ምክር ቤቱ የስደተኞች ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ባካሄደው 19ኛው መደበኛ ስብሰባ የስደተኞች ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅን አፅድቋል ።

ምክር ቤቱ  በዛሬው  መደበኛ ስብሰባው  የህግ ፣ የፍትህና የዴሞክራሲ  ቋሚ ኮሚቴ  ያቀረባቸውን  ሁለት  ረቂቅ አዋጆችን  መርምሮ  አፅድቋል ።

የስደተኞችን ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅን  የፀደቀው  ከጎረቤት አገራት የሚገቡ ስደተኞችን  መቀበል  የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ  ተሰሚነት  ከማሳደጉም በላይ  አገሪቷ  ከገባችበት  ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አኳያ የአገር ጥቅምን  እንደሚያስከብር ታምኖበት ነው  ።

እንዲሁም  ረቂቅ አዋጁ  ከጎረቤት አገራት  ጋር  ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማሳደግ  የበጎ ገፅታ ግንባታውን  ወደ የተሻለ  ደረጃ ለማሸጋገርና በተለያዩ መንገዶች ለኢትዮጵያ የልማት ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ድጋፋቸውን ለማጠናከር እገዛ እንደሚኖረውም በውይይቱ ተገልጿል ።

በምክር ቤቱ አባላት ረቂቅ አዋጁን ምን ያህል በክልሎች ህዝቡ ውይይት አድርጎበታል፣ የአገርን ጥቅም በምን መልኩ ያስከብራልና በአገሪቱ ላይ የሥራ  አጥነትን ቁጥር አይጨምርም በሚል ጥያቄዎችን አንስተዋል ።   

በምክር ቤቱ የህግ ፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን  በበኩላቸው በሠጡት ምላሽ  ረቂቅ አዋጁ  የሥራ አጥነትን ችግር  የሚቀርፍና  የአገሪቱን ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  ሁኔታን  ያገናዘበ  መሆኑን ገልጸዋል ።

በመጨረሻም የስደተኞች ጉዳይ ረቂቅ አዋጅ 1110 /2011 በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ ፣ በሦስት  ተቃውሞ ፣ በአብላጫ ድምጽ  በምክር ቤቱ ፀድቋል ።