ሶማሊያውያንን ከድርቅ ለመታደግ የእርዳታ ጥሪ ቀረበ

በሶማሊያ በተከሰተው ድርቅ ለምግብ እጥረትና ውሃ ጥም የተጋለጡ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥሪ አቀረበ፡፡

በሶማሊያ እየተስፋፋ ያለው ድርቅ በዜጎች ላይ እያሳረፈ ያለውን መጠነ ሰፊ ችግር ለመከላከል ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋ ድርጅቱ ማሳሰቡን በድረ ገፁ አስነብቧል፡፡

በሶማሊያ የተሰማሩ የእርዳታ ድርጅቶች ችግሩ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን በሶማሊያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ሚስተር ፒተር ዲ ክለርክ ተናግረዋል፡፡

በፑንት ላንድና በሶማላንድ የተከሰተው ድርቅ በአገሪቱ ደቡባዊና ማዕከላዊ አካባቢዎች እየተስፋፋ መምጣቱን አስተባባሪው በናይሮቢ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም በርካታ ነዋሪዎች ለችግር ተጋላጭ ሆነዋል  ነው የተባለው  ፡፡

‹‹ችግሩ በጣም ኣሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል›› ያሉት አስተባባሪው የእርዳታ ድርጅቶች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ድርቁን ተከትሎ የተከሰቱና የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል የበኩላቸውን ጥረት እንዲያርጉ አሳስበዋል፡፡

እአአ በ2016 ለሰብዓዊነት ድጋፍ ምላሽ ዕቅድ ከተጠየቀው 885 ሚሊዮን ዶላር እስከ አሁን ማግኘት የተቻለው 47 በመቶውን ብቻ መሆኑን ሚስተር ዲ ክለርክ ገልፀዋል፡፡

ዓመቱ ሊጠናቀቅ አራት ሳምንታት ብቻ እየቀሩት ከግማሽ በታች ገንዘብ መለቀቁ በሰብዓዊ ድጋፍ ጥረቱ ላይ የራሱን ጥላ ማጥላቱን ነው ያስገነዘቡት፡፡

ድርጅቱ እንዳስታወቀው ከአገሪቱ ህዝብ 40 በመቶ የሚሆኑትና አምስት ሚሊዮን የሚጠጉት ዜጎች በቂ ምግብ እያገኙ አይደለም፡፡ ከእነዚህ ደግሞ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት በከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውን  ነው ያመለከተው ፡፡

ከ50ሺ በላይ ህፃናት በጣም በከፍተኛ ጉዳት ውስጥ ሲሆኑ ከአምስት ዓመት ዕድሜ በታች የሚገኙ 320ሺ ህፃናት በምግብ እጥረት በመጎሳቆላቸው ሰውነታቸው ከሚጠበቀው መጠን በታች መሆኑን  አረጋግጧል ፡፡

በአገሪቱ ያለው ግጭት ሌላው ራስ ምታት መሆኑን ድርጅቱ ጠቁሞ ዓለም ዓቀፍ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ከአካባቢው መውጣትም የሰብአዊ ድጋፍ ሂደቱን እየተፈታተነው  እንደሚገኝ ተመልክቷል ፡፡

ከ34ሺ በላይ ዜጎችም ከመኖሪያ አካባቢያቸው በመፈናቀል ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እየተሰደዱ ነው የተባለው ፡፡