ሰላምንና መረጋጋትን እየፈጠረ ያለ አዋጅ

                                               
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተለይም ሁከትና ብጥብጥ በነበረባቸው አንዳንድ የአማራና የኦሮሚያ አካባቢዎች የነበረውን ሁኔታ በአስተማማኝ ሁኔታ እየቀየረ ነው። በዚህም ሳቢያ በእነዚህ አካባቢዎች የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሰላም ወጥተው በመግባት ስራቸውን በተረጋጋ መንገድ በማከናወን ላይ ይገኛሉ። ህዝቡም የአዋጁ አካል በመሆን የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ ነው። 
በተለይም በየደረጃው ከህዝቡ ጋር እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት፤ በፀረ-ሰላም ኃይሎችና በፅንፈኛ ዲያስፖራዎች ገፋፊነት ሳቢያ በጥቂት የሁከት ኃይሎች አማካኝነት ህይወት መጥፋቱ እንዲሁም የህዝብና የግለሰብ ንብረቶች መውደማቸውን አምርሮ ተቃውሟል። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንዲፈፀም የሚያስችል ምንም ዓይነት ሁኔታ ባለመኖሩም፤ የተግባሩ ፈፃሚዎች የሆኑት ግለሰቦች በሀገር ሽማግሌዎች (አባ ገዳዎች) አማካኝነት ተመክረው ያወደሙትን ንብረቶች እንዲከፍሉና ህብረተሰቡን ይቅርታ እንዲጠይቁ እየተደረገ ነው። በህግ መጠየቅ ያለባቸውና አዋጁ አማካኝነትም ይህም በአሁኑ ወቅት በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ያስቻለ እመርታ ነው ማለት ይቻላል። 
ሆኖም ሀገራችን ውስጥ ሰላም ሰፍኖ ህዝቡ ከሰላሙ ተጠቃሚ በመሆን ወደ ጀመረው የልማት ተግባራት ላይ እንዳያተኩር የሚሹ አንዳንድ አካላት፤ “አዋጁ ቱሪዝምን እየጎዳ ነው፤ የኢንቨስትመንት ፍሰትንም ይጎዳል” የሚል ውዥንብር በመንዛት ላይ ይገኛሉ። ዳሩ ግን በእነዚህ ወገኖች የሚሰነዘረው አሉባልታ ከአዋጁ መንፈስ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል—የአዋጁ ዓላማ የሰላሙ ባለቤት ለሆነው ህዝብ ተጨማሪ ጉልበት ለመስጠት እንጂ፣ እነዚህ አካላት እንደሚሉት ቱሪዝምንና ኢንቨስትመንትን ለመገደብ አይደለም። እርግጥ የእነዚህ አካላት ፍላጎት ለሀገራችን ከማሰብ የመነጨ አለመሆኑ ግልጽ ነው። እንዲያውም ከመንግስትና ከህዝቡ በላይ ለዚህች ሀገር አሳቢ ሆነው በመቅረብ በተዘዋዋሪ አዋጁን ለማጥላላት የሚሰነዝሩት አባባል መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም። 
ያም ሆኖ መሬት ላይ ያለው ዕውነታ እነርሱ ከሚሉት ጋር የሚጣረስ ነው። ይጋጫል። ይኸውም የአዋጁ ግብና ዓላማ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተስተዋለውን የፀጥታ መደፍረስ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር ለማዋል ብሎም የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ ስለሆነ ነው። በተለይም አዋጁ በየቦታው ለታየው ሁከት፣ ረብሻና ስርዓት አልበኝነት ዋነኛ ምክንያቶችን በመግታት፤ ሀገራችንና ህዝቦቿ ወደ ነበሩበት ጭስ አልባው የቱሪዝም ኢንዱስትሪና አሁንም ድረስ ያልቆመው የኢንቨስትመንት ፍሰት ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያደርግ እንጂ እነዚህን የልማት ዘርፎች የሚያላላ አይደለም።
እንደሚታወቀው ለቱሪዝም ፍሰት እና ለኢንቨስትመንት መስፋፋት የሰላም መኖር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። በአንድ ሀገር ውስጥ ቱሪዝምም ሆነ ኢንቨስትመንት ሊስፋፉና ሊያድጉ የሚችሉት አስተማማኝ ሰላምና ለዘርፎቹ ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ ሲኖር ነው። ከዚህ አኳያ ባባፉት 25 ዓመታት መንግስትና ህዝቡ የሀገሪቱን ሰላም በአስተማማኝ የሰላም መሰረት ላይ ለማቆም ባረደጉት ጥረት እንዲሁም መንግስት ለቱሪዝምም ሁነ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫን በመከተሉ፤ ሁለቱም ዘርፎች ከፍተኛ የሆነ እመርታ አሳይተዋል። 
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሀገራችን ‘የሰላም ተምሳሌት’ ተብላ ስትጠቀስ ኖራለች። ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገቧና የነገ ራዕይዋ ከወዲሁ እየታየ በመሆኑም የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች መዋዕለ ነዋያቸውን ሀገራችን ውስጥ በማፍሰስ አብረውን ለማደግ ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛሉ። ሆኖም ላለፈው አንድ ዓመት ያህል ሀገራችን ውስጥ በተፈጠረው የመረጋጋት ችግር ወደ ነበርንበት የተረጋጋ ቦታችን ለመመለስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ ከተለያዩ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ አካላትን ባቀፈ ኮማንድ ፖስት አማካኝነት ተግባራዊ እየሆነ ነው። በአዋጁ አንቀፅ 18 ላይ “ያለ ፈቃድ ስለሚደረግ የዲፕሎማቶች እንቅስቃሴ” በሚለው ርዕስ ስር፤ “የኮማንድ ፖስቱን እውቅና እና ፈቃድ ሳያገኙ ዲፕሎማቶች ለራሳቸው ደህንነት ጥበቃ ሲባል ከአዲስ አበባ አርባ (40) ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውጪ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው” በሚል ተደንግጓል።  
ታዲያ ድንጋጌው በግልፅ እንደሚያመለክተው ክልከላው ዲፕሎማቶችን ብቻ የሚመለከት እንጂ ከቱሪስቶች ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር አለመኖሩን ነው። ያም ሆኖ ዲፕሎማቶቹም ቢሆኑ ክልከላው የተመለከታቸው ከአዲስ አበባ መውጣት አይችሉም በሚል የመንቀሳቀስ መብታቸውን ለመገደብ አይደለም—ከአዲስ አበባ ሲወጡ ለኮማንድ ፖስቱ በማሳወቅ እጀባ ይደረግላቸዋል ከሚል ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ከማሰብ በመነጨ የኃላፊነት ስሜት እንጂ። እርግጥም የኢፌዴሪ መንግስት እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉትን ሁሉንም የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አካላትን የመጠበቅ ዓለም አቀፍ ግዴታ ያለበት በመሆኑ፤ ሰላምና መረጋጋቱ ይበልጥ አስተማማኝ እስኪሆን ድረስ ዲፕሎማቶቹ ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውጭ ሲንቀሳቀሱ እንዲያሳውቁ መደረጉ ተገቢ ይመስለኛል። ግና እዚህ ላይ አዋጁ በየትኛውም የውጭ ዜጋ ላይ ‘የመንቀሳቀስ መብት’ አለመገደቡን ማወቅ ይገባል እላለሁ። ምክንያቱም ጉዳዩ ለኮማንድ ፖስቱ የማሳወቅ እንጂ በመንቀሳቀስ መብት ላይ ገደብ ከመጣል ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር አይደለምና። 
ያም ሆኖ ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ባለው ራዲየስ ውስጥ ለዲፕሎማቶቹ ደህንነት ሲባል የተቀመጠው የማሳወቅ ተግባር ሰላምና መረጋጋቱ ይበልጥ እየጎለበተና አስተማማኝ እየሆነ ሲሄድ ሊቀር የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን መንግስት በቅርቡ ፍንጭ ሰጥቷል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከመሰንበቻው በፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ የቀረበውን ሞሽን ለማስፀደቅ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አማካኝነት ሀገራችን ውሰጥ ያለው ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ እየሆነ በመምጣቱ በዲፕሎማቶች ላይ ለደህንነታቸው ሲባል ተጥሎ የነበረው ገደብ የሚነሳበትን ሁኔታ መንግስታቸው ሊያየው የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል። ሌሎች አዋጁ ላይ የተቀመጡ ገደቦችም እንደ ሁኔታው እየታዩ ሊነሱ የሚችሉበት አግባብ ሊኖር እንደሚችል መጠቆማቸውም እንዲሁ። ይህ ሁኔታም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰላምና መረጋጋትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕውን እያደረገ መሆኑን የሚያመላክት ይመስለኛል።
በእኔ እምነት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለቱሪስቶችና ለኢንቬስተሮች ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው። ቱሪስቱ ከተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ወደ ሀገራችን ለጉብኝት ሲመጣ፤ ሀገሪቱ ውስጥ አስተማማኝ ሰላም መኖሩን አረጋግጦ ነው። እርግጥ ይህ ሰላም ላለፉት 25 ዓመታት በጥሩ መሰረት ላይ የተገነባ በመሆኑ እንደ ደንቡሽት ቤት በጥቂት ጊዜ ውስጥ የሚፈራርስ አይደለም። ምንም እንኳን በየትኛውም ማህበረሰብ ውሰጥ ሰላም ያለው እሴታዊ ዋጋ የሚታወቅ ቢሆንም፤ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ያላቸው ሀገራት ሰላማቸው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሲደፈርስ ብሎም በትርምስና ሁከት ውስጥ ሲቆዩ የተመለከትናቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም። 
ከእኛ ሀገር አንፃር ግን ሰላማችን ሲጀመር የተገነባው በህዝቦች ፅኑ ፍላጎት በመሆኑ በቀላሉ ሊናጋ የሚችል አይመስለኝም። ሆኖም ልክ እንደ አለፈው አንድ ዓመት ሰላማችን የመሸራረፍ ሁኔታ ሲያጋጥመው የሰላሙ ባለቤቶች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመሆናቸው በቀላሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተለያዩ ድንጋጌዎችን በማውጣት መጠገን ይቻላል፤ እየተቻለም ነው። ይህም ወደ ሀገራችን መምጣት ለሚፈልጉ ቱሪስቶች አስተማማኝ ዋስትናን ይሰጣል። 
ኢንቬስተሮችም በአዋጁ ዋስትናቸው በአስተማማኝ ሁኔታ የሚረጋገጥ ይመስለኛል። በስራቸው ላይ የሚፈጥረውም ተፅዕኖም ሊኖር አይችልም—ሰላምን ይበልጥ አስተማማኝ በማድረግ መዋዕለ ነዋያቸውን ይበልጥ እንዲያፈሱ ያነሳሳቸዋል እንጂ። እርግጥ ሀገራችን ለወደፊቱ ብሩህ ተስፋ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ እየሆነች ነው። ለዚህም ከመሰንበቻው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF)፤ ኢትዮጵያ በመጭው ዓመት በምሥራቅ አፍሪቃ የኢኮኖሚ መሪነትን ከኬንያ እንደምትረከብ ያወጣውን ትንበያ መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል። ይህም ሀገራችን ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል በተወሰኑ አካባቢዎች የነበረው ሁከትና ብጥብጥ በሀገራችን የልማት ግስጋሴ ውስጥ ትርጉም የሌለው ተፅዕኖ አለመፍጠሩን የሚያሳይ ነው። 
እርግጥ ሁከትና ብጥብጥ በነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው የንብረት ውድመት ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ አልፈጠረም ሊባል አይቻልም። ይሁንና ችግሩ ከመንግስትና ከህዝብ አቅም በላይ የሚሆን አይደለም። በቀላሉ በመንግስትና በህዝቡ ጥረት ሊስተካከል የሚችልና በመስተካካል ላይ ያለ ጉዳይ ነው። የሰላም ማጣት ትንሽ ባይኖረውም፤ ከጠቅላላው የሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ አኳያ ሲታይ፣ ችግሩ ያስከተለው የልማት መስተጓጎል እዚህ ግባ ሊባል የሚችል አይመስለኝም። 
በመሆኑም በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው የሰላም እጦት በመንግስትና በህዝብ ቅንጅታዊ ስራ በቀላሉ በቁጥጥር ስር እየዋለ በመሆኑ እንዲሁም ዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋማት የመሳሰሉ ድርጅቶች ሀገራችን የምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የኢኮኖሚ ባለቤት እንደምትሆን መተንበያቸው ኢንቬስተሮችን የሚያረጋጋ ይመስለኛል። እስካሁንም ድረስ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ተጠናክሮ መቀጠሉ ይህን አባባሌን የሚያጠናክረው ይመስለኛል። እናም አዋጁ ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር ለቱሪስቱም ሆነ ለኢንቬስተሩ ምቹ ምህዳርን እያረጋገጠ መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት እውነታውን ማወቅ እንጂ ከነባራዊ ሃቁ መራቅ አይሆንም ባይ ነኝ። በመጨረሻም እኔም ሀገራችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተለይም ሁከቱ ተፈጥሮባቸው በነበረበት አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ ሰላሟንና መረጋጋቷን ዕውን እንደምታደርግ በመተማመን፤ መጭው ጊዜዋ እንዳለፉት ጊዜያት የምስራቅ አፍሪካ የሰላም ጮራ ፈንጣቂና አሁን ካለው ይበልጥ ጠንካራ የኢኮኖሚ አብሳሪ እንደምትሆን በመመኘት ፅሑፌን እዚህ ላይ እቋጫለሁ።