የእንግሊዝ መገበያያ ገንዘብ ፓውንድ የምንዛሬ ዋጋ ማንሰራራት ጀመረ

ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት ለመውጣት ያቀረበችው ጥያቄ  ውድቅ መደረጉን ተከትሎ የእንግሊዙ መገበያያ ገንዘብ ፓውንድ የምንዛሪ ዋጋ መንሰራራት ጀምሯል እየተባለ ነው፡፡

ታላቋ ብሪታኒያን ወክለው ከሁለት አመታት በላይ ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት ድርድር ሲያደርጉ የነበሩት የእነግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ሃሳባቸው ለጊዜው የተሳካ አይመስልም፡፡ ምክኒያቱም ብሪታንያ ከህብረቱ ለመውጣት ያቀረበችውን ጥያቄ ተከትሎ የሀገሪቱ ፓርላማም በ432 ተቃውሞና በ202 የድጋፍ ድምፅ ጉዳዩን ውድቅ አድርጎታልና፡፡

ይህንንም ተከትሎ ባለፉት አመታት ከአውሮፓ ህብረት አባላት ጋርም ሆነ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ሀገሪቱ ያላት የንግድ ግኑኝነት እየተቀዛቀዘ መቷል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ፓውንድም ከነበረበት ምንዛሪ መውረድና የመዋዥቅ ሁኔታ ባለፉት አመታት ተስተውሏል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ደጋግመው ሲያነሱት እንደነበረው ሀገሪቱ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት ለመውጣት ባደረገችው እንቅስቃሴ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት አለመረጋጋትና መውረድ የታየበት ዋነኛው ምክኒያት የፓውንድ ዋጋ መውረድ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

ለዚህ ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ሀገሪቷ ከህብረቱ ጋር ፍች ለመፈፀም ያነሳችው ሀሳብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ብዙሃኑ ጣቱን ወደ ጠ/ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ እንዲጠቁሙ አድርጓል፡፡ ለዚህም ነው የፓርላማ አባላቱ የሰጡትን አነስተኛ የድጋፍ እና አብላጫ የተቃውሞ ድምፅ ተከትሎ የሀገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ፓውንድ መጨመሩ እየተነገረ የሚገኝው፡፡

የተሰጠውን ድምፅም ተከትሎ በርካታ ነጋዴዎች ደስተኛ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን በተለይም በአውሮፓ ህብረት እና በብሪታንያ መካካል የነበረው ግኑኝነት መልካም አለመሆኑ የፈጠረውን ተፅእኖ የሚቀርፍ እና የንግድ ግኑኝነቱንም የሚያሻሽል እንደሚሆን ተጠብቋል፡፡

የድምፅ አሰጣጡ ውሳነ ከመተላለፉ በፊት አጠቃላይ የፓውንድ ዋጋ 1 ነጥብ 2 በመቶ የነበረ ሲሆን በየቀኑ 0 ነጥብ 1 በመቶ ይቀንስ እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡ ይህ ደግሞ ከዩሮ አንፃር ሲታይ በግማሽ መወረዱን የዘርፉ ሙያተኞች ያብራራሉ፡፡

ይሁንና ከድምጸ-ውሳኔው በኋላ የፓውንድ ዋጋ በፍጥነት መሻሻሉ እየተገለጸ ነው፡፡ ይህም በተለይም ተቀዛቅዞ የነበረውን የኢንቨስትመንት እና አጠቃላይ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው እንዲያንሰራራ  እድል ሊከፍት የሚችል እንደሆነም ተገምቷል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡