አየር መንገዱ ወደ ዊንድሆክ በረራ ሊጀምር ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመጪው ጥቅምት ጀምሮ ወደ ናምቢያ ርዕሰ መዲና ዊንድሆክ አዲስ በረራ ሊጀምር ነው።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንዳሉት፥ በረራው መጀመሩ ወደ ናምቢያ ለሚጓዙ ደንበኞች ምቹ የጉዞ አማራጭ ይሆናል።

አዲሱ መስመር አየር መንገዱ በአፍሪካ የሚያደርገውን በረራ ወደ 53 ከፍ ያደርገዋል።

በቦትስዋና ዋና ከተማ ጋቦሮኒ በኩል ወደ ዊንድሆክ የሚደረገው በረራ በቦይንግ 737 አውሮፕላን ነው።

አውሮፕላኑ 15 ዘመናዊ የክላውድ ናይን እና 138 የቢዝነስ ክፍል መቀመጫዎች አሉት።

አየር መንገዱ በረራውን በማስፋት በአህጉሪቱ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰራ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

የናምቢያ ዋና ከተማ ዊንድሆክ የአገሪቱ ትልቋ ከተማ ስትሆን ብሔራዊ ተቋማትና የተለያዩ ድርጅቶችን በውስጧ ይዛለች።(ኤፍ.ቢ.ሲ)