የከተራና የጥምቀት በዓል ያለምንም ፀጥታ ችግር እንዲከበሩ ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀ፡፡

የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበሩ ከበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ፣ ከሌሎች የፀጥታ እና የፍትህ አካላት እንዲሁም የፀጥታው ዋና ባለቤት ከሆነው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ጋር እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ በዓላቱ በሰላም ተጀምረው እንዲጠናቀቁ ለወንጀል እና ትራፊክ አደጋ መከላከል ተግባሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ የሰው ኃይል ማሰማራቱን ገልጿል።

በታቦት ማደሪያ ስፍራዎች በተለይም በርካታ የበዓሉ ታዳሚዎች በሚገኙበት ጃን ሜዳ ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያ ተከፍተው አግልጋሎት የሚሰጡ መሆኑ ነው የተገለፀው።

ፀበል በሚረጭበት ወቅትም  በሚፈጠር ግፊያ ምዕመናኑ ጉዳት እንዳይደርስበት፣ ንብረቶቹ እንዳይሰረቁበት እንዲሁም ከስፍራ ወደ ስፍራ ሲንቀሳቀሱ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ተገልጿል።

የእምነቱ ተከታዮች በተለይ ወጣቶች ከዚህ በፊት እንደሚያደርጉት ሁሉ በተደራጀ መንገድ ከፖሊስ እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጎን በመቆም ለበዓሉ በሰላም መከበር እያደረጉት ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ተብሏል።

ህብረተሰቡ በማንኛውም ወቅት ከፀጥታ ስራ ጋር ተያይዥ እና አጠራጣሪ ነገሮች ሲመለከት እና ማንኛውንም  የፖሊስ አገልግሎትን ለማግኘት በስልክ ቁጥር 01-11-26-43-77 ፣ 01-11-26-43-59 ፣ 01-18-27-41-51 ፣ 01-11-11-01-11 አሊያም በ991 ነፃ የስልክ መሥመር በመጠቀም ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል።

ከጥር 10 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በዓሉ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በጃን ሜዳ ዙሪያ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ክልክል መሆኑንና አሽከርካሪዎች ተገንዝበው አማራጭ የማቆሚያ ሥፍራዎችን እንዲጠቀሙ አሳስቧል፡፡