በደቡብ ሱዳን ወታደራዊ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ታዳጊ ልጆች ወደ ቀድሞ ህይወታቸው ለመመለስ እየተሰራ ነው

በደቡብ ሱዳን ወታደራዊ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ታዳጊ ልጆች ወደ ቀድሞ ህይወታቸው እንዲመለሱ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑ ተገልጸዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን ያምቢኦ ግዛት በሀገሪቱ ረጅም ጊዜ በወሰደው የእርስ በርስ ጦርነት ለመሳተፍ የተገደዱ ሕፃናት ወታደሮች አሁን ላይ ከወታደራዊ ሀይሉ ውጪ ተደርገዋል፡፡

ይህ ቢሆንም ግን እነዚህ ህፃናት ወደ ቀድሞ  ኑሮአቸው  ተመልሰው ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ለመኖር ባሳላፉት አስከፊ ግዜ የተነሳ ስቸገሩ ይስተዋላል፡፡

የህክምና ማዕከሉ ሳንስ ፍሮንተርስ ታዳጊዎቹ ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ማህበራዊ ህይወታቸው የተስተካከል እንዲሆን ለማስቻል የአእምሮ ጤናቸውን መጠበቅ የሚያሥችሉ ፕሮግራሞችን ቀርፆ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ግጭቶች ዜጎቻቸው በርካታ አስከፊ ግዜዎችን አንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም እጅግ አስከፊ ከሆኑት ክስተቶች  አንዱ ታዳጊ ህጻናት በግዴታ የጦር ሀይሉን እንዲቀላቀሉ መደረጉ እና ታዳጊ ተዋጊዎቹ በታላላቆቻቸው የሚታዘዙትን ሁሉ ሳይረዱት መተግበራቸው ነው፡፡

በጦርነቱ ላይ የተካፈሉት  ታዳጊዎች  ብዙውን ጊዜ የስሜት ቀውስ ያጋጥማቸዋል ተብሏል፡፡ ምክኒያቱ ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው  ተገደው ተለይተው የወንጀል ስራዎችን እና ከባድ የጉልበት ስራ እንዲሰሩ ሲደረጉ መቆየታቸው፣ ፆታዊ ጥቃት እና ድብደባ ሲፈፀምባቸው መቆየታቸው አሁን ላይ ህፃናቱን ለጭንቀት ይዳርጋቸዋል ሲሉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ግን መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በጋራ በመሆን  እነዚህ  ሕጻናት ወደ ማህበረሰባቸው  እንዲመለሱ እየሰሩ ይገኛሉ ነው ተባለው፡፡

በሳንስ ፍሮንተርስ ህክማና ማዕከል ውስጥ የሚገኙ የስነአእምሮ ባለሙያዎች ለልጆች የአእምሮ ጤና ጥበቃ በሚሰጡት አገልግሎት 632 ታዳጊዎች መርዳታቸውን ነው ያስታወቁት፡፡

በርካታ ህጻናት እርግጠኛ ያልሆኑበትን የወደፊት ጊዜ እንደምፈሩና በማኅበረሰባቸው ውስጥ እንዴት እንደሚቀበሉ እና ህይወታቸው ምን እንደሚሆንላቸውም ይሰጋሉ፡፡ ለዛም ነው ልጆቹ አፋጣኝ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሉም ባለሙያዎቹ ያብራራሉ፡፡

የቀድሞ ወታደሮቹ ታዳጊዎች ወደ ህብረተሰባቸው ሲመለሱ ተቀባይነትን አለማግኘታቸው፤ ለልጆቹ ፈታኝ ነው ተብሏል፡፡ ከታጣቂ ቡድኖች ጋር ያደጉ ህፃናቱ ከሲቪሉ ማህበረሰብ ጋር ሲቀላቀሉ በፍራቻ ነው ሲሉም የዘርፉ ሙያተኞች ይሟገታሉ፡፡

በሳንስ ፍሮንተርስ የህክምና ማዕከል የዚህ ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ ፖል ሚነን  ሁሉም ልጆች ለማለት በሚያስችል ደረጃ  ወደ መደበኛው ኑሮአቸው  ለመመለስ ይፈልጋሉ፡፡ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ እንደሚፈልጉ በመረዳታቸውም ለልጆቹ አዲስ ሕይወት ለመስጠት የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት፡፡

የተጀመረው ፕሮግራም ህፃናቱ ህይወታቸውን እንዲቀይሩ የሚረዳቸው ቢሆንም በሀገሪቱ መሰል እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከ19 ሺ 500 በላይ የሚገመቱ ታዳጊዎች በመኖራቸው ብዙ መስራት ይጠበቃል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡ (ምንጭ፤ ሱዳን ትሪቡን)