በህወሓት 40ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ዙሪያ እነማን ምን አሉ?

በሰለሞን ሽፈራው

(ክፍል ሁለት)

በዚሁ ርዕስ የቀረበውን ክፍል አንድ ፅሁፍ ያነበባችሁ እንደምታስታውሱት ባለፈው የካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም የተከበረውን የህወሓት 40ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተመለከተ አስተያየታቸውን ከሰጡን የበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አንዱን አቅርበናል። ዛሬ ደግሞ ከዲያስፖራው እንግዳችን ቀጥሎ ያነጋገርናቸውን አንድ አዛውንት አርሶ አደርና እንዲሁም በትጥቅ ትግሉ ዘመን ለከፋ የአካል ጉዳት ከተዳረጉ የድርጅቱ ታጋዮች መካከል ጥቂቶቹ የሰጡኝን አስተያየት ጠቅለል ባለ መልኩ ላስነብባችሁ።

አቶ ኪዱ ወ/ገሪማ በዓሉን ለማክበር ከማዕከላዊ ትግራይ ዞን የመጡ አዛውት አርሶ አደር ናቸው። ትዕበ የምትባል ሴት ልጃቸውን በትጥቅ ትግሉ ዘመን መርቀው እንደሸኙና ትዕበ ዳግመኛ ወደ ቤተሰቦቿ እንዳልተመለሰችም ነግረውናል አቶ ኪዱ። በግልፅ አነጋገር አዛውንቱ እንግዳችን ወጣት ሴት ልጃቸውን ዛሬ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለተጎናፀፉት ራስ በራስ የማስተዳደር ዲሞክራሲያዊ መብት መረጋገጥ ገብረዋል ማለት ነው።

አሁን አሁን በኢትዮጵያ እየመጣ ያለውን ፈርጀ ብዙ ለውጥ ሲያስቡ የልጃቸው መስዋዕትነት ፍሬ ማፍራቱን እንደሚገነዘቡ የገለፁልን አቶ ኪዱ ከሐዘን ይልቅ ኩራትና መፅናናት እንደሚሰማቸው ነግረውናል። ሁኔታውን ይበልጥ ግልፅ እንዲያደርጉልን ጠይቀናቸው ሲመለሱም አዛውንቱ አርሶ አደር “እንኳንስ እኔ አንድ ልጅ ብቻ ያጣሁት ሁለት ሦስት የተሰዋባቸው ወላጆችም አሁን ባለው ልማት ተፅናንተዋል! ደግሞስ ልጆቻችን ታግለው ደርግን ያህል የአፈና አገዛዝ ስላሰወገዱልን አይደል እንዴ ዛሬ እኛ እንደ ሰው በአደባባይ ተከብረን ለመታየት የበቃነው እንጂ በቀደሙት ስርዓተ መንግስታትማ እንደኔ ዓይነቱን ተራ አፈር ገፊ ማን ከሰው ይቆጥረው ነበር!!” ብለዋል።

ለድፍን 17 ዓመታት የተካሄውን ደም አፍሳሽ የትጥቅ ትግል በድል አድራጊነት ለመወጣት ይቻል ዘንድ በተለይም የትግራይ ሕዝብ ለማመን የሚያዳግት ፅናት የሚጠይቅ ፈርጀ ብዙ  መስዋዕትነት ለመክፈል መገደዱን ያስታወሱት አቶ ኪዱ፤ አሁን ያለው ትውልድም ከመሪ ድርጅቱ ህወሓት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ለሀገር ልማት መነሳትና መረባረብ ከቻለ ድህነትንም ልክ እንደ ደርግ ማሸነፍ አያዳግትም የሚል እምነት አላቸው።አዛውንቱን አርሶ አደር በ40ኛው የየካቲት 11 በዓል ላይ መገኘታቸው የፈጠረባቸውን ስሜት እንዲገልፁልን ለጠየቅናቸውም የሚከተለው ምላሽ ሰጥተዋል…

“ወይለይ ብዝ ዓባናይሎሚ ዘበን ብዓል ለካቲት ድአ እንታይ ኸዝረበሉ ኢልካዩ አታወዳይ!? ከምቲ ትርእዮ ዘለኸፍሉይድ ምቀት ዝተፀንበለ እዩ እምበርኧ!” እንዴ ስለ ዘንድሮው የየካትት 11 በዓልማ ምኑ ይነገራል ብለህ ነው የኔ ልጅ! ይኸው እንተም እንደምታየው ልዩ ድምቀት ተጎናፅፈዋል እንጂ።

ከእርሳቸው ጋር የነበረኝን የደቂቃዎች ቆይታ እንደጨረስን ያመራሁት ደግሞ በአዲሱ የመቀለ እስቴድየም አንዱ ጥግ ላይ ሰብሰብ ብለው ወደ ተቀመጡ ጥቂት የጦር ጉዳተኛ ታጋዮች ነው። እናም ማንነታችንን ገልፀን ስለ በዓሉ አከባበር የተሰማቸውን እንዲነግሩኝ ጠየቅሁ።

እነርሱ ግን የበዓሉ ድምቀት በፈጠረው ልዩ ድባብ ከመመሰጣቸው የተነሳ እኔን እንብዛም ልብ ያሉኝ አይመስሉም። ስለሆነም ቀልባቸውን የወሰደው የመድረክ ትዕይንት ተከናውኖ እስኪያልቅ ጠብቄ ነው ምን እንደፈለኩ ያስረዳኋቸው። ከዚያም የጉዳዩን አስፈላጊነት ከመረዳት በመነጨ ፍቃደኝነት ጭንቅላታቸውን እየነቀነቁ እኔም እንድቀመጥ ጋበዙኝና ጭውውታችን ጀመርን።

ምንም እንኳን አብዛኞቹ በደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ምክንያት ራሳቸውን ችለው ለመንቀሳቀስ እንደሚቸገሩ ብረዳም የታጋይነት ወኔያቸው አሁንም ድረስ ጢም እንዳለ ስለ መሆኑ ግን የሰጡንን አስተያየት በማንበብ መፍረድ አያዳግትምና እነሆ እንደሚከተለው አቀነባብሬዋለሁ። ታጋይ የጦር ጉዳተኞቹ በቁጥር ሰባት ወይም ስምንት ያህል እንደነበሩ ልብ ይባልልኝና እርስ በእርሳቸው እየተጋገዙ የሰነዘሩትን ሃሳብ ለእኔ እንዲያመቸኝ አድርጌ ባቀርበው ቅር እንደማይሰኙ ስለገለፁልኝ ይሄው በስምምነታችን መሠረት እንዲህ ጠቅለል ባለ መልኩ አቀርቤላችኋለሁ…

“መቼስ የየካተት 11ን በዓል ማክበር ለእኛ ለህወሓት ነባር ታጋዮች አዲስ ነገር እንዳልሆነ እናንተም የሚገባችሁ ይመስለኛል። ምክንያቱም በትጥቅ ትግሉ ዘመን እንኳ የደርግ መንግስት ድርጅታችንን በሃይል ለመጨፍለቅ ሲል በሚያካሂደው መጠነ ሰፊ ወረራ ውስጥ ሆነን ጭምር የካቲት 11ን ከማክበር ተቆጥበን አናውቅምና ነው !” በማለት አንደኛው የአካል ጉዳተኛ ታጋይ የጀመረልኝን ጨዋታ ሌላ ጓደኛው ተቀብሎ ቀጠለበት…

“ይሄ ጓድ የነገራችሁ ትክክል ነው …! እንዲያውም አንድ ጊዜ ለየካትት 11 በዓላችን ማክበሪያ ጫካ ውስጥ ያዘጋጀነውን ድግስ የደርግ የጦር አውሮፕላኖች ድንገት መጥተው ባዘነቡበት የቦምብ ናዳ ምክንያት ጠላውም ምግቡም ከጥቅም ውጭ እንደሆነ አስታውሳለሁ። ለነገሩ በዚያን ቀኑ ድንገተኛ የአውሮፕላን ድብደባ ተመትተው የተሰውና የቆሰሉ ታጋዮች ጥቂት እንዳልነበሩም ትዝ ይለኛል። እንዲያውም ሆኖ ግን የተረፍነው ጓዶቻቸው በዕለቱ የየካቲት 11ን በዓል እንዳናከብር ሊያደርጉን አልቻሉም ነበር” ሲል የትጥቅ ትግል ዘመን ትዝታውን ተረከልን 2ኛው ተናጋሪ።

እኔም ይሄኔ በመሀል ገብቼ “እስቲ የዘንድሮን የየካቲት 11 በዓል እናንተ ነባር የህወሓት ታጋዮች ከዚህ ቀደም ከምታውቁት አኳያ በምን በምን ምክንያት እንደሚለይ ግለፁልኝ?” የሚል ጥያቄ አነሳሁና የመጀመሪያው ተናገሪ የሚከተለውን ምላሽ ሰጠኝ…

“እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የዛሬው በዓል እኛ በትጥቅ ትግሉ ዘመን ከምናውቀው አከባበር ብቻ ሳይሆን ደርግ ከወደቀ ጀምሮ ከተከበሩት የየካቲት 11 በዓላት ሁሉ የተለየ ነው ማለት ይቻላል። ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የካቲት 1967 ዓ.ም ልክ በዛሬዋ ዕለት ደደቢት ላይ የተጀመረው የትግራይ ሕዝብ የትጥቅ ትግል ላለፉት 40 ዓመታት በተካሄደው የሥርዓት ለውጥ ጉዞ ውስጥ ያፈራቸው ወዳጆች ከጊዜ ወደ ጊዜ በቁጥር እየተበራከቱ በመምጣታቸው ድርጅታችን ህወሓት ይዞት የተነሳው ቅን ዓላማ ለመላው ኢትዮጵያውያን ጭምር የመታገያ መድረክ ለመሆን ስለቻለ ይመስለኛል።

በግልፅ አነጋገር እኛ የታገልንለትን ህዝባዊ ዓላማ የሚጋሩ የኢህአዲግ አባል ድርጅቶችና ሌሎችም ወዳጆቻችን የየካቲት 11 በዓልን ሀገራዊ ገፅታ እንዲላበስ እያደረጉት ነው ብሎ ማጠቃለል ይቻላል። በተለይም ደግሞ ይህን ያህል በርካታ ቁጥር ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች መገኘታቸውን ስናይ ህወሓት/ኢህአዲግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በሚያስተማምን ቁመና ላይ ስለመሆኑ እንገነዘባለን” አለና እኔን ምን እንደተሰማኝ ለማወቅ ባለመ መንፈስ ትኩር ብሎ ሲመለከተኝ አሁንም ሌላኛው የቡድኑ አባል ጣልቃ ገብቶ ቀጠለ…

“ደግሞም እኮ እንኳንስ ለኢትዮጵያ ህዝቦች በአፍሪካ ደረጃም ቢሆን በተሳካ የትግል ጉዞ 40ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ለማክበር የበቃ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ ማግኘት እንብዛም የተለመደ ነገር አይደለም። ዋሸሁ እንዴ ጋዜጠኛ?” ሲል የቀልድ ቃና ባዘለ ድምፅ እኔኑ መልሶ ጠየቀኝ ተረኛው ተናገሪ።

“ስለዚህ ሁላችሁም ስደተኞች ናችሁ ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ አስከተልኩ  እኔም እንደ እነርሱ በፈገግታ እየደመቅሁ። አካል ጉዳተኛ ታጋዮቹ “መጠርጠሩስ!?” እንደ ማለት በሚቆጠር የደስተኝነት ስሜት ጭንቅላታቸውን ነቀነቁና ለሌላ ጥያቄ ጋበዙኝ።

ለመሆኑ እናንተ የጦር ጉዳተኛ ታጋዮች አካላችሁን ካጣችሁበት የህወሓት/ኢህአዲግ ዓላማ ጋር በተያያዘ የምትከፉበት ወይም ቅር የምትሰኙበት ምክንያት አለ ወይስ የለም? ካለስ ምንድን ነው?” ስል ላቀረብንላችው የመጨረሻ ጥያቄዬ በሰጡት ተመሳሳይ ምላሽ  ጽሁፌን አጠናቅቃለሁ…

“ እንደ እውነቱ ከሆነ አሁን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከምትገኝበት አጠቃላይ ሁኔታ አኳያ እኛን የጦር ጉዳተኛ ታጋዮችን ለመከፋት ወይም ለቅሬታ የሚጋብዝ መሰረታዊ ጉዳይ አይታየንም። ምክንያቱ ደግሞ ለእኛ ቁልፉ መመዘኛችን የደምና የአጥንት መስዋዕትነት ከፍለን ያመጣነው የስርዓት ለውጥ ለመላው ያገራችን ሕዝቦች ዘላቂ ህልውና መረጋገጥ የሚበጅ ተጨባጭ ውጤት እየመጣ ነው? ወይስ አይደለም? የሚል መሰረታዊ ጥያቄ እንደመሆኑ መጠን በዛሬዋ ኢትዮጵያ የሚስተዋለው እውነታ ሊያስከፋን አይችልም።

ይህ ማለት ግን አንዳንድ ከላይ የተገለፀውን ሀገራዊ እውነታ የሚያደበዝዝ አሉታዊ ተፅእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ጥቃቅን ድክመቶች መኖቸውን ሳንገነዘብ ቀርተን እንዳልሆነ ልብ ይባልልን። እኛ ለማለት የፈለግነው የአካላችንን አንድ ክፍል አጥተን ቀሪ የህይወት ዘመናችንን በዚህ መልኩ ለማሳለፍ የተገደድንበት ዓላማ በህወሓት/ኢህአዲግ አመራር ግብ እየመታ መሆኑን ስለምንረዳ ያን ያህልም የምንከፋበት መሰረታዊ ምክንያት የለም ነው እንጂ መቀረፍ የሚኖርባቸው ተግዳሮቶች እንዳሉማ መካድ አይቻልም።

በዚህ ረገድ እኛንም ጭምር አንገት የሚያስደፋን ወይም ደስታችን ምሉዕ እንዳይሆን የሚያደርገን ደግሞ በተለይ ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር በተያያዘ መልኩ የሚነሳ የህዝብ ቅሬታ ነው።

ሰር ነቀል የስርዓት ለውጡ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ባጎናፀፋቸው ራስን በራስ የማስተዳደር ዲሞክራሲያዊ መብትና የዚሁ መብት ድምር ውጤት በሆኑት ሌሎች የአዲሲቷ ኢትዮጵያ በጎ ገፅታዎች ከልብ የመነጨ ኩራት እንደሚሰማን ሁሉ የመንግስታችንን ደካማ ጎን የሚያመለክቱ የህዝብ ቅሬታዎችን መስማት ያስከፋናል።

ስለሆነም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የፌዴራልና እንዲሁም የክልል መንግስታት የስራ ሀላፊዎች በዚህ አጋጣሚ ማስተላለፍ የምንፈልገው መልዕክት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ ይገባል የሚል ነው” የጥቅሱ መጨረሻ።