በምዕራብ ኦሮሚያ 18 የመንግስትና የግል ባንኮች ላይ ዝርፊያ መፈፀሙን የክልሉ መንግስት አስታወቀ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች በሚገኙ 18 የመንግስት እና የግል ባንኮች ላይ ዝርፊያ መፈፀሙን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ። 

የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፥ ባለፉት አምስት ቀናት ውስጥ ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 18 ባንኮች ዝርፊያ ተፈጽሟል።

ዝርፊያውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ላይ ነው የተፈፀመው ያለው ቢሮው፥ ከዚህ በተጨማሪም በኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ላይም ዝርፊያ መፈፀሙን አስታውቋል።    

ከባንኮች ዝርፊያ በተጨማሪም የተለያዩ የግል እና የመንግስት ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱንም ቢሮው በመግለጫው አክሎ አስታውቋል።

በዚህም ቁጥራቸው 10 የሚደርሱ የመንግስት እና የግል ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸው በመግለጫው ተመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ከላይ በተጠቀሱት ዞኖች የመንግስት መሣሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል ያለው ቢሮው፥ የተለያዩ የስራ ሰነዶችን የማቃጠል እና የማውደም፣ የመንግስት ተሽከርካሪ እና የግል ንብረቶች ዝርፊያ እንዲሁም መንገድ በመዝጋት የህዝቡን የመንቀሳቀስ መብት የመገደብ ተግባር ተፈፅሟል ብሏል።

እንዲህ አይነቱን ህገ-ወጥ ተግባርም ህዝቡ አምርሮ በመቃወም አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ ከመንግስት እና ከፀጥታ አካላት ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ገልጿል።

በዚሁ መሰረት ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች በዚህ ህገ ወጥ ተግባር ላይ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ነው ቢሮው ያስታወቀው።

ይህንን የወንጀል ተግባር በማቀነባበር እና በመፈፀም የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በህግ ቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑንም ገልጿል።

በአሁኑ ወቅትም የህግ የበላይነትን ለማስከበር እና የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ባለው ስራም በምእራብ ኦሮሚያ ያለው የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱንም ጠቅሷል።

አሁን የተገኘው የሰላም ሁኔታ ቀጣይነት እንዲኖረውም የአካባቢው ህዝብ እና መንግስት ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን እየሰሩ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል።

በተመሳሳይ የደቡብ ዞን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጦር የጉጂ ኦሮሞ አባ ገዳዎች ያቀረቡለትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላማዊ ትግል እየተመለሱ መሆኑን ቢሮው በመግለጫው ጠቅሷል።

በዚህም መሠረት ኤሊያስ ጋምቤላ ጎሎ የሚመራው የጉጂ ዞን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጦር ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ወደተዘጋጀለት ማረፊያ እየገባ መሆኑንም አስታውቋል።