ሀገራቸውን ለ52 ዓመታት በዲፕሎማትነት ያገለገሉት አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ እውቅና ተሰጣቸው

ኢትዮጵያን ለ52 ዓመታት በተለያዩ ሀገራትና ተቋማት በመወከል በዲፕሎማትነት ያገለገሉት አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ የአገልግሎት ዕውቅና ተሰጣቸው፡፡

አምባሳደር ቆንጅት የአገልግሎት እውቅናው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በትናንትናው ዕለት ተሰጥቷዋል፡፡

ይህ ሽልማት አምባሳደሯ ለረጅም ዓመታት  ላበረከቱት ስኬታማ አገልግሎት  እንደተበረከተላቸው ተነግሯል፡፡

አምባሳደር ቆንጂት በግብፅ ፣ በእስራኤል ፣በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሀገራቸውን  በዲፕሎማትነት በመወከል ውጤታማ ስራ ማስመዝገባቸው ተገልጿል።

አምባሳደሯ ከምንም በላይ ሀገራቸውን በማስቀደም በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያበረከቱት አስተዋፅኦም ለሌሎቸ ዲፕሎማቶች አርዓያ የሚሆን ነው ተብሏል።

አምባሳደሯ ለተደረገላቸው እውቅና ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ፥በቅርቡ  የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በሀገሪቱ ትልልቅ ቦታዎች ላይ ሴቶች እንዲሾሙ መደረጉንም አድንቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን በመወከል የሚሰሩ አምባሳደሮችም ለሀገራቸው ጥቅም  ቅድሚያ በመስጠት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአምባሳደር ቆንጂት በተጨማሪም በተለያዩ ሀገራት በአምባሳደርነት ሲሰሩ ቆይተው በጡረታ ለተሰናበቱ ቀደምት ዲፕሎማቶች የሰርተፊኬት ዕውቅና ሰጥቷል።(ኤፍቢሲ)