የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ቀን ተከበረ

የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ኢንዱስትሪ ቀን በየዓመቱ ህዳር 20 ቀን እንዲከበር በወሰነው መሰረት የዘንድሮ በዓል ትናንት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ተከብሯል፡፡

የአፍሪካን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን ኢንዱስትሪ ወሳኝ በመሆኑ አፍሪካውያን ለኢንዱስትሪ ልማት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው በዕለቱ ተገልጿል፡፡

የዘንድሮ የአፍሪካ ኢንዱስትሪ ቀን ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት 50ኛ ዓመት በዓል ጋር መከበሩ የተለየ ያርገዋል ተብሏል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የንግድና ኢንዱስትሪ ተወካይ የአፍሪካን የኢንዱስትሪ ጉዞ ለማቀጣጠል የግልና መንግስታዊ የገንዘብ ተቋማት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ ፍሰት፣ ምቹና አስተማማኝ ፖሊሲ፣የመንግስታት ቁርጠኝነት የአፍሪካን ኢንዱስትሪ ለማፋጠን ወሳኝ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

በጉባዔው እንደተመለከተው ከሰሀራ በታች በሚገኙ አገራት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እያደገ ነው፡፡ እአአ በ2010 ዓ.ም 28 ቢሊዮን ዶላር የነበረው የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት በ2015 ዓ.ም 40 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡

ቀኑ ‹‹የአፍሪካን ኢንዱስትሪ በገንዘብ ለመደገፍ ያሉ ተግዳሮቶችና ምቹ ሁኔታዎች›› በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡

እአአ በ2063 የበለፀገች አፍሪካን ዕውን ለማድረግ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ማጠናከር እንደሚገባ መመልከቱን ዋልታ ዘግቧል፡፡