የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በሶማሊያ የተጣለውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እየጣሰች መሆኑ ተገለጸ

የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የመንግስታቱ ድርጅት በሶማሊያ ላይ የጣለዉን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እየጣሰች ስለመሆኗ ተገለፀ።

ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የማዕቀብ ጣይ ኮሚቴ የተወጣጣ የባለሙያዎች ቡድን ያወጣዉ ሪፖርት እንዳሳየዉ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የፀጥታዉ ም/ቤት በሶማሊያ ላይ የጣለዉን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እየጣሰች ስለመሆኗ አመላክቷል።

አልጀዚራ ከታማኝ ምንጮች አገኘሁት ያለዉ ሪፖርት እንዳሳየዉ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የመንግስታቱ ድርጅት በሶማሊያ ላይ የጣለዉን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ በመተላለፍ በሀገሪቱ የሶማሊላንድ ግዛት ዉስጥ የጦር ሰፈር መገንባቷ እና የጦር መሳሪያዎችንም ወደ ሶማሊያ እያጓጓዘች ስለመሆኗ ጠቁሟል።

የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ወታደራዊ ሰፈሩን መገንባት የጀመረችዉ ባለፈዉ አመት ሲሆን ለግንባታዉም ከእራስ ገዟ የሶማሊያ ግዛት ሶማሊላንድ መሪዎች ጋር ስምምነት ፈፅማለች። ሶማሊላንድ ከ991ዱ የሶማሊያ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ከእናት ሀገሯ ሶማሊያ ተነጥላ በእራስ ገዝ አስተዳደርነት ትመራለች።

የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ከጦር ሰፈር ግንባታም ባለፈ በሶማሊ ላንድ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎችን በመስራት ላይ ትገኛለች። ለአብነትም በየመን ድንበር አቅራቢያ የሚገኘዉን ወደብ በማልማት የየመን ሀዉቲ አማፂያንን ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በመሆን ላለፉት ሶስት አመታት ስትወጋ መቆየቷም የሚታወስ ነዉ።

ሶማሊያ ግን ድርጊቱን በተደጋጋሚ በመቃወም የመንግስታቱ ድርጅት በወታደራዊ ሰፈሩ ግንባታ ላይ አስፈላጊዉን እርምጃ እንዲወስድ በተደጋጋሚ አቤቱታዋን ስታቀርብ ቆይታለች።

የባለሙያዎቹ ቡድን በጦር መሳሪያ ባዕቀቡ መጣስ ዙሪያ የሶማሊ ላንድ ግዛት አስተዳሪዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ ቢጠይቅም ምንም ምላሽ ማግኘት እንዳለቻለ ተነግሯል።

በተመሳሳይ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የተጠየቀዉ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች መንግስት ማብራሪያ ከመስጠት ይልቅ ለግዛቲቱ በተሰጠዉ ህገ መንግስታዊ ስልጣን መሰረት ትክክለኛዉን ዉል ከሶማሊ ላንድ ግዛት አስተዳዳሪዎች ጋር ስለመፈፀሙ ገልጧል።  

ሪፖርቱ በ2017 ቻይና ሰራሽ መሳሪያዎች ወደ ሶማሊ ላንድ ስጓጓዙ መያዛቸዉን ይፋ ያደረገ ሲሆን ቻይና ግን እጄ ከደሙ ንፁህ ነዉ ከማለት ባለፈ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ስለመቆጠቧ ተነግሯል።

በተመሳሳይም የሰርቢያ መንግስት በወቅቱ ከተያዙት መሳሪያዎች መካከል 1000 ያክሉን በ2016 ለተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ስለመሸጡ ገልፆ ሆኖም መሳሪያዎቹን የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ወታደሮች ይጠቀሙበታል በሚል ስምምነት እንደነበር አስታዉቋል።

በመንግስታቱ  ድርጅት የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች አምባሳደር ላና ኑሴቤህ ሪፖርቱ ይፋ ሆኖ ባለመታተሙ በጉዳዩ ላይ ምንም ማለት አልችልም ብለዋል። በተጨማሪም ሀገራቸዉ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታዉ ም/ቤት ዉሳኔዎችን እንደምታከብር በመግለፅ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፀጥታዉ ም/ቤት ፕሬዝደንት ዚያድ ባሬ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ለአመታት በሶማሊያ የዘለቀዉን ደም መፋሰስ ለማስቆምና የጦር መሳያ በአሸባሪዎች እጅ እንዳይገባ ለማድረግ በፈረንጆቹ 2012 የጦር መሳሪያ ማዕቀብ በሶማሊያ ላይ መጣሉ የሚታወስ ነዉ ሲል የዘገበዉ አልጀዚራ ነዉ።