ካናዳ ለ18 አመቷ ሳዑዲ አረቢያዊት ጥገኝነት መስጠቷን አስታወቀች

ካናዳ ለአስራ ስምንት አመቷ ሳዑዲ አረቢያዊት ወጣት ራሃፍ ሞሃመድ አል ኩኑን ጥገኝነት መስጠቷን አስታወቀች፡፡

ራሃፍ ሞሃመድ አል ኩኑን የሳዑዲ ዜግነት ያላት የአስራ  ስምንት አመት ወጣት ናት፡፡

ወጣቷ ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያዎች በለቀቀችው ተንቀሳቃሽ ምስል ምክንያት ዓለማቀፍ ትኩረትን ይዛ ሰንብታለች፡፡

ወጣቷ ከቤተሰቦቿ ጋር ለመዝናናት ወደ ኩዌት ባቀናችበት ወቅት ከቤተሰቦቿ ተደብቃ ወደ አውስትራሊያ ለመጓዝ የአውሮፕላን የጉዞ ትኬት ቆርጣ ወደ ታይላንድ ባንኮክ ትጓዛለች፡፡

በባንኮክ አየር ማረፊያ እንደደረሰችም ከቤተሰቦቿ አምልጣ እንደመጣችና ተመልሳ ወደ ሳዑዲ ብትሄድ ግድያ እንደሚጠብቃት  በመግለጽ በአውስታራሊያ ጥገኝነት ማግኘት እንደምትፈልግ በማህበራዊ ሚዲያዎች በለቀቀችው ተንቀሳቃሽ ምስል ለአለም ታሳውቃለች፡፡

ወጣቷ ይህን ትበል እንጂ የታይላንድ ኢሚግሬሽን ሰራተኞች ወደ መጣችበት ሊመልሷት ሞክረው ነበር፡፡

የዚህች ልጅ ጉዳይ የአለምን ቀልብ የሳበ በመሆኑ ወጣቷ በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ ጥላ ስር ሰንብታ ቆይታለች፡፡

ልጅቷ ጥገኝነት ከጠየቀችበት ሀገር አውስትራሊያ ምንም አይነት ምላሽ ሳይገኝ ቀናቶች የተቆጠሩ ቢሆንም ከወደ ካናዳ ወጣቷንም ሆነ የአለምን ማህበረሰብ ያስደሰተ ዜና ተሰምቷል፡፡

ካናዳ ለዚህች ወጣት እንስት ጥገኝነት መስጠቷን አስታውቃለች፡፡

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒሰትር ጀስቲን ቱሩዶ የተባበሩት መንግስታትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የወጣቷን የጥገኝነት ጥያቄ መቀበላቸውን ተናግረዋል፡፡

ድራማዊ ክስተትን ያስተናገደችው ይህች የ18 አመት ወጣት ማረፊያዋ ካናዳ ሆኗል፡፡

አዲሱን የህይወት ምዕራፏንም በካናዳ አሃዱ ብላ ጀምራለች፡፡

ካናዳ ስትደርስም በሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቀባበል ተደርጎላታል፡፡

በቅርቡ ካናዳ በሚቀጥሉት 3 አመታት ውስጥ ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን የመቀበል እቅድ እንዳላት አስታውቃ እንደነበር አስታውሶ ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡