ህዝብን ይዞ የማይወጣ ዳገት የለም!

ሀገራችን ከ2003 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ የተካሄደውን የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ተልማ በአጥጋቢ ሁኔታ ገቢራዊ አድርጋለች። ከቀዳሚው ዕቅድ ተከታይና ተመጋጋቢ የሆነና ከ2008 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ተፈፃሚ የሚሆን፣ ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነድፋም ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ ከጀመረች ከአንድ ዓመት በላይ ሆኗታል። 
ምንም እንኳን ዕቅዱ በተጀመረበት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ምክንያት ምጣኔ ሐብታዊና ማህበራዊ መስተጋብር መስተጓጉሎች መፈጠራቸው እርግጥ ቢሆንም፤ ይህ ሁኔታ ግን ዕቅዱን በአግባቡ እንዳንፈፅም የሚያደርገን አይደለም። 
ቀሪው ጊዜ ረጅም ስለሆነም ዕቅዱን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማሳካት የሚያግደን ነገር ያለ አይመስለኝም—ምንም እንኳን የሀገራችንን ዕድገትና ብልፅግናን የማይሹ አንዳንድ የውጭ ኃይሎችና ተላላኪዎቻቸው ጥረት ቢደርጉም። ሁሉም በላይ ሀገራችን የያዘችው ዕቅድ ብሔሮቿ፣ ብሔረሰቦቿና ህዝቦቿ ተወያይተው የገቡበት በመሆኑ የማይሳካበት ምክንያት ሊኖር የሚችል አይመስለኝም—ህዝብን ይዞ የተከናወነ ማንኛውም ልማት ግቡን መምታቱ አይቀርምና። አዎ! ህዝብን ይዞ የማይወጣ ዳገት፣ የማይወረድ ቁልቁለት ስለሌለ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥን ለማምጣት የታቀደው የልማት ዕቅድ ስኬታማ መሆኑን መጠራጠር የሚገባ አይመስለኝም። በመሆኑም እኔም በዚህ ፅሑፌ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ በልማት ዕቅዱ የተያዙትን አንኳር ነጥቦች አለፍ…አለፍ እያልኩ ለመቃኘት እሞክራለሁ።   
በሁለተኛው የልማት ዕቅድ ዘመን ከሚከናወኑት ጉዳዩች ውስጥ “ዘላቂ የልማት ግቦች” (Sustainable Development Goals) ተጠቃሽ ነው። በመሆኑም ሁሌም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ማዕከል የሚያደርገው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስትም ተነሳሽነቱን በመውሰድ ከዓለም አቀፉ ራዕይ ውስጥ የተወሰኑትን ለማሳካት ይቻል ዘንድ በዕቅዱ ውስጥ እነዚህን ግቦች እንዲካተቱ አድርጓል። ርግጥም ልክ እንዳለፈው የልማት ዕቅድ ሁሉ፣ በሁለተኛው የዕቅድ ዘመንም መንግስትና ህዝቡ በጋራ ተባብረው የተወሰኑትን ግቦች እንደሚያሳኩ መናገር የሚቻል ይመስለኛል።
በዕቅዱ ውስጥ በዓለም ላይ ያሉ የመለዋወጥ አዝማሚያዎችም ታሳቢ ሆነዋል። እርግጥ በዚህ ዘመን ሁሉም ነገሮች በፈጣን ሁኔታ ይለዋወጣሉ። ታዲያ ለውጦቹ ሀገራችንን በመሳሰሉ እየለማ የሚገኝ ኢኮኖሚ ባላቸው ሀገራት ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸው ስለማይቀር፣  በለውጦቹ ሳቢያ የሚፈጠሩ አዎንታዊና አሉታዊ ጉዳዩች ከግምት ውስጥ ገብተዋል። 
እንደ እውነቱ ከሆነ በዓለም ላይ የሚከናወኑ ሁሉንም አዝማሚያዎች ግምት ውስጥ አስገብቶ ዕቅድ ውስጥ ማካተት ሊፈጠሩ የሚችሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ነው። ሰነዶች እንደሚያመለክቱት፤ ሀገራችን በቀጣዩቹ አስር ዓመታት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን፣ የክፍለ-አህጉር የንግድና ኢኮኖሚ ቀጣናዎች ነፃ በሆነ ሁኔታ የማካሄድ፣ የምጣኔ ሃብታችንን በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት የማሳደግ እንዲሁም ያደጉ ሀገራት አነስተኛ ኢኮኖሚ ላላቸው ሀገሮች የሰጡት ከቀረጥና ከኮታ ነፃ የሆኑ የገበያ ዕድሎችን ይበልጥ በማስፋት ተጠቃሚ መሆንን የመሳሰሉ ጉዳዩችን እንዲያካትት ተደርጎ ዕቅዱ ገቢራዊ ሆኗል። 
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ፓርላማ ተገኝተው በፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ የሀገራችንን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ግብርናውን ማዘመን ዋናው ጉዳይ እንደሆነ ገልፀዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም የመስኖ ግብርናን ማስፋትና ግብርናን መሰረት ያደረጉ የግብርና ግብዓት የሚጠቀሙ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ትኩረት እንደሚሰጠውም አስረድተዋል። 
አዎ! በተያዘው የዕቅድ ዘመን ለልማታችንና ለፈጣን ዕድገታችን የማይተካ አስተዋፅኦ የሚያደርገውና የግብርናው ዘርፍ ዕድገታችን ቀዳሚ ማገር እንዲሆን ተተልሟል፡፡ ከዚህ አኳያ ቀደም ባሉት ጊዜያት ለውጥ ማምጣት የጀመሩትን የስትራቴጂክ የምግብ ሰብሎች ምርታማነትና ጥራት የበለጠ ከማሳደግ በሻገር የላቀ ዋጋ የሚያወጡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችና የኤክስፖርት ምርቶች ላይ የልማት ቀጣናን ማዕከል ያደረገ ርብርብ በማድረግ ልዩ ትኩረት በመስጠት ግብርናው የመሪነት ሚናውን ለኢንዱስትሪው እስከሚያስረክብ ድረስ ብርቱ ርብርብ ይደረጋል። 
ምን ይህ ብቻ። መዋቅራዊ ለውጡን ለማምጣት የመስኖ ግብርና የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሥራን በከፍተኛ ደረጃ እንዲስፋፉ ይደረጋሉ፡፡ በምርት ሂደት ውስጥ ተዋናይ የሆኑ የአርሶና የአርብቶ-አደሩ የቤተሰብ ግብርና ተጠናክሮ የሚቀጥል ሆኖ የአርሶ አደሩ የተማሩ ወጣቶችና የግል ባለሃብቱ ቅንጅት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል፡፡ ይህንን ለማድረግም በግብርና ልማትና ግብይት ውስጥ ያሉ የሥርዓት ማነቆዎችን በአስተማማኝ ደረጃ መፍታት ልዩ ትኩረት በመስጠት ወጣቱን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቧል፡፡     
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ራዕይ ራሱን ችሎ በመቀመጡ ሳቢያ ላለፉት 12 ተከታታይ ዓመታት የተመዘገበውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠልና የመካከለኛ ገቢ ራዕዩን ለማሣካት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚመዘገበው እመርታና በኢኮኖሚው ላይ የሚከሰተው መዋቅራዊ ለውጥ ልዩ ትኩረት አግኝተዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም የኢኮኖሚው የማምረት አቅም ላይ ለመድረስ ቅልጥፍና መጨመርና አምራች ዘርፎች ለጥራት፣ ለምርታማነት እና ለተወዳዳሪነት የላቀ ድርሻ እንዲኖራቸው ታስቧል። ለዚህም ይመስለኛል—የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ለፓርላማው በሰጡት ማብራሪያ ላይ፤ ክልሎች አነስተኛ እና መካከላኛ ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋት ድርሻ ይዘው እንደሚንቀሳቀሱና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ይህንንም ለመደገፍ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተዘረጋው የማሽነሪ ሊዝ ፋይናንሲንግ ስርዓት ገቢራዊ እንደሚሆን ያስታወቁት።  
በዕቅዱ ላይ የከተማነት መስፋፋት ፈጣን ዕድገትና መዋቅራዊ ለውጥ አስተዋፅኦ የጎላ እንዲሆን ለማስቻል እና ከሚጠበቀው ፈጣን ኢንዱስትራላይዜሽን እንቅስቃሴ ጋር ለማጣጣም የሚያስችል ትልም ተይዟል። ለሀገር ውስጥ የግል ባለሃብቶችም ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ በዚህም የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በሚሳተፉባቸው ሁሉም ዘርፎች የሚበረታቱበት ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ገቢራዊ በመሆን ላይ ይገኛል። 
በአነስተኛና ጥቃቅን ደረጃ የሚገኙትን ኢንተርፕራዞች ወደ መካከለኛ እና ከፍተኛ ማኑፋክቸሪንግ የማሸጋገርና በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩትን ደግሞ በተደራቢ ለራሳቸው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማምረት የገቢ ምርትን በመተካት ላይ እንዲያተኩሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠትም ታቅዷል፡፡ የሰው ሃብት ልማትን በቴክኖሎጂ አቅም ተደግፎ ስራውን እንዲያከናውን ለማስቻልም ሰፊ ስራ እንደሚከናወን ዕቅዱን አስመልክቶ የወጡ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡
ሀገራችን የምትታወቅበት የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂም በዕቅዱ ላይ ከተያዙት ጉዳዩች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራትም ዕቅድ ተይዟል፡፡ እናም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂን በማዘጋጀትና በመተግበር ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በዕቅዱ ዓመታት ውስጥ የአካባቢ ሙቀት ሳቢ ጋዞችን ልቀት የመቀነስ፣ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የእንስሳትና የሰብል ምርታማትን በማሳደግ የአርሶና አርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ደንን መጠበቅና ማልማት፣ ከታዳሽ ኃይል ምንጭ የኤሌክትሪክ ኃይል በሰፊው ማመንጨትና ዘመናዊና ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን በትራንስፖርት፣ በኢንዱስትሪና በህንፃ ኮንስትራክሽን ዘርፎች በመጠቀም በኩል ሰፋፊ ስራዎችን ለመተግበር ራዕይ ሰንቃለች፡፡ ሌሎች የሀገራችንን ችግር የሚፈቱና የህዝብን ተጠቃሚነት፣ እርካታንና አመኔታን የሚፈጥሩ የልማት ግቦችም ለውጥ በሚያመጡበት ደረጃ ተፈፃሚ እንዲሆኑም ግብ ተጥሏል።
ታዲያ እነዚህ ሁሉ የልማት ዕቅዶች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉት በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ መሆኑ አጠያያቂ አይመስለኝም። እርግጥም የህዝቡ የልማቱ መሰረትና አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑ የሚታበይ አይደለም። እናም ይህን ለዕድገቱ ቀናዒና ለተጠቃሚነቱ ታታሪ የሆነን ህዝብ ይዞ ከግብ የማይደርስ ልማት አይኖርም። ይህን ለሀገሩ ሰላም የሚተጋን ህዝብ ይዞ የውጭ ኃይሎችን ሴራና የተላላኪዎቻቸውን መልዕክት ሀገር ውስጥ ሳይገባ መንገድ ላይ ማስቀረት የማይቻልበት ምክንያት የለም። አዎ! የሀገራችንን ሁለንተናዊ ችግሮች ከህዝቡ ጋር በመሆን ማስተካከል እንደሚቻለው ሁሉ፤ የሀገራችንን ዕደገትም ከህዝቡ ጋር በመሆን በማሳለጥ የውጭና የውስጥ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችን አፍ ማስያዝ የማይቻልበት ምንም ዓይነት አመክንዮ ሊኖር የሚችል አይመስለኝም—ህዝብን ይዞ የማይወጣ ዳገት እንዲሁም ሸጥና ቁልቁለት የለምና።