ኢትዮጵያ በአጎዋ የገበያ እድል ተጠቅማ የምትልከው የምርት መጠን በ62 በመቶ አድጓል

ኢትዮጵያ አሜሪካ ለአፍሪካ ሃገራት በፈቀደችውና ከቀረጥና ከኮታ ነጻ የገበያና የዕድገት እድል (አጎዋ) የምትልከው የምርት መጠን እድገት ማሳየቱ ተገለጸ።

በምስራቅ አፍሪካ የአለም አቀፉ የአሜሪካ ልማት ተራድኦ ድርጅት ማዕከል ከጥቅምት 2017 እስከ መስከረም 2018 ባለው ጊዜ ውስጥ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት፥ በአጎዋ እድል በመጠቀም ወደ አሜሪካ የሚልኩት የምርት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጿል።

ኢትዮጵያም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 137 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ስትልክ፥ በእድሉ በመጠቀም የላከችው የምርት መጠን ደግሞ በ62 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ነው ያለው።

በዚህ ጊዜ ውስጥ ከተላኩት ምርቶች መካከል አልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ ከፍተኛውን መጠን ይይዛሉም ነው የተባለው።

ኢትዮጵያም አሁን የምትልከውን የምርት መጠን ማስቀጠል ከቻለችም በአጎዋ የገበያ እድል በመጠቀም፥ ሁለተኛዋ ከፍተኛ ምርት ላኪ ሃገር ትሆናለችም ነው ያለው የማዕከሉ መረጃ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ማዳጋስካር፣ ታንዛኒያ፣ ሞሪሺየስ እና ቡሩንዲ በአጎዋ እድል ተጠቃሚ ሃገራት ናቸው።

ኬንያ በእድሉ በመጠቀም ቀዳሚዋ ሃገር ስትሆን፥ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 454 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ወደ አሜሪካ ልካለች።

መረጃው የቀጠናው ሃገራት በ11 ወራት ውስጥ ወደ አሜሪካ የላኩት የምርት መጠን 1 ቢሊየን ዶላር እንደሚጠጋም አመላክቷል።

ከዚህ ውስጥ የአልባሳት ምርቶች 84 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ አላቸው።

አጎዋ በፈረንጆቹ 2000 አሜሪካ የአፍሪካ ሃገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥና ከኮታ ነጻ በሆነ መልኩ እንዲያስገቡ የጀመረችው የገበያ እድል ነው። (ምንጭ፡ ኤፍ ቢ ሲ)