የሰው ልጅ በህይወት የመኖሪያ እድሜ ጣሪያ 115 አመት ሊሆን እንደሚችል አንድ ጥናት ጠቆመ

የሰው ልጅ በህይወት የመቆያ እድሜ ጣሪያ 115 አመት ሊሆን እንደሚችል ተመራማሪዎች ተናገሩ።

በሰዎች እድሜ ላይ ለአስርት አመታት በተደረገ ጥናት ነው ተመራማሪዎቹ እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሱት።

የዚህ ጥናት ውጤትም በኔቸር ጆርናል ላይ ታትሟል።

ጥናቱ የሰው ልጆች የእድሜ ጣሪያን 115 ቢያደርገውም በጣም ጥቂት ሰዎች ግን ከዚህም በላይ ሊኖሩ እንደሚችሉ አመላክቷል።

በኒውዮርክ በተደረገው ጥናት በፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ ብሪታንያ እና አሜሪካ ከ110 በላይ እድሜ የነበራቸው ሰዎች አሟሟት ተዳሷል።

በዚህም መቶን የተሻገሩ ሰዎች በህይወት የመቆየት እድላቸው እየቀነሰ እንደሚመጣ ተረጋግጧል። 

አንዳንድ ተመራማሪዎች የጥናቱን ውጤት ቢያደንቁም የሚቃወሙትም አልጠፉም።

በአልበርት አንስታይን የህክምና ኮሌጅ ውስጥ የሚሰሩትና የጥናቱ ተሳታፊ ፕሮፌሰር ጃን ቪጅ፥ እድሜያቸው ከ105 አመት በላይ የሆኑ አዛውንቶች በአብዛኛው ወደ ሰው ልጅ የእድሜ ጣሪያ እየተጠጉ የሚመጡ ናቸው ብለዋል።

ለፕሮፌሰር ጀምስ ቫውፔል ግን በጥናቱ የተጠቀሰው በህይወት የመቆያ እድሜ ጣሪያ በጣም የተጋነነ ነው።

ጥናቱ ከዚህ ቀደም ተመራማሪዎች የእድሜ ጣሪያው 65፣ 85 እና 105 ነው በማለት ያወጡትን ጥናት ውድቅ ለማድረግ ብቻ እንጂ የጨመረው ምንም አይነት አዲስ ሳይንሳዊ ግኝት የለም ብለዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ቫውፔል ገለፃ በህይወት የመኖሪያ እድሜን ጣሪያን መወሰን አይቻልም።

አመጋገብ፣ የኑሮ ዘይቤ እና የመኖሪያ አካባቢ የአየር ሁኔታ ናቸው በህይወት የመቆየት እድልን የሚወስኑት ባይ ናቸው።

ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ በህይወት የመቆያ እድሜ እድገት እያሳየ መጥቷል።

ለዚህም የክትባቶች መስፋፋት፣ የጤናማ ህፃናት ውልደት እንዲሁም እንደ ካንሰር እና የልብ ህመም ያሉ በሽታዎችን ለመቆጣጠር የተከናወኑ ተግባራት በአበይት ምክንያትነት ተቀምጠዋል።( ኤፍቢሲ)