‹‹የአክሱም ጫፍ አቁማዳ››

ገጣሚው ደበበ ሰይፉ፤ ‹‹ከአክሱም ጫፍ አቁማዳ›› ብሎ የሚጠራው አንድ ግጥም አለው፡፡ ይህ ግጥም እንደሚከተለው ይነበባል፤
እኔ እና ወንድሞቼ …. ሁላችን ሁላችን፤
ከባዶ አቁማዳ ነው እሚዛቅ ፍቅራችን፡፡
‹‹ከአክሱም ጫፍ አቁማዳ›› ከተሰኘው ግጥም የተወሰዱት፤ ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለቱ የደበበ ስንኞች፤ የግጥሙ ዘውድ ወይም ኃይለ ቃል የሆኑ ስንኞች ናቸው፡፡ ግጥሙ ተራኪ ነው፡፡ የአንድ ወቅት ኢትዮጵያውያንን ፈተናኝ ይተርካል፡፡  በሐገሩ ረሃብ ገብቷል፡፡ በሐበሻ ጓዳ ሸረሪት አድርቶበታል፡፡ በአውድማው አይጥ ይፈነጭበታል፡፡ መሶብ እና ሌማቱ ግትቻ ሆኗል፡፡ ከጓዳ አንዲት ቅንጣት ጥሬ ጠፍቶ፤ የሐበሻ ቱቢት ተገምዶ፤ ቅስሙም አንገቱም ተሰብሮ፤ አንጀቱ በረሃብ ተፈርፍሮ፤ የሐበሻ የኑሮ መልካ ተናግቶ፤ ‹‹እባክህ አንድ ቁና ጤፍ አበድረኝ?›› ከሚል መልዕክት ጋር አንዲት አቁማዳ በምድረ ኢትዮጵያ ትዞራለች፡፡ ይህችን አቁማዳ ትግራይ – ለወሎ ላካት፤ ወሎ – ለሸዋ፤ ሸዋ – ለሐረር፤ ሐረር – ለባሌ ይልካታል፡፡ 
‹‹እባክህ አንድ ቁና ጤፍ አበድረኝ›› ብሎ አንዱ ለሌላው ይልክበታል፡፡ ሁሉም ‹‹የለኝም›› ማለት እያፈረ፤ ወገኑ ሲቸገር ለመርዳት አለመቻል ‹‹ባህሉን መንቀፍ›› ሆኖበት እየተቸገረ፤ ለተራበ ወገኑ እህል ለመላክ ያን አቁማዳ ‹‹እህል አበድረኝ›› እያለ፤ ችግሩን ውጦ ዝም ወዳለው ጎረቤቱ ይልከዋል፡፡ የራሱን ችግር ቻል – ዋጥ አድርጎ፤ ለወዳጁ ለዘመዱ ለወገኑ ሊደርስለት ይመኛል፡፡ ‹‹ኧረ በሞቴ … ይቺን ብቻ›› እያለ ያጎርሰው የነበረ ወገኑ፤ በልቶ የጠገበ ሳይመስለው ያስተናግደው የነበረ ያ ደግ ዘመዱ፤ ወዳጁ ክፉኛ መቸገሩን ሲሰማ በጣም አዝኖ፤ ከጎረቤቱ እህል ቢያገኝ፤ ተለቅቶ ሊልክለት አስቦ፤ በብቅ አቁማዳውን ይልካል፡፡ 
‹‹እባክህ አንድ ቁና ጤፍ አበድረኝ?›› ብሎ ትግራይ ለወሎ አቁማዳ ሲልክ፤ ወሎ ወደ ሸዋ ላከ፡፡ ሸዋ ለሐረር- ሐረር – ለባሌ፤ ባሌ- ለአርሲ፤ አርሲ – ለሲዳማ፤ ሲዳማም – ለጋሞ፤ ጋሞ – ለከፋ፤ ከፋ – ለኤሊባቡር፤ ሁሉም ኩራቱን ዘቅዝቆ፤ ሐፍረቱን ደብቆ በስውር አቁማዳውን ይልካል፡፡ ኢሉአባቦርም -ለወለጋ፤ ወለጋም -ለጎጃም፤ ጎጃምም – ለጎንደር፤ ለጎንደርም መልሶ ለትግራይ ላከለት ያች ባዶ አቁማዳ ድፍን ኢትዮጵያን ዞረች፡፡ ሁሉም ለጎረቤቱ፤ ‹‹እባክህ ላክልኝ አንድ ቁና ስንዴ፤ ልሞት ነው ተርቤ›› እያሉ የላኳት ያች አቁማዳ፤ ተመልሳ ትግራይ ገባች፡፡ ትግራይም አቁማዳውን አይቶ፤ የእርሱ አቁማዳ መሆኑን ተረድቶ፤ ለዚህ ድንቅ ፍቅር መታሰቢያ እንዲሆን፤ የፍቅራቸው አብነት አፈር እንዳይነካው፤ ክፋት እንዳያረክሰው፤ ለትውልድ መዘክር ይሆን ዘንድ ከአክሱም ሐውልት ጫፍ ሰቀለው፡፡   
እኔ እና ወንድሞቼ …. ሁላችን ሁላችን፤
ከባዶ አቁማዳ ነው እሚዛቅ ፍቅራችን፤ አለ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝቦች እንዲህ ናቸው፡፡ ዛሬ ያች ባዶ አቁማዳ መሙላት ጀምራለች፡፡ በተስፋዋም ታጠግባለች፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝቦች ‹‹ባዶ አቁማዳ›› ይዘው አይዞሩም፡፡ ዛሬ ‹‹የፍቅር ጽዋ›› መሥርተው፤ የህብረት ጀማ አበጅተው፤ በዓመት አንድ ቀን ህዳር 29 ከባለ ‹‹ወር ተራው›› ወይም ‹‹ከባለ ዓመቱ›› ቤት ይገናኛሉ፡፡ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በሐገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፤ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፤ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን፤ የራሳችንን ዕድል፤ በራሳችን የመወሰን መብታችንን፤ ተጠቅመን በነጻ ፍላጎታችን፤ በህግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ፤ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት፤ ቆርጠን በመነሳት፤ ኢትዮጵያ ሐገራችን….በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረን አብረን የኖርንባት እና የምንኖርባት ሐገር በመሆኗ፤ ያፈራነው የጋራ ጥቅም እና አመለካከት አለን ብለን ስለምናምን፤ …አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን፤ ከላይ ለገለጽናቸው ዓላማዎች እና እምነቶች ማሰሪያ እንዲሆነን…..ዛሬ ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ይህን ህገ መንግስት አጽድቀነዋል›› ብለው በአዲስ ጎዳና የህብረት እና የአንድነት፤ የልማት እና የዴሞክራሲ ግንባታ ጎዳና ጉዞውን ጀምረው ለ22 ዓመታት በዚሁ ቀና መንገድ ተጉዘው ከዚህ ደርሰዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ህዝብ በክፉ ቀንም ፍቅራቸው የጸና ነበር፡፡ እንኳን ዛሬ ከረፉ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ሲኖሩ ሳለ ‹‹ከባዶ አቁማዳ›› ፍቅር እየዛቁ በአንድነት ኖረዋል፡፡ ይህ ነገር ከውጭ ሆኖ እኛን ለሚመለከት ሁሉ ግራ አጋቢ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያውያን ሐገራቸውን የሚደፍር የውጭ ጠላት ሲመጣ የውስጥ ችግራቸውን ወደ ጎን አድርገው በአንድነት ተሰልፈው ሐገራቸውን ለዘመናት ከጠላት ጥቃት ጠብቀው፤ በነጻነት ኮርተው ኖረዋል፡፡ 
አሁን ሁኔታችን በእጅጉ ተለውጧል፡፡ ባዶው አቁማዳችን በተስፋ መሙላት ጀምሯል፡፡ እኔ በጣም መለወጣችንን ለመረዳት የሚያስችል አንድ የቅርብ ጊዜ ገጠመኝ አለኝ፡፡ ይህ ገጠመኝ ለመስክ ሥራ በወጣሁበት አጋጣሚ የተፈጠረ ነበር፡፡ ከእኔ ጋር ለሥራ የወጣና በፌዴራላዊት ኢትየጵያ በተቀተጸ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ያለፈ አንድ ወጣት የለውጡ ጎዳና ምን እንደሚመስል ለመገንዘብ የሚያግዝ ሁኔታ ፈጠልኝ፡፡ 
ወጣቱ የፌዴራላዊት ኢትየጵያ ፍሬ ነው፡፡ ከእኔ ትውልድ የተለየ ቋንቋ አለው፡፡ ከልጆቼ የመማሪያ መጽሐፍ የማውቃቸውን አንዳንድ የትምህርት ቃላትን ሲጠቀም፤ እኔ እርሱ በተለያዩ ስርዓተ ትምህርቶች ማህጸን የተወለድን መሆኑ ገባኝ፡፡ በልጆቼ የመማሪያ መጽሐፍ የማውቃቸውን ‹‹እፍግታ፣ ምድገት፣ ልይ ዘር፤ ዋህድ ዘር፣ ነጥበ ፍሌት፣ ነጥበ ብርደት›› የሚሉ ቃላትን ይጠቀማል፡፡ ከእኔ የተለየ የትምህርት ቤት ህይወት ትውስታ አለው፡፡ በእርሱ የብሔር ብሔረሰብ ቀን አከባበር ልዩ ትርጉም አለው፡፡ በእርሱ የትምህርት ቤት ህይወት ውስጥ የብሔር ብሔረሰብ ቀን ክብረ በዓል፤ በደስታ የሚጠቀስ ትውስታ ነው፡፡ 
‹‹የብሔር ብሔረሰብ ቀን ስናከብር .…›› እያለ አንዳንድ ገጠመኞቹ ሲያወራልኝ፤ ክብረ በዓሉ የህይወት ዘመኑ ጌጥ መሆኑን አወቅኩ፡፡ በርግጥ የብሔር ብሔረሰብ ቀንን ልጆቼ ምን ያህል በናፍቆት እንደሚጠብቁት አውቃለሁ፡፡ ተማሪዎች በየዓመቱ የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህላዊ አለባበስ ለብሶ የመሄድ ጉጉት እንዳላቸውም አውቃለሁ፡፡ ሆኖም የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ለአዲሱ ትውልድ የተለየ ስሜት እንደሚሰጠው በውል የተረዳሁት ከወጣቱ በሰማሁት ጨዋታ ነው፡፡ ምናልባት፤ ክበረ በዓሉ ጨፍሮ የመመለስ ከንቱ ሥራ መስሎ የሚታያቸው ሰዎች ምን ያህል እንደተሳሳቱ ሊያስረዳ የሚችል ነው፡፡ የብሔር ብሔረሰብ ቀን፤ አዲሲቱ ኢትዮጵያ የምትሰራበት አንድ ግብዓት ሆኗል፡፡ 
ፌዴራላዊው የሚገርም ነው፡፡ ልጄ ቤተ መጻሕፍት ገብታ የምታደረገው ነገር በወቅቱ ብዙም ትርጉም ሳይሰጠኝ አልፎ ነበር፡፡ አሁን ወጣቱ በተከፈተልኝ አዲስ የዕይታ መስኮት ነገሩን ስመለከተው፤ ዓይን ገላጭ ተዐምር አድርጌ አየሁት፡፡ በወቅቱ ብዙም ትርጉም ያልሰጠኝ ድርጊቷ፤ አሁን ልዩ ትርጉም ይዞ ታየኝ፡፡ ሐገራችን ከመሠረቱ መለወጧን አበሰረኝ፡፡ ሥነ ዜጋ እየተማረ፤ ስለ ዴሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶች እያሰበ እና እየተወያየ የሚያድገው ይህ ትውልድ የሐገሪቱ የተስፋ ቡቃያ ነው፡፡ ልጄ ስነ ዜጋ ስታጠና ‹‹የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነ ህግ›› እያለች ለምትጠቅሰውና ቤተ መጻህፍት ገብታ ተንደርድራ  ለምትገልጠው የሀገራችን ህገ መንግስት ልዩ ስሜት ይዛ እንደምታግ አሰብኩ፡፡ ልጆቻችን ከእኛ ዘመን በብዙ በተለየ የሥነ ምግባር እሴቶች ታንጸው እያደጉ ነው፡፡ የሐገራችን ተስፋ እነዚህ ናቸው፡፡ እንደ ተረት የልጅነት ህልማቸውን እያቀለመ የኖረውን ይህን ህገ መንግስት በደንብ ለመጠበቅ የሚያስችል የህይወት ልምድ ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ ‹‹ህገ መንግስቱ የጸደቀው አሁን ነው›› አልኩ፡፡ 
እንደ ብዙዎቹ ልጆች፤ የእኔም ልጆች ስለብሔር ብሔረሰቦች ቀን የሚያስቡት፤ ከህዳር 29 15 ቀን አስቀድመው ነው፡፡ በዚሁ ሰሞን በሌሎች ብሔሮች ቋንቋ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ለማለት ሲሞክሩ አይቻለሁ፡፡ ቃሉን ከሰው ጠይቀው፤ በትምህርት ቤት በሰልፍ ላይ ወጥተው ይናገራሉ፡፡ ይህ ነገር መኖሩን የተረዳሁት፤ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ፤ ‹‹ሀሹ ሰሮ ገቴብ….›› እያሉ ደጋግመው ሲያወሩ በማየቴ ጥያቄ አቅርቤ ባገኘሁት መልስ ነው፡፡ ምን እያላችሁ ነው? አልኳቸው፡፡ ‹‹እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ማለት ነው›› አሉኝ፡፡ በምን ቋንቋ እንደሆነ ጠየቅኳቸው፡፡ ወላይትኛ መሆኑን ነገሩኝ፡፡ ሌሎች የማላስታውሳቸውን ነገሮችም ብለዋል፡፡ ግን እኔ ማስታወስ የቻልኩት ከላይ የጠቀስኩትን ቃል ብቻ ነው፡፡ 
ልጆቻችን ከእኛ የተለዩ ሆነዋል፡፡ ከተዛባ አመለካከት ተጠብቀው አድገዋል፡፡ ከሐገሪቱ ልዩ ልዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ከልጅነታቸው ጀምረው ተዋውቀው ስለሚያድጉ፤ ሥነ ልቦናቸው በአንድነት ስሜት የታነጸ ይሆናል፡፡ በእውነት ልጆቻችን ይበልጡናል፡፡ ከእኛ ከወላጆቻቸው በተለየ የአስተሳሰብ ዘዬ እያደጉ ነው፡፡ ከፊውዳላዊ እሴቶች እና ከአብዮት እብደቶች ተጠብቀው፤ በዴሞክራሲያዊ እሴቶች ታንጸው ማየት ደስታ ነው፡፡ ልጆቻችን በፌዴራላዊ ስርዓታችን ከሚስተዋሉ አንዳንድ መጥፎ አዝማሚያዎች እና ጉድለቶች ተጠብቀው እንዲያድጉ መሥራት ይኖርብናል፡፡ እግሮቹን በቶሎ ማረም ይገባናል፡፡ ከትናንት የተሻገሩ መጥፎ ጸረ- ዴሞክራሲያዊ እሴቶች እና ባህሎች ወደ ልጆቻችን እንዳያልፉ መትጋት ያስፈልገናል፡፡ ይህን ካደረግን፤ በእውነት የሐገራች መጻዒ ጊዜ በጣም ብሩህ ይሆናል፡፡ እነዚህ ክቡር ፌደራላዊ እሴቶች፤ ወላጆቻችን ባወረሱን ድንቅ የታሪክ ቅርስ መደብ ላይ ሲያድጉ የሚፈጠረው ነገር ያስደስታል፡፡ 
ወላጆቻችንን ‹‹ከባዶ አቁማዳ የሚዛቅ ፍቅር›› አውርሰውናል፡፡ አኩሪ የነጻነት ተጋድሎ ታሪክም ሰጥተውናል፡፡ ይህን የሐገራችንን ህዝብ ልዩ እሴት ስዜስታሎው ጀስማን (CZESTLAW JEŚMAN) የተባለ አንድ አጥኚ በደንብ እንዳስተውለው አድርጎኛል፡፡  ጀስማን ጥናት የታተመ እኤአ በ1968 ነው፡፡ ‹‹ ETHIOPIA: A TEST CASE OF RACIAL INTEGRATION›› በሚል ርዕስ የቀረበው ጥናት ነው፡፡ 
ኢትዮጵያ ‹‹በይነ ብሔራዊ›› (RACIAL INTEGRATION) ግንኙነት ወይም ዝምድና የመመሥረት እና የማጽናት ልዩ ችሎታ ያላት ሐገር መሆኗን የሚጠቅሰው ፀሐፊ፤ ‹‹የተለያየ የዘር ሐረግ ያላቸው ሰዎች በአንድ የፖለቲካ ስርዓት አብረው በሚኖሩበት ጊዜ ሊፈጠር የሚችለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም ብቃት ያላትና ለሌሎች ሐገራት ምሣሌ የምትሆን ሐገር መሆኗን ይጠቅሳል፡፡ ብዝሃነት ያላቸው ህዝቦች አብሮ ለመኖር የሚያስችል አውድ ለመፍጠር ሞዴል ሆኖ ሊያገለግል ይችላል›› ይላል — ጀስማን፡፡ የእርሱን ነገር በዚህ ጽሑፍ ለማየት አልሻም፡፡ ሆኖም ‹‹እነዚህ ሰዎች ይህን ሁሉ ልዩነት አቻችለው በሰላም ለመኖር የቻሉት እንዴት ነው?›› የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ የአብሮ መኖር ቅርስ ያለን ህዝቦች ነን፡፡ ቅኝ ገዢዎች፤ ቅኝ ግዛታቸው ለማጽና ሲሉ የኢትዮጵያውያንን ጉዳይ ይመረምሩ ነበር፡፡ ሩሲያም ሰው ልካ የኢትዮጵያን ሁኔታ ታስጠና እንደነበር ጀስማን ይጠቅሳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በህገ መንግስታቸው ‹‹…. ኢትዮጵያ ሐገራችን በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረን አብረን የኖርንባት እና የምንኖርባት ሐገር በመሆኗ፤ ያፈራነው የጋራ ጥቅም እና አመለካከት አለን›› የሚሉት ይህንኑ ነገር ነው፡፡