በቀን ከስድስት ሰዓት በታች መተኛት ለልብ ሕመም እና ስተሮክ እንደሚያጋልጥ ጥናት አመላከተ

በቀን ከስድስት ሰዓት በታች መተኛት ለልብ ሕመም እና የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ (ስትሮክ) እንደሚያጋልጥ አንድ ጥናት አመላክቷል፡፡

በ24 ሰዓታት ውስጥ ከስድስት ሰዓት በታች እንቅልፍ የሚተኙ ሰዎች ከሰባት እስከ ዘጠኝ ሰዓታት ከሚተኙ ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ በልብ ሕመም እና ስትሮክ የመጠቃት ዕድላቸው 35 በመቶ እንደሚጨምር ነው የአሜሪካ የልብ ህክምና ኮሌጅ ይፋ ባደረገው ጥናቱ ያስታወቀው፡፡

በቂ እንቅልፍ አለመተኛት የደም ቧንቧዎች ጥበትን እና መደንደንን ያስከትላል ያለው ጥናት ይህም ለልብ ሕመም እና ስትሮክ ዋነኛ ምክንያት ይሆናሉ ብሏል፡፡

በጥናቱ ከ4 ሺህ በላይ የባንክ ቤት ሠራተኞች የእንቅልፍ እና የጤና ሁኔታ የተመረመሩ እና ሁሉም ተሳታፊዎች ከዚህ ቀደም የልብ ሕመም የሌለባቸው መሆኑ ተረጋግጦ ነው ወደ ጥናቱ የገቡት፡፡

ተሳታፊዎቹ ወደ እንቅልፍ የሚሄዱበት፣ ሌሊት የሚነቁበት እና ጠዋት የሚነሱበት ሰዓት ተሰልቷል፡፡ በዚህም በቀን ከስድስት ሰዓታት በታች የሚተኙ ተሳታፊዎች ለልብ ሕመም እና ስትሮክ ተጋላጭ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

የእንቅልፍ ሰዓትን ማስተካከል እና በቂ እንቅልፍ መተኛት በልብ ሕመም ከተያዙ በኋላ ከሚደረገው ከባድ ሕክምና እና ወጪ እንደሚያድንም ጥናቱ አስረድቷል፡፡

የአልኮል መጠጥ እና እንደ ቡና ያሉ አነቃቂነት ያላቸውን መጠጦች አብዝቶ መውሰድ ለእንቅልፍ ማጣት እንደሚያጋልጥም ተመራማሪዎች አስረድተዋል፡፡

እንቅልፍ ‹ሜላቶኒን› እና ‹አዲኖሲን› በተሰኙ የአንጎል ንጥረ ነገሮች አማካኝነት እንደሚከሰትና በቂ እንቅልፍ መተኛት አንጎላችን እና አካላችን ያለድካም ሥራቸውን እንዲሠሩ እንደሚያደርግ በጥናቱ ተገልጿል፡፡ (ምንጭ፡-ናይን ኮች.ኮም)