የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችን በዝርዝር ገምግሞ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቀቀ

ለአራት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የነበረው የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችን በዝርዝር ገምግሞ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቀቀ።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባደረገው ዉይይት የለውጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ እና ተግዳሮቶቹን ለመቅረፍ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ሲመክር ቆይቷል።

ኮሚቴው ለውጡ ባስገኛቸው መልካም ውጤቶች፣ ባጋጠሙ ተግዳሮቶች እና ወደፊት ሊያጋጥሙ በሚችሉ ሁኔታዎች ላይ በጥልቀት ከመከረ በኋላም የድርጊት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ 11ኛው የኢሕአዴግ ጉባኤ ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች መሰረት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያስቻሉ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ስራ አስፈፃሚው ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ ተወስቷል።

እሰከ አተገባበር ችግሩም ቢሆን ህዝቡ የመሰለውን በነፃነት የሚገልፅበት የእፎይታ ስሜት መፈጠሩ፣ ታራሚዎችና ፍርደኞች በይቅርታና ምህረት መለቀቃቸው፣ በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተፎካካሪ ሃይሎችም ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸው፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማረም የተወሰዱ እርምጃዎች እና የመገናኛ ብዙሃን በነፃነት የህዝቡን ድምጽ ማሰማት መጀመራቸው ከዴሞክራሲ ምህዳሩ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ድሎች መሆናቸውን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው መመልከቱን መግለጫው አትቷል።

ሌሎች በኢኮኖሚ፣በፖለቲካ እና በማህበራዊ ዘርፎች እንዲሁም በዲፕሎማሲው መስክ የተገኙ ስኬቶችንም ኮሚቴው ገምግሟል፡፡

በሌላ በኩል በድርጅቱ  ውስጥ አሁንም በለውጡ ምንነት፣ በለውጡ ውስጥ ባለ ሚና እና በወደፊት አቅጣጫዎች ላይ የተሟላ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ፈጥሮ በእኩል ሚዛን እየተጓዘ አለመሆኑ፣ የታችኛው መዋቅርም አለመደገፉ እና በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ያሉ የአካሄድ ዝንፈቶችና የእርስ በርስ መጠራጠር በግልፅ ተነስተው ትግል ተደርጎባቸዋል።

እነዚህ ችግሮች በቀጣይ እንዲስተካከሉም መግባባት ላይ መደረሱን መግለጫው አትቷል።

እንደ ሀገርና ህዝብ ያለው አማራጭ ፅንፈኝነትን በማክሰም አንድነቷ የተጠናከረ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ለውጡን ማስቀጠል መሆኑ ላይም መግባባት መፈጠሩም መግለጫው አመላክቷል።