የአየር ብክለት በ2019 በዓለም ዋነኛው የጤና ስጋት መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

የአየር ብክለት እአአ በ2019 የዓለማችን ዋነኛው የጤና ስጋት መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡

ከዓለማችን አጠቃላይ ህዝብ ከ10 ሰዎች ዘጠኙ የተበከለ አየር የሚተነፍሱ ሲሆን በአየር ብክለት ምክንያት በየዓመቱ 7 ሚሊዮን ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡

እንደ ካንሰርና ስትሮክ ላሉ የመተንፈሻ አካላትና የልብ ህመሞች የሚያጋልጠው የአየር ብክለት ችግር በስፋት የሚታየው በታዳጊ አገራት ነው፡፡

ዘንድሮ ዓለማችን የተጋረጡባትን በርካታ የጤና ፈተናዎች ለመመከት የዓለም የጤና ድርጅት ለ5 ዓመታት የሚያገለግል አዲስ የጤና ስትራቴጂ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

አዲሱ የጤና ስትራቴጂ በዓለም ዙሪያ 3 ቢሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የጤና ሽፋን እንዲያገኙ፣ ከአጣዳፊ የጤና ችግሮች እንዲጠበቁ እና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ እንዲከተሉ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል ተብሏል፡፡ 

የዓለም የጤና ድርጅት ለዓለም ዋነኛ ፈተናዎች ናቸው ያላቸውን 10 የጤና ጠንቆች በመለየት ይፋ አድርጓል፡፡

ከአየር ንብረት ለውጥ እና ከአየር ብክለት በመቀጠል በርካቶችን ለህልፈት የሚያበቁት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መሆናቸውን የጤና ድርጅቱ መረጃ ያሳያል፡፡ 

እንደ ስኳር ህመም፣ ካንሰር እና የልብ ህመም ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በዓለማችን ለሚከሰተው ከ70 በመቶ በላይ ወይንም ከ41 ሚሊዮን በላይ ሞት ምክንያት መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ሌላው ዓለማችንን በ2019 ያስጨንቃታል የተባለው የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ሲሆን መቼና የት ሊከሰት ይችላል የሚለው አለመታወቁ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ ፈታኝ ያደርገዋል፡፡

የዓለማችን 22 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የሚኖረው ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች በመሆኑ ለአስከፊ ድህነት፣ ረሀብ እና ስደት እንደሚጋለጥና በነዚህ አካባቢዎች ባለው ያልተረጋጋ ሁኔታ ምክንያት ደግሞ አፋጣኝ የጤና አገልግሎት ለማቅረብ አዳጋች መሆኑ ተገልጿል፡፡

መድሃኒት የተላመዱ ባክቴሪያዎችና ቫይረሶች፣ የኢቦላ ወረርሽኝ፣ ኤች አይቪ ኤድስ እና የክትባቶች አለመዳረስ ዘንድሮ ከተጋረጡብን የጤና ስጋቶች ውስጥ ተካተዋል፡፡ (ምንጭ፡- የዓለም የጤና ድርጅት)