የወራቤ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው

የወራቤ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ጀማል ከድር ለዋልታ ቴሌቪዥን ገልጸዋል፡፡

ሆስፒታሉ የተሟላ የህክምና ቁሳቁስ ከመያዙም ባሻገር በእያንዳንዱ የህክምና ክፍል (ዋርድ) ውስጥ ቢያንስ ሁለት ሃኪሞች(ዶክተር) እና አንድ ስፔሻላይዝድ ሃኪም እንደሚገኝም ዶክተር ጀማል አስረድተዋል፡፡

ሆስፒታሉ በስልጤ ዞን ዉስጥ በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተገነባ ሲሆን ባለሙያዎችም ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉም ሜዲካል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በሆስፒታሉ በህክምና ላይ የነበሩና ዋልታ ያነጋገራቸው ህሙማንም ሆስፒታሉ የተሟላ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን መስክረዋል፡፡

ሆስፒታሉ ከግንባታው ጀምሮ እስከ ያዛቸው የህክምና ቁሳቁስ አንጻር የተሟላ መሆኑ ለህሙማን የተሟላና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻሉን ባለሙያዎቹ አስረድተዋል፡፡

የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባደረገው ግምገማ ሆስፒታሉ 88 በመቶ የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ መረጋገጡን ዶክተር ጀማል ተናግረዋል፡፡

አንድ ሆስፒታል 80 በመቶ የተሟላ አገልግሎት መስጠት ከቻለ ወደ ልህቀት ማዕከልነት እንደሚያድግ ዶክተር ጀማል ጠቁመው የወራቤ ሆስፒታልን ወደ ልህቀት ማዕከልነት ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡