ሜጀር ጀነራል ክንፈንና 13 ግለሰቦች ከ544 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ የሙስና ወንጀል ተከሰሱ

ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘውና ሌሎች 13 የሜቴክ የቀድሞ ሠራተኞች በመንግስትና ህዝብ ላይ ከ544 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ የሙስና ወንጀል ተከሰሱ። 

በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው 1ኛ ተከሳሽ ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ገብረሥላሴ፣ 2ኛ ኮሎኔል በርሄ ወልደሚካኤል ገብሩ (ያልተያዘ)፣ 3ኛ ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብርኤል ገብረእግዚአብሄር፣ 4ኛ ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዲ ኤጀታ ናቸው ።

5ኛተከሳሽ ኮ/ል ተከስተ ኃይለማርያም አድሃኖም፣ 6ኛ አቶ ሰለሞን ሀይለሚካኤል አስገዶም (ያልተያዘ)፣ 7ኛ ኮ/ል መሀመድብርሃን ኢብራሂም ሀጎስ (ያልተያዘ)፣ 8ኛ ሻ/ቃ ሰለሞን አብርሃ አለሙ፣ 9ኛ ኮ/ል አለሙ ሽመልስ ብርሃን፣ 10ኛ ኮ/ል አዜብ ታደሰ ሀይሉ፣ 11ኛ ሻ/ል ይኩኖአምላክ ተስፋዬ ሀገዞም፣ 12ኛ ሻ/ል ሰመረ ሀይሌ ሀጎስ፣ 13ኛ ሚስተር ሞህድ ራፍ ኤች (ያልተያዘ) እና 14ኛ አቶ ኡስማን አብዱ ዋሃብረቢ (ያልተያዘ) ናቸው።

አቃቤ ህግ ግለሰቦቹን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከ28 ዓመታት በላይ የተገለገለባቸው አባይ ወንዝ እና አብዮት ከተባሉ ሁለት መርከቦች ግዢ ጋር በተያያዘ ተፈፅሟል ባላቸው የሙስና ወንጀል ነው የከሰሳቸው።

የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ 1ኛ ተከሳሽ የኢፌዴሪ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር እና ከ2ኛ እስከ 5ኛ የተጠቀሱት ተከሳሾች ደግሞ በየስማቸው አንፃር በተጠቀሰው የሥራ ኃላፊነታቸውን ያለአግባብ በመጠቀም ህዝብና መንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብሏል ።

የመንግስት የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት  ከሥልጣናቸው በማለፍ ከኮርፖሬሽኑ ዓላማ ጋር ተያያዥነት በሌለው በባህር ትራንስፖርት ዘርፍ ለመሰማራት መወሰናቸውን ክሱ  ያስረዳል።