እኔንስ የፈጀኝ…

ጥበቡ ታዬ

ከሁለት ሳምንታት በፊት 16ኛው የኤች.አይ./ኤድስና የአባለዘር በሽታዎች በአፍሪካ (ኢካሳ) ዓለም አቀፍ ጉባዔ በኢትዮጵያ መካሄዱ ይታወሳል፡፡ በየዓመቱ የኤች.አይ./ኤድስ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአመቱ በተመረጠ መሪ ቃል ላይ በመንተራስ ተከብሮ ይውላል፡፡ የዘንድሮው መሪ ቃልም ‹‹አንድም ሰው በኤች.አይ.. እንዳይያዝ ኃላፊነታችንን እንወጣ›› የሚል ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ያለምክንያት አይደለም፤ያለውጤትም አይደለም፡፡ ባጠቃላይአልን፣ አደረግንለማለትም አይደለም፡፡ አንድ አቢይ ዓላማን መነሻ በማድረግና ቀጣይ ስኬትን ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ በየዓመቱ ለምናደርገው ለዚህ ዝክርት ምክንያቱ 25 ዓመታት ገደማ ጀምሮ የሰውን ልጅ መፈታተን የጀመረ አንድ አደገኛ ክስተት በመኖሩ ነው፡፡ እስቲ ላንዳፍታ በጽሁፌ ጀልባ ላይ ተሳፍረንና የትዝታ ቱባ እየተረተርን 25 ዓመታት በላይ የጊዜ ርዝመት ያለውን የታሪክ ውቅያኖስ አብረን እንቅዘፍ፡፡ በዚህች የሦስትና የአራት ደቂቃዎች ገሃዳዊ ዕድሜ ባላት ጽሁፍ 25 የትዝታ ዓመታት ውስጥ በሃሳብ እንመላለሳለን፡፡ መቅዘፍ እንጀምር፡፡

ሸንጎ ከማይዳኘው ከሳት ያጣላናል

እኛ እንጭረዋለን እሱ ይፈጀናል፣

እየቆሰቆስን ፈጀን ተቀጣጥሎ

መላ መላ መላ ቶሎ!

በማለት በሀዘንና በረዳት አልባነት ያንጎራጎርነው መቼ ነበረ?! አዎ፣ የዛሬ 25 ዓመታት በፊት ጀምሮ፡፡ ምሱ የሰው ሥጋና ደም የሆነው፣ ደርሶ የሰው ዘር ለምን ባይኔ አይቼ በሚል ሰው እየነጠለ ማሳደድ የጀመረ ጸረ ሰው አደጋ በሰው ዘር ላይ የተነሳበትና በስፋት እየተስፋፋ የመጣበት ዘመን፡፡ ያ ክፉ ዘመን፣ ጊዜ ሰጠውና እኛም ቀድመን ሳንነቃና ሳንዘጋጅበት የሰውን ልጅ ጾታ፤ዘር፤ሃይማኖት፤እድሜ፤ቦታ ሳይለይ እያረደ በላ፡፡ አፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና፣ የወገን ያለህ እያሉ ወገን ሳይደርስላቸው፣ የሰው ያለህ እያሉ ድምጻቸው ሰሚ አጥቶና ችግራቸውም ለመፍትሄ እርቆ እንደ በረሃ አሸዋ፣ በሚቀዝፈው አየር ውስጥ እነዲሁ ተበትኖ የቀረውን የዚህ የሰው ዘር ሁሉ ጸር የሆነ አሳዛኝ ክስተት ሰለባ የሆኑትን ወገኖቻችንን 25 ዓመታት የቁጭት ታሪክ ይዘክራቸው፡፡

ያኔህሙማን የጸረ ኤች አይ ቪ/ኤድሰ መድሃኒት ባልተገኘበት ዘመን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩቱ ህይወታቸው እንደ ደረቀ ቅጠል ረገፈ፡፡ እንደ ዋዛ ከጎናችን እብስ ሲሉ ከንፈር ከመምጠጥና እንባ ከማፍሰስ ያለፈ ነገር ልናደርግላቸው አልቻልንም ነበርበምን አቅማችን፡፡

እነኚህ ወገኖቻችን የረገፉት እኮ ብቻቸውን አልነበረም፤ እውቀታቸው፣ ጉልበታቸውና ሃብታቸው ሁሉ ነው አፈር የበላው፡፡ ዛሬ በህይወት ኖረው ቢሆን ኖሮ ብላችሁ አስቡ እስቲ! ዛሬ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ ምናልባትም እኮ ዛሬ ባለው የዓለም ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ፣ሰላም፣ በኪነ ጥበብናሌሎች ዘርፎች ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማበርከትለውጡ አካል ይሆኑ ነበር፡፡ ይህንንም እዚህ ላይ ገታ እናድርገውና እሺ፣ ምናልባትም ቤተሰብ ሳያፈሩና የትውልድ መስመራቸውን ሳያስቀጥሉና ትውልዳዊ አሻራቸውን ሳይተው የተለዩንም እንዳሉ አትዘንጉ፡፡ በህይወት ኖረው ልጆችና የልጅ ልጆች፣ አፍርተው ቢሆን ኖሮ ከመሃላቸው ምናልባትም የዓለማችንን ታሪክ የሚለውጡ የሃገር መሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣  በተለያዩ ዘርፎች እውቅ ባለሙያዎች፤ ሳይንቲስቶች፤አትሌቶች ወዘተ ሊሆኑ የሚችሉ ትውልድ ተረካቢ ዜጎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ማሰብ ይቻላል፡፡ እኔ እንደዚህ አሰብኩ እንግዲህ፡፡ ብቻ በነሱ ሞት አሁንም ድረስ ዓለማችን ምን ያህል ጉልበት፣ ምን ያህል ኃይል እንዳጣችና እያጣች እንደሆነች፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ በሽታውን ለመቋቋምና ለመከላከል ምን ያህል ገንዘብ፤ ሪሶርስና ጊዜ እንደባከነና ምናልባትም ላልተወሰነ ቀጣይ ጊዜም ሊያስከፍል የሚችለውን ከፍተኛ ዋጋ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ ከሁሉም በላይ መተኪያ የሌለው የሰው ልጆች ሞት አሳዛኝና አስከፊ ውጤት ያለው ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ክስተት ሳቢያ ወላጆቻቸውን በማጣታቸው ለከፍተኛ ችግርና ጉስቁልና የተዳረጉ ወላጅ አልባ ህጻናትን፤ጧሪ ቀባሪ ያጡ አቅመ ደካሞችን ስናስብ ደግሞ የችግሩ ግዝፈት በአይነ ህሊናችን ፍንትው ብሎ ይታየናል፤ እኔስ ብሆን ኖሮ ብሎ ቆም ብሎ በጽሞና ማሰብ፤ደግሞ ደጋግሞ ማሰብ፡፡ ዛሬስ ከዚህ አስከፊ ሁኔታ ምን ያህል ተላቀናል? የወደፊት ተስፋችንስ ምን ይመስላል?

ዛሬማ ከሰማይ በላይ ውዳሴ ለፈጣሪ፣ ከሰማይ በታች ዕድሜ ለሳይንስ ይሁንና ጩኸታችን ተሰምቶ ጉድ መላ ተገኘለት፡፡ ከቫይረሱ ጋር እየኖርንም ቢሆን መኖር ቻልን፣ መሥራት ቻልን፡፡ ዛሬ ቫይረሱ ጨርሶ ባይጠፋም ተጽእኖውና ስርጭቱ በእጅጉ ቀንሷል፡፡ ዛሬ ግን ከራሱ ከበሽታው ይልቅ ይበልጥ እያሸማቀቀንና እያሳሰበን ያለው ሌላ ነው፡፡

እሳት ዘሎ አይዝም ካልደረሱበት

እሳት ፍም አይዝም ካልቆሰቆሱት

እኔንስ የፈጀኝ የሰው ግንባር ነው፣ እረ የሰው ፊት

ቀና ብዬ ላየው ልጠጋ ያልቻልኩት!

አሁን አሁን የምናንጎራጉረው እንዲህ እያልን ነው፡፡ ግን እስከመቼ? በርግጥ አሁን ባለው ሁኔታ ቀድሞ እንደነበረው ዓይነት መገለልና መድልኦ የለም ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ በእርግጥም የሰዎች ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳዬ በመምጣቱ በተወሰነ ደረጃ የቀነሰበት ሁኔታ ስለመኖሩ መመስከር ይቻላል፡፡ ሆኖም ጨርሶ ከሥሩ ተመንግሎ ወድቋል ማለት ግን አይቻልም፡፡ ማግለልና መድልኦ እንደ ቀድሞው እምብዛም ፊት ለፊት ገዝፎ ባይወጣም አልፎ አልፎ ጓዳ ጓዳውን ግን እንደ አይጥ መሹልክለኩን አልተወም፡፡ የዘንድሮው የዓለም የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቀን መሪ ቃል ‹‹አንድም ሰው በኤች.አይ. እንዳይያዝ ኃላፊነታችንን እንወጣ!›› የሚል ነው ብለናል፡፡ መገለልና መድልኦ ባለበትና ድብብቆሹ ፈጽሞ ባልቀረበት ሁኔታ ይህን በማለታችን ብቻ ግን የሚሳካ ይመስላችኋል? ጎበዝ ተግባራችን ከቃላችን በላይ ባይሆን የቃላችንን ያህል፣ የቃላችንን ያህል ባይሆን እኩሌታውን ያህል መናገር ቢችል በርግጥ ቃላችን ነፍስ ይዘራል፣ ያለጥርጥር!

በያመቱ የኤች.አይ./ኤድስ ቀንን ስንዘክር ተሰብስበን በየመድረኩ ላይ  በቃላት ብቻ ምለንና ተገዝተን ለመለያየት ሳይሆን የተማማርነውን በልባችን ይዘን ወደ ተግባር ለመመንዘር ይሁን፡፡ በሚቀጥለው የስንኝ ቋጠሮ እንለያይ፣

የሌሊቱ ውድቅት ጨለማው ካልዋጠው

የፀሀይ ንዳዱ ከማይለበልበው

ፍጹም ሰላማዊ ከማይነዘንዘው

ከናትህ ማህፀን ከንቅልፍህ ስትነቃ

ማነው ያስተማረህ የዚህን ዓለም ቋንቋ፣

ማነው የነገረህ የዚህን ዓለም ነገር

ያላጋዥ እርዳታ በራስህ አልነበር?!

አፍህንብለህ መክፈት ስትጀምር

የለቅሶአቡጊዳመማርህ አልነበር?

ያፍህን ጎዳና ጉሮሮህን ከፍቶ

የናትህን ጡትስ ማናሳየህ ከቶ?

እኮ ማን በል አለህእማማአባባ

እንዲህ ያለውን ቃል ሆድን የሚያባባ?

እና ወዳጄ ሆይ ይህንን ካወቅህ

ሳታዳላ መኖር፣ ሳታገልስ መኖር እንደምን ሊሳንህ

ተሳስቦ መኖርስ ከቶ እንዴት ሊያቅትህ?!

ጥበቡ ታዬ (ዊዝደም)

ከመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ህዝብ ግንኝነትና ኮሙኒኬሽን