የእቅዱ ትሩፋቶች

ዮናስ ገረመው

ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ያሳየችው የኢኮኖሚ እድገት በፍጥነቱ ከአፍሪካ የተለየና በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ስለመሆኑ በርካታ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችና ተቋማቶች ያረጋገጡት እውነታ ነው። የአለም የገንዘብ ድርጅት የኢኮኖሚ እደገትን በተመለከተ ባወጣው የ2010-2015 መረጃ ላይ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከቻይናና ህንድ ቀጥላ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ሃገራችን በአማካይ የ11 በመቶ እደገት በየአመቱ በማስመዝገብ ባለ ሁለት   አሀዝ ሃገራዊ የኢኮኖሚ እደገት ማምጣቷ የመንገስትን ፖሊሲና ስትራቴጂ ትክክለኛነት የሚያመላክት እንደሆነም ብዙዎቹ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የሚስማሙበት እንደሆነም የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በሪፖርቱ ጨምሮ አስፍሯል።

የመንግስት የልማት ፖሊሲ ገና ከመነሻው ሲቀረጽ በመላው አገራችን በሁሉም አይነት ዘርፍ እድገት በማስመዝገብ የኢኮኖሚ እደገቱን ያለማቋረጥ ማረጋገጥ እንዲያስችል ሆኖ  ስለመሆኑም የተለያዩ የመንግስት መረጃዎች ያመለክታሉ።

PASDEP (The plan on accelerated and Sustained Development to end Poverty) ፈጣንና ቀጣይነት ባለው ልማት ድህነትን የማስወገድ እቅድ 2002/3-2004/5 በኢትዮጵያ አቆጣጣር የወጣበት ወቅት ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እደገት ማስመዝገብ እንደሚቻል  የተረጋገጠበት ወቅት  ነው።

ይህ ቀጣይነት ያለውና ፈጣን የሆነው የልማት ዕቅድ በዋናነት ለመሰረተ ልማት ግንባታና ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ልዩ ትኩረት የሰጠ  ሲሆን፤ከ2003-2007 ዓ.ም ተፈፃሚ የሚሆነው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድም ልክ እንደቀደመው የመሰረተ ልማትና የኢንዱስትሪው ዘርፍ ቁልፍ ተግባራቶች ይሆናሉ የሚል ግብ ተቀምጧል።

ለሃገራችን ፈጣን የሆነ ልማትና የኢኮኖሚ እደገት ከኢንዱስትሪና መሰረተ ልማት ግንባታዎች ሁሉ በዋናነትና በተለየ መልኩ ቦታ የሚሰጣቸውና ለኢኮኖሚ እድገቱ አስተዋፅኦቸው የማይተካው ደግሞ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግንባታዎችና የስኳር ኢንዱስትሪ የግንባታ ዘርፎች እንደሆኑም በእቅዱ ነጥሮ ተቀምጧል። በዚሁ መሰረትም ከኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግንባታዎች በመነሳት ዋና ዋና የተባሉትን የኢንዱስትሪና የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎችን  ለመቃኘት እሞክራለሁ።

ለሃገራዊ ኢኮኖሚ ልማት ቀጣይነትና ዘላቂነት የሃይል ማመንጫ ግንባታ ስራዎች ድርሻ ከሁሉም የላቀ መሆኑን በመገንዘብ መንግስት ለዘርፉ የተለየ ትኩረት  መስጠቱ መጀመሪያ ሊያስመሰግነው ይገባል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት በተገኘው ተከታታይነት ያለው እደገት የሃይል ፍላጎትና አቅርቦት ልዩነት ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ መምጣቱ ለዘርፉ የተለየ ትኩረት ለምን ተሰጠ ለሚሉት  ሌላው ተጨማሪ ምላሽ  ይመስለኛል። ስለሆነም ነው ለዘርፉ የበርካታ ቢሊዮን ኢንቨስትመንት ወጪ በመሆን ላይ የሚገኘው።

እነዚህን ግዙፍ የሃይል ማመንጫ ግንባታዎች ማከናወን እንደሚቻል ደግሞ በጣና በለስ፤ ተከዜና ጊቤ II ማረጋገጥ ተችሏል። በቂ ልምድም ተወስዷል፤ አቅምም ተገንብቷል። በዚህም 714 ሜጋ ዋት ብቻ የነበረውን የሃይል ምንጭ በድህነት ቅነሳ ፕሮግራሙ የመጨረሻ ወቅት ላይ 2000 ሜጋ ዋት ማድረስ ተችሏል። ይህ ደግሞ በትራንስፎርሜሽን እቅዱ ለተያዙ የሃይል ማመንጫ ግንባታዎች ዕቅድ ከፍተኛ ግብዓትና አቅም መሆን የሚችል አፈፃፀም ነው።

በዚህ የተነሳ የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ የነበሩ 648 የገጠር ቀበሌዎችን ወደ 5,163 ማድረስ ሲቻል የደንበኞች ቁጥር ደግሞ ከ952 ሺህ ወደ 2 ሚሊዮን ከፍ ብሏል። በ2004-05 እ.ኤ.አ እሰከ 2009/10 በተያዘው የድህነት ቅነሳ ፕሮግራም 3,380 ኪሎ ሜትር ብቻ የነበረውን የሃይል ማስተላለፊያ መስመር በእቅዱ መጨረሻ ወደ 14,792 ኪ.ሜ ማድረስ የተቻለ ሲሆን በ5 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተሰራውን(13,147 ኪ.ሜ) ብቻ ልብ ቢሉ ምን ያህል መስራት እንደሚቻል የተረጋገጠበት ዘመን ነው ብሎ መውሰድ የሚያስችልና ለቀጣዩ ጉዞም ስንቅ እንደሚሆን መገንዘብ የሚያስችል ነው።

በሰብ ስቴሽን በኩል ያለውን ተሞክሮ ስናይ 2004/5 25 ሺህ ኪ/ሜ የነበረውን በ126 ሺህ38 ወይም 91 በመቶ በማሳደግ 2009/10 ላይ 136 ሽህ 320 ኪ.ሜ ማድረስ  መቻሉም ሌላው የእቅዱ ስንቅ ነው።  ይህ ብቻም አይደለም፤ እነዚህ የሃይል ማመንጫ ግንባታ ስራዎች ሲሰሩ ከ26,176 ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ የሚገኝ የደን ጥበቃ ስራ የተከናወነ ሲሆን፤ የተፈጥሮ ሃይል ክምችትም ጎን ለጎን ተሰርቷል። በዚህ የተፈጥሮ ሃይል 238 የገጠር ጤና ጣቢያዎችና ከ10 ሺህ  በላይ አባወራዎች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ  መሆን ችለዋል። የተከማቸ የፔትሮሊየም አቅማችንም ከ279,800ኪዩቢክ ሜትር ወደ 369,800 ኪዩቢክ ሜትር የደረሰው በዚሁ በድህነት ቅነሳ ፕሮግራሙ ዘመን ከ2004/05-2009/10 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።

እስካሁን የጠቀስኩት እንግዲህ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ዋና አካል ስለሆነው የሃይል ማመንጫ ግነባታ መነሻ ሁኔታዎችና የዕቅዱን ስኬት ለሚጠራጠሩ ወገኖች የነበረውን ተሞክሮ ለማሳየት ያህል ነው። በዚሁ መነሻነት ወደ እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ  ሳመራ አሁንም የምነሳው ከኤሌክትሪክ ሃይል ልማት ነው።

በ2003 ዓ.ም የሚጀምረው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማብቂያ 2007 በኢትዮጵያ አቆጣጠር ነው። አሁን ያለንን ሃይል በ2007 ላይ  በሁለት እጥፍ ለማሳደግና 10 ሺህ ሜጋ ዋት ለማድረስ ሲታቀድ ቀደም ብዬ የጠቀስኩት ተሞክሮ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያ 45,000 ሜጋ ዋት ሃይል ማመንጨት የሚያስችል ዕምቅ ሃብት ያላት መሆኑም አብሮ ሊጤንና ልብ ሊባል የሚገባ መሆኑን መጀመሪያ መጥቀስ ያስፈልጋል።

ዕቅዱ ሃይልን ለመቆጣጠርና በተመጣጣኝ ዋጋ ህዝቡ መጠቀም የሚችልበትን ሁኔታ ከግምት ውሰጥ በመክተት የተዘጋጀ ሲሆን ለዚህም የንፋስና የከሰል ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታዎች ታሳቢ ተደርገዋል። በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የተያዘውን የሃይል ማመንጫ ግንበታ መነሻ በተመለከተ ይህን ያህል ካነሳን ዘንዳ ዋና ግቡንና 2007 ላይ የሚጠበቁትን  ዋና ዋና ነጥቦች ባጭሩ መቃኘት ዝርዝሩን ለመረዳትና የልማቱ አካል ለመሆን ይጠቅመናልና የሃይል ማመንጫ ግንባታዎቻችን ትሩፋቶችን በጥቂቱ መመልከት ጠቃሚ ይሆናል።

የመጀመሪያውና መሰረታዊው ጉዳይ 2000 ሜጋ ዋት የነበረውን የሃይል አቅም ወደ 10,ሺህ ሜጋ ዋት በማሳደግ የያንዳንዱን ቤተሰብ የሃይል ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ማሟላት ነው። የሃይል አቅርቦት ያልነበራቸውን የገጠር መንደሮች ማዳረስ ደግሞ ቀጣዩና በፕሮግራሙ የተካተተ ጉዳይ ነው። የሃይል ብክነትን በማስወገድ በፍላጎትና አቅርቦት መሃከል የነበረውን ሰፊ ክፍተት መሙላት ሶስተኛው መሰረታዊ ነጥብ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ በዋናነት የሃገር ውስጥ ፍጆታን በተሟላ መልኩ ለማሳካት የሚያስችል ስትራቴጂ ነው።

ከሃገር ውስጥ ፍጆታ በኋላ በመቀጠል የሚመጣውና በዕቅዱ ውስጥ የተካተተው የሃይል ማመንጫ ግንባታ ለሽያጭ የሚውለውና የውጭ ምንዛሪን ለማስገኘት የሚረዳው የሃይል ዘርፍ ነው።  እነዚህ እንግዲህ ግንባታውን ብቻ የተመለከቱ ጉዳዮች ናቸው። በዚሁ የትራንስፎርሜሽን ዘመን ከሃይል ማመንጫ ግንባታዎች ጎን ለጎን ወጪ  የሚቆጥቡና በብቃት ሃይል ማስተላለፍ የሚቸሉ የማስተላለፊያ መስመር  ተከላዎችም አብረው የሚከናወኑ ይሆናል። እነዚህ የማስተላለፊያ መስመሮች ከሁሉም ብሄራዊ የሃይል ማከማቻ ጣቢያዎች ጋር የሚገናኙ መሆናቸው ደግሞ ዘመናዊነታቸውን ያጎለዋል።  ይህ ደግሞ የሀይል  ስርጭቱን አገልግሎት የሚያሳድገው ሲሆን፤ የሃይል ብክነትንና ወጪንም በከፍተኛ ሁኔታ ይቆጥባል፡፡ ይህ አይነቱ አሰራር የሃይል ፍላጎትን በበቂና በተማላ ሁኔታ ማዳረስ ከማስቻሉም በላይ ለደንበኞቸ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠትም  ያገለግላል። የሃይል መቆራረጥ ባጋጠመ ጊዜም በጅምላ መብራት የሚቋረጥበትን ሁኔታ በማስቀረት ችግር በተፈጠረበት አካባቢ ላይ ብቻ ኃይል በማቋረጥ በውስን ሰዓታት ውስጥ ማስተካከል የሚቻልበትን እድልም የሚፈጥር አዲስ ቴክኖሎጂ ነው።

በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ዘመን ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በአግባቡና በተባለው ጊዜ ማከናወን እንዲቻልም የተቀመጠ የማስፈፀሚያ አቅጣጫ አለ። የታዳሽ ሃይሎች ልማት፣ የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ እንዲሁም ብቃትና አቅም ያለው የሃይል አስተዳደር ስርዓት መዘርጋትና አቅም መገንባት  ዋነኞቹ አቅጣጫዎች  ናቸው፡፡ ከአረንጓዴ ልማትና አየር ብክለት ጋር በተያያዘም የሃይል ማመንጫ ግንባታዎቹ በውሃም ሆነ ከሌሎች የታዳሽ ሀይል ማመንጫ ግንባታዎች የምናመንጨው ሃይል ከሃገሪቱ አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ጋር ተጣጥሞ የተቀረፀና በራሱም ታዳሽ ሃይል መሆኑ ስጋት  አለን ለሚሉት ሀይሎች የሀሳባቸውን ምክንያት አልባነት የሚያሳይ ነው። የካርበን ልቀትን የሚያስወግዱ የሃይል ማመንጫ ንዑሣን ዘርፎች በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ታግዘው  እየተቋቋሙ መሆናቸውም ሌላው የዚህ ዘርፍ ፋይዳ ነው፡፡

በሌላ በኩል የነዳጅ ማጠራቀሚያና ማሠራጫ ታንከሮችንና ተያያዥነት ያላቸውን ቴክኖሎጂዎችን በመላው ሃገሪቱ መጠቀም የሚያስችል አሠራር የተዘገረጋ ሲሆን በተለይም የገጠሩ ክፍል በራሱ አቅምና እውቀት ማከናወን የሚያስችለውን የሃይል አማራጭም የሚሰጥ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከሃይል ፍላጐትና አቅርቦት ጋር የተያያዘውን ችግር በዘላቂነት ለማስወገድ የተያዘውን  አቅጣጫና እስካሁን የተገኘውን ትሩፋት በተመለከተ ይህን ያህል ካነሣን አሁን ደግሞ የሃይል ማመንጫ ግንባታ ሥራዎችን ጅማሬዎችና ሂደቱን የተመለከቱ ዝርዝር ነጥቦችን  እናንሳ ፤ መነሻችን የሚሆነውና ምናልባትም  አንባቢያንም እንዲሆን የምትጠብቁት ደግሞ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁና ወደዚሁ እናምራ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፡-

የአባይ ወንዝን መሠረት አድርጐ  ግንባታው የተጀመረውና ከምስራቅ ሱዳን 4ዐ ኪ.ሜ ከአዲስ አበባ ደግሞ 75ዐ ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ አሁን በቅርቡ በተገኘ መረጃ መሰረት 75 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የሚይዝ ሲሆን፤ ባጠቃላይ 168ዐ ኪሜ ስኪዌር ቦታን ይሸፍናል፡፡ እያንዳንዳቸው 35ዐ ሜጋ ዋት የሚያመነጩ 15 ተርባይኖች ያሉት ሲሆን፤ ይህም  በአጠቃላይ 525ዐ ሜጋዋት የማመንጨት ብቃት ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡ 4.8 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጀው ይህ ግድብ ወጪው የሚሸፈነው በህዝብና በመንግሥት ሲሆን፤በዚህ ረገድም ከህዝቡ የጋ ምላሽ የተገኘበት ሁኔታ ከመፈጠሩም በላይ ለሌሎችም የልማት ሥራዎች ትልቅ መነቃቃት ፈጥሯል፡፡

ግንባታው በሠዓት 15 ሽህ 128 ጌጋዋት ሃይል ማመንጨት እንዲችል ታስቦ ዲዛይን የተደረገ ሲሆን፤ በዓመት 15.1 ቢሊዮን ኪሎ ዋት ማለት ነው፡፡ ይህን በያንዳንዱ አባወራ ስናሠላው ደግሞ ባለ 6ዐ ሻማ ለ8 ሠዓታት 86 ሚሊዮን አምፖሎችን በቀን ማብራት  ያስችላል ማለት ነው፡፡ እንደባለሙያዎች ግምት ደግሞ መካከለኛ አቅም ያላቸውን 6 የኒውክለር ሃይል ማመንጫዎች ያክላል፡፡

ግንባታው የአካባቢ ብክለትን በከፍተኛ ሁኔታ ከመቀነሱም ባሻገር ወደ ግብጽና ሱዳን ይገባ የነበረውን ጨዋማ ውሃ በማስቀረት ተያያዥነት ያለው ጥቅም ይሰጣል፡፡ በተለይም በደለል ለሚሞላው የሱዳኑ ፎሠሪስ ግድብ ፍቱን መድሃኒት ነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፡-

የህዳሴው ግድብ ትሩፋት ይህ ብቻ አይደለም፤ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በወንዙ ዳርቻና አካባቢው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም  ሱዳናውያንን ከጐርፍ አደጋ የሚታዳጋቸው ሲሆን በቋሚነት የሚኖሩበትን ዋስትናም ማረጋገጥ የሚችሉት በዚሁ ግድብ ብቻ ነው፡፡ ሌላው የህዳሴው ግድብ ተስፋ በትነት የሚባክነውን ውሃ በማስቀረት የተፋሰሱ ሃገሮችን ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነትን መብት ማረጋገጥ መቻሉ ነው፡፡ ግብጽና ሱዳን በተመጣጣኝ ዋጋ የሃይል ፍላጐታቸውን መጨመር የሚችሉበትን  እድል የሚፈጥር መሆኑም ሌላኛው ጥቅም ነው፡፡

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ጠባብ በሆኑ ሸለቆዎቹ የሚከማቸውና ወደ 7.5 ቢሊዮን ብዩቢክ ሜትር የሚደርሰው ውሃ በትነት  ሲባክን የቆየ ሲሆን አሁን የህዳሴው ግድብ   በግብጽና ሱዳን የሚገኙ ግድቦችን ህይወት ያራዝማል ይላሉ ጥናቶቹ፡፡ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጐጂ ሳይሆኑ ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆናቸውንም በየደረጃው የተደረጉ  የግንባታው ጥናቶች በግልጽ የሚያመለክቱ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

በዚሁ መሠረት የግንባታ ፍጥነቱን በተያዘለት እቅድ መሰረት ጠብቆ በመጓዝ ላይ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከ44 ወራት በኋላ በ2 ተርባይኖች 7ዐዐ ሜጋዋት ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡ ከ72 ወራት በኋላ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ 525ዐ ሜጋ ዋት  በማመንጨት የሃገራችንን የሃይል አቅም  በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምርልናል ተብሎ ታላቅ ተስፋ ተጥሎበታል። ከእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ አኳያ ግዙፉን የውሃ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ በተወሰነ ደረጃ ለመቃኘት ሞክረናል፡፡ አሁን ደግሞ  ጉዟችንን ወደ ግልገል ጊቤ ሶስት እናድርግ፡፡

ግልገል ጊቤ ሶስት፡-

የግንቦታ ሥራው የተጀመረው በፌብሩዋሪ 2ዐ11 ላይ ነው፡፡ አሁን ባለበት ደረጃ ወደ 42 ከመቶ የሚሆነው ሥራ ተጠናቋል፡፡ በኦሞ ወንዝ ላይ የሚገነባው ይህ የሃይል ማመንጫ ጣቢያ የጊቤ አንድ ሁለትና  የቀጣዮቹ   አራትና አምስት ግንባታ አካል ሆኖ የሚከናወን  ነው፡፡ የማመንጫ ጣቢያው ግንባታ እንዲያመነጭ የሚጠበቀው ሜጋዋት የጊቤ አንድን ሁለትንና 1472 ሜጋዋት የሚያመነጨውን ጊቤ አራትን እንዲሁም 56ዐ ሜጋዋት እንዲያመነጭ የሚታሰበውን ቀጣዩን ጊቤ አምስት ታሳቢ ያደረገ የውሃ ፍሠትና የአካባቢ ሁኔታ ከግምት ያስገባ ግንባታ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን መረጃ መሠረት የግድቡ ግራና ቀኝ ክንፍ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን የሃይል ቤት / power house/  ግንባታውም 87 በመቶ ተጠናቋል፡፡ የውሃው መግቢያ /power intake/ 77 በመቶ፣ የውሃ ማስተላለፊያው ዋሻ/power tunnels/ ደግሞ 82 በመቶ ተሰርቶ አልቋል።ይህ የሃይል ማመንጫ 2013 እ.ኤ.አ ተጠናቆ ስራ አንዲጀምር የሚጠበቅ ሲሆን አያያዙ ደግሞ በተባለው ጊዜና በተቀመጠለት እቅድ መሰረት መጠናቀቅ እንደሚችል ይገመታል።

የግድቡን መዋቅራዊ ሁኔታ ስንመለከት 243 ሜትር ከፍታ ባለው ኮንክሪት የተሞላና በ210 ስኩየር ኪሎ ሜትር ሜዳ ላይ የተቆፈረ 14 ኪዩቢክ ኪሎ ሜትር ውሃ መያዝ የሚችል የማጠራቀሚያ ገንዳ ያለው ነው። በማከማቻ ገንዳው ውስጥ ከሚገኘው ውሃ 11.75 ኪዩቢክ ኪሎ ሜትር የሚሆነው ሁሌም ስራ ላይ የሚውል ሲሆን 2.85 ኪዩቢክ ኪሎ ሜትር ያህሉ ስራ ላይ አይውልም። ሃይል የማመንጨት አቅሙንም ስናይ እሰካሁን ከተገነቡት ከፍተኛና እየተገነቡ ከሚገኙት ደግሞ ከህዳሴው ግድብ ዝቅ ብሎ በ10 ተርባይኖች 1 ሽህ 870 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ይኖረዋል።

አሁን ደግሞ ወደንፋስና መሰል የሃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታዎች እንሻገር።

አሸጎዳ የነፋስ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታ

አሸጎዳ የነፋስ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታ የሚጠናቀቀው እኤአ በጁላይ 2012 ሲሆን ከ50 በመቶ በላይ ግንባታው ተጠናቋል። መገኛ ቦታውም በትግራይ   ብሄራዊ ክልል መቀሌ መግቢያ አሸጎዳ በተባለ ስፍራ ነው። ይህ ማመንጫ ጣቢያ 210 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን 120 ሜጋዋት ሃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ከነፋስ የሚገኝ የሃይል ግንባታን ቀደም ብላ በአዳማ አይሻና ደብረብርሃን የተለማመደች ሲሆን በተያያዥነት በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎችንና ኢንቨስትመንቱን 70 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏታል። የነዚህ የነፋስ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታዎች ደግሞ የአምስት አመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አካላት ናቸው። በድምሩ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ወጪ የሚሆንባቸው ተመሳሳይ የነፋስ ሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በገባ ዙሪያ ሃለሌ ወራቤሳ፤ ቸሞጋ እና ገናሌ አካባቢም የሚገነቡ ይሆናል ።በቀጣዮቹ አምሰት አመታት አሁን በመገንባት ላይ የሚገኙት የነፋስና የውሃ ሃይል የማመንጫ ጣቢያ ግንባታዎች ሲጠናቀቁ  በነዚሁ አምስት አመታት ጊዜ ውስጥ አንድ የውሃ ሃይል ማመንጫ ጣቢያና ሌሎች የንፋስ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታዎች እንደሚጀመሩም ዕቅዱ ያመለክታል።

እነዚህ የሃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታዎች ሲጠናቀቁ ምሉዕ ሆነው አገልግሎት መስጠት የሚችሉት የሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች በተጓዳኝ ከተሰሩላቸው ብቻ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ሃቅና መሰረታዊ መሆኑ ቢታወቅምና ሊገርም ባይችልም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አሁን የሚሰሩት የሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እኩል በኩል ከሃይል ማመንጫ ግንባታዎቹ ጋር ነው። በአንድ ላይ ተጠናቀው ስራ መጀመር እንዲችሉ አንዱ ቀዳሚ አንዱ ተከታይ እንዳይሆን በቂ ዝግጅት ተደርጎበት ወደስራ የተገባ መሆኑን ነው ከኢትዮጵ,ያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የተገኙ መረጃዎች የሚያመለክቱት ።

የሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ግንባታ አዳዲስ ከሚገነቡትና ከተገነቡት የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ጋርና የሃይል መካመቻ ጣቢያዎች ጋር  በኔትወርክ እንዲገናኝ ሆኖ እየተገነባ ሲሆን፤ ለአብነት ያህል የጣና በለሱ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ ከሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ጋርና ከማእከል የኃይል ማጠራቀሚያ ጣቢያዎች ጋር  የማገናኘቱ ስራም  ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ከውጭ ስራ ተቋራጮች ጋር በገባው ውል መሰረት 2,424 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው  ባለ 23ዐ እና 132 ኪሎ ቮልት የመሸከም አቅም ያላቸውን የመሥመር ዝርጋታዎች በማከናወን ላይ ነው፡፡ ከነዚህ ሥራዎችም ነሼ፣ ፊንጫ፣ ጐዴ ገፈርሳ ተከዜ ሽሬ እንደስላሴ ሁመራን የሚያገናኘውን ባለ 23ዐ ኪሎ ቮልት መስመር ተዘርግቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ባለ 132 ኪሎ ቮልት የመስመር ዝርጋታ ግንባታው ደግሞ አላማጣ – ኮምቦልቻ ኮተቤ ቃሊቲ ሃይል ማስተላለፊያ ድረስ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ሃረር፣ ፊካንድ ነቀምት 298 የሃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታና ሌሎች አዳዲስ የመስመር ዝርጋታ ሥራዎችም 132 ኪሎ ቮልት የመሸከም አቅም ባላቸው ማስተላለፊያዎች እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡

ባጠቃላይ እስካሁን የተሠሩት ከፍተኛ የሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች በኪሎ ሜትር 1ዐ ሽህ 884 የደረሱ ሲሆን መካከለኛና ዝቅተኞቹ የማስተላለፊያ መሥመሮች ሲጨመሩ ደግሞ 126 ሽህ 3ዐ8 ኪሎ ሜትር ይደርሣሉ፡፡ በሌላም በኩል የዘርፉ መስፋፋት “ኤሌክትሪክ ለሁሉም” የሚለው የመንግስት መርህ እየተሣካ ያለበትን ሁኔታ በተጨባጭ እያመላከተ መምጣቱን መመስከር ይቻላል፡፡ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የመጀመሪያ አመት እንኳ ብናይ 678 አነስተኛ ከተሞችና የገጠር መንደሮች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

ይህን ሁኔታና አፈጻጸም ከተመለከትን ከሃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ   የሃይል ማመንጫ ግንባታው ስኬት እንደማያጠራጥር መገንዘብ ይቻለናል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም  የተሠሩት ሥራዎችና አፈጻጸሙ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የሃይል ማዕከል  መሆን እንደሚቻላትም የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ቀደም ብዬ እንደጠቃቀስኩት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከነዚህ ግዙፍ የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከቤት ውስጥ ፍጆታ ጀምሮ ወደ ኢንዱስትሪ ለምናደርገው ሽግግር የሚኖራቸው አስተዋጽኦ በዋናነት እንደተጠበቀ ሆኖ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን በሽያጭ ለጐረቤት ሃገሮች በማቅረብ በውጭ ምንዛሪ በኩልም ተጠቃሚ ለመሆን ግብ ተጥሎ ወደ እቅድ በመቀየር እየተሰራ ነው፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በዕቅዱ ዘመን የተካተቱት የሃይል ማመንጫ ግንባታዎች ተጠናቀው ሥራ ሲጀምሩ ጅቡቲ /አሁንም ጀምራለች/ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ግብጽ የዕቅዱ ትሩፋት ተቋዳሾች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡  እነዚህ ጐረቤት ሃገሮች የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ሃይል በሁለት ምክንያት ይፈልጉታል፡፡ ታዳሽ ሃይል በመሆኑ ከአየር ለውጥ ጋር  የተያያዘ ችግር አይኖረውም ይህ የመጀመሪያው ምክንያት ሲሆን፤ በዋጋ ደረጃም ዝቅተኛ ወይም ርካሽ በመሆኑ መጠቀማቸው አይቀሬ ይሆናል የሚለው ደግሞ ሁለተኛው ምክንያት ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ጅቡቲ አዲስ የሃይል አቅርቦት የሽያጭ ውል 35 ሜጋዋት በመሸጥ ኢትዮጵያ በወር የ1.5 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ታስገባለች፡፡ ይህ ደግሞ በአመት ሲሠላ ለኛ ትርጉሙ ብዙ እንደሆነ የሚያመለክት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ለአካባቢው አገሮች ሠላማዊና መረዳዳትን /መተጋገዝን/ መሠረት ላደረገ ግንኙነት የሚሰጠው ጠቀሜታም ሌላውና ከፍተኛው ዕድል ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን መረጃ ከሆነ ቀደም ብሎ በኬንያና በኢትዮጵያ መንግስታት በተደረሰ ስምምነት መሠረት የሃይል ማስተላለፊያ መሥመር ግንባታ /ኢትዮ – ኬንያ/ እየተገነባ ነው። በነዚህ አምስት አመታት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ 4ዐዐ ሜጋዋት ለኬንያ 2ዐዐ ሜጋ ዋት ደግሞ ለሱዳን ለማቅረብ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡