በኬንያ በተፈጸመ ጥቃት 12 ሰዎች ተገደሉ

በኬንያ በተፈጸመ ጥቃት 12 ሰዎች መገደላቸውን የሃገሪቱ ፖሊስ ገለጸ።

በሃገሪቱ ሰሜናዊ ምስራቅ ክፍል በምትገኘው ማንዴራ ከተማ በተፈጸመው ጥቃት፥ የታጣቂው አል ሸባብ እጅ ሳይኖርበት እንደማይቀርም ነው ፖሊስ የገለጸው።

በተቀጣጣይ ፈንጅዎች የተፈጸመው ጥቃት በአብዛኛው ክርስቲያኖችን ኢላማ ያደረገ ነበር ተብሏል።

እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆቹ ጥቅምት ወር መጀመሪያ አካባቢም ታጣቂ ቡድኑ በፈጸመው ጥቃት ስድስት ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ነው። 

ጥቃቱ ክርስቲያኖችን ከአካባቢው ለማስወጣት ያለመ መሆኑን ቡድኑ በወቅቱ ገልጿል።

ይህን መሰሉ የቡድኑ አካሄድ ግን በአካባቢው አብዛኛውን ቁጥር በሚይዙት ሙስሊም ኬንያውያን ዘንድ አልተወደደም።    

የቡድኑ እንቅስቃሴ የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን በማመሰቃቀል ወደ ከፋ ችግር እንዳይከታቸውም በተደጋጋሚ ስጋታቸውን ገልጸዋል። 

አልሸባብ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ወደ ከተማይቱ የገቡ ክርስቲያን ዜጎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ፍላጎት እንዳለው፥ ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚዲያ ተቋማት ዘገባ ያስረዳል።

ኬንያን ከሶማሊያ የምታዋስነው ማንዴራ ከተማ ደካማ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያለባት እንደሆነች ይነገራል።

በከተማዋ አብዛኛው የመንግስት ስራ እና የንግድ እንቅስቃሴ ከመካከለኛው ኬንያ በሚመጡ ኬንያውያን የሚካሄድ ነው።(ኤፍ ቢ ሲ)