አራቱ ኩታ ገጠም ችግሮቻችን

 

ከመስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን አገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያስፈጽም ታስቦ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት፤ የተጣለበትን ኃፊነት በአግባቡ እየተወጣ ስለመሆኑ ከሚሰጣቸው ወቅታዊ መግለጫዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ለአብነትም ከሰሞኑ ኮማንድ ፖስቱ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ እንደተመለከተው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና  እነርሱን ለማገዝ የመጡ ሌሎች ዲፕሎማቶች ጭምር ከአዲስ አበባ እንባዛም ርቀው እንዳይሄዱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጥሎባቸው የነበረው እግድ መነሳቱን አሳውቋል፡፡

ሌሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ሲባል የተደነገጉ የእገዳ አንቀጾችም እንዲሁ ደረጃ በደረጃ እንደሚነሱና አጠቃላይ አዋጁም አስቀድሞ ከተገመተው  የስድስት ወራት ዕድሜ ባጠረ ጊዜ ሊያበቃ እንደሚችል ጭምር ነው ኮማንድ ፖስቱ በወቅታዊው መግለጫው አክሎ ያሳወቀው፤

ይህ ማለት ደግሞ፤ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነግግ ምክንያት የሆኑት አሳሳቢ የአገራዊ ደህንነት አደጋዎች እንዲቀለበሱና የችግሩን መጠን በጸጥታ ኃይሎቻችን ጥረት መቋቋም ወደ ሚቻልበት ደረጃ እንዲወርድ ማድረግ መቻሉን የሚያመላክት መልካም ዜና ይመስለኛል፡፡

ስለዚህም፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማውጣት እጅግ በጣም አስፈላጊ ሆኖ እንዲገኝ ያደረጉት የአገራችን ወቅታዊ ችግሮች ከምን የመነጩ ናቸው? የሚል ጥያቄ ማንሳትና ተገቢ ምላሸ መስጠት ቀጣይ የቤት ስራ ሊሆን እንደሚገባ ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገግም ሆነ የተደነገገውን አዋጅ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ አመርቂ ስራ መስራት ፋይዳ የሚኖረው ለዘለቄታዊው አገራዊ ግብ መምታት ትርጉም ያለው አዎንታዊ ተፅእኖ ማሳደር የሚችል አዲስ አቅም ፈጥረን እንድወጣ በሚያደርግ መልኩ ወደ ተጨባጭ ጠቀሜታ ስናሳድገው ብቻ እንደመሆኑ መጠን፤ ዋነኛው ጉዳይ አራቱን ኩታ ገጠም የጋራ ችግሮቻችንን ለመሻገር መረባረብ ነው የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡

እንደእኔ የግል ግንዛቤ ከሆነ፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት እንደምንም ታግለው ሊሻገሯቸው ይገባል የምላቸው አራቱ ኩታ ገጠም ወይም ደግሞ  ተወራራሽ አገር አቀፍ ፈተናዎቻችን የመልካም አስተዳደር እጦት ተደርጎ የሚወሰደው ስር የሰደደ ችግርና እርሱን ይበልጥ በማባባስ ረገድ አሉታዊ ሚና የሚጫወቱት ወገኖች የሚገለጽባቸው ሶስት ተያያዥ ዕክሎች እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡

ከዚህ አኳያ ለአገር አቀፋዊ ተደጋጋሚ የሕዝብ ቅሬታ መደመጥ ምክንያት እንደሆነ የሚታመንበትን የመልካም አስተዳደር እጦት ጉዳይ ገና በቅጡ ያልተሻገርናቸው እንድም አራትም ሊባል የሚችል ተዛማጅ ይዘት ያላቸው ችግሮቻችን አስኳል አድርገን ብንወስደው፤ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚተግባር የሚገለጽባቸው ኢ-ፍትሐዊ የጥቅም ክፍፍሎችና ለዚሁ ህገ ወጥ ድርጊት መበራከት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደሩ የሚገኙት የትምክህት እና የጠባብ ብሔርተኝነት  ጽንፈኛ አስተሳሰብ አቀንቃኝ ቢሮክራቶች ደግሞ ሌሎቹ ትኩረት የሚሹ ተግባሮቻችንን ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

እነዚህን እርስ በእርስ የመመጋገብ ባህሪይ ያላቸው ተጓዳኝ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል የመፍትሔ ሀሳብ ስለመለዋወጥ አስፈላጊነት ሲነሳም ጭምር ጉዳዩ ይሄኛውን አሊያም ደግሞ ያኛውን ብሔር ለማሸማቀቅ ሲባል እንደተቃጣ አላስፈላጊ ትንኮሳ ሲቆጥሩት የሚስተዋሉ ወገኖች መኖራቸው ግን ነገሩን እያወሳሰበው ያለ ይመስላል፡፡ ምንም እንኳን ስለትምክህተኝነትም ሆነ ስለጠባብ ብሔርተኝነት የአስተሳሰብ ጽንፍ ጎጂነት ደፍረን ለመናገር የምንገዳገደው ጉዳዩ ከወዲሁ ትኩረት ተሰጥቶት እልባት ካልተበጀለት መላውን የአገራችንን ሕዝቦች ለጋራ ጥፋት የሚዳርግ አጠቃላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ከሚል የሃላፊነት ስሜት እንጂ፤ የየትኛውም ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊ የህብረተሰብ ክፍል ላይ የተለየ ዓላማ ኖሮን እንዳልሆነ አይገነዘቡም ባይባልም፤ እነርሱ  እንደፈለጉ ትርጉም  ሲሰጡትና የአማራን ወይም ደግሞ የኦሮሞን ሕዝብ የሚመለከት ለማስመሰል ባለመ ጸጉር ስንጠቃ ሲጠመዱ የሚስተዋሉ የ‹‹ፌስቡክ›› ፖለቲከኞች መበራከታቸው ግን የሚካድ አይደለም፡፡

ስለዚህም ነው አሁን ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመደንገግ እንድንገዳድ ምክንያት ከሆኑት የአገራችን ወቅታዊ ችግሮች መካከል የጠባብ ብሔርተኝነትና የትምክህት አመለካከትን የሙጥኝ ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች የየራሳቸውን ጽንፍ ወክለው የሚያደርጉት ጸረ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አፍራሽ እንቅስቃሴ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል የምለው፡፡

እነዚሁ የትምክህትንና የጠባብ ብሔርተኝነትን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ጽንፍ በመሪ ተዋናይነት ሲያንቀሳቅሱ የሚያስውሉት ተቃዋሚ ቡድኖች፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከፈርጀ ብዙ ድህነት ጋር የሞት ሽረት ትግል የገጠሙበትን የልማት ንቅናቄ በበጎ መንፈስ መመልት ካቃታቸው እንደግብጽ ካሉ ስትራቴጂክ ጠላቶቻችንን ጋር እየተመሳጠሩ፤ እኛን በብሔር ወይም በሃይማኖት ልዩነታችን ምክንያት አናቁረው አገራችንን ወደለየለት ትርምስ ለማስገባት የማይፈነቅሉት የክፋት ድንጋይ ሊኖር እንደማይችል ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የተረዳንበት ወቅት ላይ የምንገኝ እንደመሆናችን መጠንም፤ እነርሱን በቸልታ ማለፍ የማይታሰብ ጉዳይ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡  ወጣም ወረደ ግን፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተደነገጉት የሕግ አንቀጾች ተፈጻሚ ሆነው የታለመላቸውን ግብ መቱ ሊባል የሚችለው፤ በተለይ ለአዋጁ መውጣት እንደ አስገዳጅ ምክንያት የሚወሰዱትን የዚህች አገር አሳሳቢ ችግሮች ትርጉም ባለው ስፋትና ጥልቀት የመቅረፍ ጥረት ለማድረግ የሚያስችለንን አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ሲቻል ነው፡፡

በግልጽ አነጋገር፤ ከላይ እንደ ማሳያ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ገና ያልተሻገርናቸውን አገር አቀፍ የጋራ ችግሮቻችንን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቅረፍ የሚያስችል ዘለቄታዊ የመፍትሔ እርምጃ እየወሰድን፤ ሕዝቡ ክፉኛ የሚማረርባቸውን አንገብጋቢ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንዲመለሱለት ማድረግ እስካልቻልን ድረስ፤ እነዚሁ ድክመቶቻችን በሚፈጥሩላቸው ጥቃቅን ክፍተቶች እየተጠቀሙ እኛን እንደ ህብረተሰብ ርዕስ አበጣብጠው ኢትዮጵያን ወደለየለት ትርምስ ሊያስጋቧት የሚሹት የውጭና የውስጥ ኃይሎች እየጋረጡብን ያለውን አሳሳቢ ፈተና፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ሲባል በሚሰራ ስራ ብቻ መቀልበስ እንደማይቻል ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል ማለቴ ነው፡፡

ስለሆነም፤ በዚህ መጣጥፍ የተወሱትንና መሰል ይዘት ያላቸውን አንገብጋቢ መፍትሔ የሚሹ ተጨባጭ ችግሮቻችንን በማያሻማ መልኩ እየቀረፍን ሁከት ፈጣሪ ቡድኖችን የሚያስተናግድ ምንም ዓይነት አጀንዳ ወይም ደግሞ የህዝብ ቅሬታ እንዳይኖር የማድረግ የቤት ስራችንን መስራት እንደሚጠበቅብን ሊሰመርበት ይገባል እላለሁ፡፡

በተረፈ ግን አዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ እያሳየ ላለው ጥረት አድናቆቴን ሳልገልጽ አላልፍም፡፡ መዓ ሰላማት!