የቻይናና የኢትዮጵያን የንግድ ግንኙነትን የማጎልበት አቅም ያለው የቻይና ንግድ ሳምንት በትናንትው ዕለት በአዲስ አበባ ተከፈተ ።
የቻይና የንግድ ሳምንት ከሰኔ 27 እስከ ሰኔ 29 ድረስ በኃይል ፣ በኤሌክትሪክ ሥራ ፣ በግንባታ፣ በማሽን ፣ በአልባሳት ፣በጨርቃጨርቅ ፣ ጤናና ውበት ዘርፎች የተሠማሩ 38 የቻይና ትልልቅ ኩባንያዎችን በማሳተፍ እየተካሄደ ይገኛል ።
የቻይና የንግድ ሳምንት በቻይና የንግድ ምክር ቤትና በቻይና ዓለም አቀፍ የንግድ ምክር ቤት ድጋፍ እየተካሄደ መሆኑን ተመልክቷል ።
ንግድ ሳምንቱ አስተባባሪ ሚቼል ሜይሪክ እንደተናገሩት በአዲስ አበባ የተከፈተው የቻይና ንግድ ሳምንት በአጠቃላይ 38 የሚሆኑ የቻይና የንግድ ተቋማት እየተሳተፉበት ሲሆን ምርትና አገልግሎታቸውን ለኢትዮጵያ ገበያ እያስተዋወቁ ነው ብለዋል ።
እንደ ሜይሪክ ገለጻ የንግድ ትርኢቱ የአገር ውስጥ የንግድ ማህበረሰብ ከቻይና ትልልቅ የንግድ ተቋማትና ኩባንያዎች ጋር የጠበቀ የንግድ ግንኙነት እንዲመሠርቱ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ።
በኢትዮጵያ በዘንድሮ የበጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ከተጀመሩ 121 የውጭ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ውስጥ 40 የሚሆኑት በቻይና ኩባንያዎች የሚከናወኑ ሲሆኑ በአጠቃላይ ከ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል የሚካሄዱ ናቸው ብለዋል አስተባባሪው ።
ቻይና በኢትዮጵያ የምታደርገው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ዓመታዊ የቻይና የንግድ ሳምንትን በኢትዮጵያ ለማዘጋጀት ዕቅድ ተይዟል ።
ለሦስት ቀናት በሚካሄደው የቻይና የንግድ ሳምንት አውደ ርዕይ ከ3ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ይጎበኙታል ተብሎ ይጠበቃል ።