በመተው ለኢትዮጵያ አንድነት መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ዋልታ ያነጋገራቸው የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየታዩ ያሉትን ግጭቶች ለማስቆምና የሀገር ሰላም ወደ ቀድሞው ይመለስ ዘንድ ከመንግስት ጎን በመቆም እንደሚሰሩ  ገለጸዋል፡፡

አባቶቹ ወጣቶች ወደ ግጭት እንዳይገቡና በስነምግባር  የታነፁ ሆነው እንዲያድጉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጨምሮ እናቶች፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ማህበረሰባዊ እሴቶችን በማጎልበት ማስተማርና መምከር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡