የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አሠጣጡን ሊያሻሽል ይገባል ተባለ

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አሠጣጡን ሊያሻሽል እንደሚገባ ዋልታ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡   

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ በተጨናነቀ ትራፊክ በታክሲ በመጓዝ ከሚያደርስባው እንግልት የታደጋቸው ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ የሚታየውን  የመዘግየት ችግር ሊያሻሽል ይገባል፡፡

ባቡሩ እየዘገየ በሚመጣበት ወቅት በየፌርማታውና በባቡር ውስጥ ከፍተኛ መጨናነቅ እየተፈጠረ ተሳፋሪዎች ለተለያዩ ችግሮች እየዳረገ እንደሚገኝም ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡

ከችግሮቹም መካከል ለተላላፊ በሽታዎች መጋለጥና ለተለያየ ዝርፊያ መዳረግ ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ በበኩላቸው በነዋሪዎቹ የተነሱት ቅሬታዎች አግባብ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

የኃይል መቆራረጥ፣ የመለዋወጫ አለመኖርና፣ የፋይናንስ እጥረት የችግሮቹ መንስዔዎች መሆናቸውን አቶ ደረጀ ገልጸው ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡