የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ጥሎት የነበረውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ አራዘመ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤቱ በኤርትራ እና ሶማሊያ ላይ ጥሎት የነበረውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ አራዘመ።

ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው ስብሰባ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ የቆይታ ጊዜን ያራዘመው አሁንም ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው አሸባሪ ቡድን አልሸባብ ለደህንነት ስጋት ሆኖ መቀጠሉን በመግለፅ ነው።

ምክር ቤቱ የተመድ የሶማሊያ እና ኤርትራ ተቆጣጣሪ ቡድን የሥራ ጊዜንም በአንድ ዓመት አራዝሟል።

የኤርትራ መንግስት በተለይም ስለያዛቸው ጅቡቲያውያን የጦር እስረኞች ለተቆጣጣሪ ቡድኑ መረጃ እንዲሰጥ እና ቡድኑ እንዲገባ እንዲፈቅድ አሳስቧል።

የውሳኔ ሀሳቡ በአስር የድጋፍ ድምፅ እና በአምስት ታቅቦ ነው ያለፈው።

ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ የምክር ቤቱ አባል አገራት ለውሳኔው ያላቸውን ድጋፍ ገልፀዋል።

የውሳኔ ሃሳቡን ያረቀቀቸው ብሪታኒያ ተወካይ የጦር መሳሪያ ማዕቀቡ መራዘም አልሸባብ የሚያገኘውን ድጋፍ የሚቆርጥ እና የሶማሊያን የተፈጥሮ ሀብት የሚጠብቅ ነው ብለዋል።

በተለይም ኤርትራን በተመለከተ በዚያች አገር የተለወጠ ነገር ባለመኖሩ መሻሻሎች አሉ የሚለውን አገራቸው እንደማትቀበል አስታውቀዋል።

የአስመራ መንግስት ተባባሪ ባለመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ በጉዳዩ ላይ እጁ መታሰሩንም አመልክተዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ አለመተባባር በአገሪቱ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ አያስችልም ብላለች።

ታህሳስ ወር 2009 ላይ የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ጠንቅ የሆነውን አልሸባብን በገንዘብ እና በቁሳቁስ እንደምትደግፍ በማስረጃ በማረጋገጡ በአገሪቱ ላይ የጦር መሳሪያ ግዢ፣ በተመረጡ የመንግስት ባለሰልጣናት ላይ የጉዞ ገደብ እና ሀብታቸውን እንዳያንቀሳቅሱ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።

እንዲሁም በአውሮፓውያኑ 2009 ላይ አገሪቱ ከጎረቤቷ ጅቡቲ ጋር ጦርነት በመግባት በሃይል ከያዘችው ግዛት ለቃ ለመውጣት ፈቃደኛ አለመሆኗም ማዕቀቡ እንዲጣልባት አድርጓል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)