ከእውነታ የተጣላ አቋም

ዶ/ር መረራ ጉዲና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉ ቀናት ተቆጥረዋል። ዶ/ር መረራ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተቃውሞው ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል። እርሳቸው ይመሩት የነበረውን የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግሬስ (ኦብኮ) በአባልነት ይዞ የነበረውን የኢትዮጵያ ዴሞክራቶች ኃይሎች ህብረት (ህብረት) በመወከል በ3ኛው ዙር አገራዊ ምርጫ የፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ አግኝተው ነበር። የምክር ቤት አባል ሳሉ የሚመሩት ፓርቲ ኦብኮ ጠቅላላ ጉባኤ በምዝበራና በአምባገነንነት ክስ ከሊቀመነበርነት አነሳቸው። ዶክተሩ በዚህ ከአመራርነት ያነሳቸው ፓርቲ ውስጥ ከመቀጠል ይልቅ የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግሬስ (ኦሕኮ) የተሰኘ ፓርቲ መስርተው በሊቀ መንበርነት ቀጥለዋል። ጥቂት የኦብኮ አባላትን የያዘው ኦህኮ የህብረት አባል ሆኖ ቀጠለ። የፓርቲዎች ስብስብ የሆነው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ሲመሰረት ከህብረት ጋር መድረክን ተቀላቀሉ። ኦሕኮ በመድረክ ውስጥ እያለ ከሌላ የመድረክ አባል – የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ጋር ተቀላቅሎ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ)ን መሰረተ። አሁን ዶ/ር መረራ ኦፌኮን ይዘው ነው መድረክ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት። የኦፌኮ ሊቀ መንበር ሲሆኑ የመድረክ ደግሞ ምክትል ሊቀ መንበር ናቸው። ላለፉት ሁለት አስርት አመታት እያረፉ አንዴ ሊቀ መንበር ሌላ ጊዜ ደግሞ ምክትል ሊቀ መንበር በመሆን “ሊቀ መንበር” የሚለው ማንጠልጠያ ሳይለያቸው እዚህ ደርሰዋል።
የዶ/ር መረራ የፖለቲካ ህይወት በወታደራዊው ደርግ ወቅት የሚጀምር ነው። በወቅቱ የወታደራዊው ደርግ ቀኝ እጅ የነበረውና ቀይ ሽብር የተባለውን የግድያ ዘመቻ በዋናነት የመራው የመላው ኢትዮጵያ  ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) አባል ሆነው መስራታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። መኢሶን በመጨረሻ እንደምርኩዙ ሲያየው ከነበረው ወታደራዊ ቡድን ጋር ተጋጨና ዶ/ር መረራም ለእስር ተዳረጉ። ዶ/ር መረራ በዚህ አኳኋን በፓርቲያቸው መኢሶን ሲዋከቡና ሲሳደዱ ከነበሩ፤ በመጨረሻም እስር ቤት ከተወረወሩ ኢህአፓዎች ጋር እስርን ቀመሱ። ሰሞኑን ባልተለመደ ሁኔታ የሚወራው የዶ/ር መረራ በወታደራዊው ደርግ ስርአት የመታሰር ጉዳይ በአጭሩ ይህን ይመስላል።
ዶ/ር መረራ ከደርግ መውደቅ በኋላ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በተረጋጋጠው የአመለካካት፤ የመደራጀት፤ አመለካከትንና ሃሳብን የመግለጽ፤ የማራመድ፤ ለመንግስት ስልጣን የመፎካከር መብትና ነጻነት በመጠቀም አይነግብ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ለመሆን በቅተዋል። ዶ/ር መረራ ምንም ሳይፈሩና ሳይሰስቱ እንደመጣላቸው በሚሰነዝሯቸው ቧልት አዘል ትችቶች ይታወቃሉ። ዶ/ር መረራ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተረጋገጠውን መብትና ነጻነት አጣጥመው ከተጠቀሙ ፖለቲከኞች  መካከል ቀዳሚው ናቸው። እንዲያውም የመብትና የነጻነትን ገደብ እያለፉም የሚዘባርቁባቸው ጊዜዎች ነበሩ። የመብትና የነጻነት ገደብን ተሻግረው ሕግ የመተላለፍ ድርጊት ሲፈጽሙም በአብዛኛው በዝምታ ነው የታለፉት፤ በዚህ ሁኔታ ግር የተሰኙ ኢትዮጵያውያን ዶ/ር መረራ ኢህአዴግ ሳይሆኑ አይቀሩም፤ በአገሪቱ ዴሞክራሲ አለ ለማስባል ያስቀመጣቸው ናቸው፤ እስከማለት የደረሱበት ሁኔታ መኖሩ ይታወቃል።  
ከወራት በፊት በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ሁከት አይሎ በነበረበት ወቅት ወደአሜሪካ ተጉዘው ኦሮሚያ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ሁከት አዘል ተቃውሞ በመምራት ፓርቲያቸው የበላይ ድርሻ እንዳለው በይፋ ተናግረዋል። የኦነግ አባላትና ደጋፊዎች በተገኙበት ቦታ ከኤርትራው ጉዳይ አስፈፃሚ ግንቦት 7 መስራችና መሪ ብርሃኑ ነጋ ጋር ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸውም ይታወቃል። እነዚህ እንግዲህ የቅርብ ጊዜዎቹ ናቸው። ዶ/ር መረራ እነዚህን ሁሉ በሕግ መተላላፍ ሊያስጠረጥሩ የሚችሉ ድርጊቶች እየፈጸሙ በዝምታ መታለፋቸው ነው ብዙዎችን ግራ ያጋባው፤ በዝምታ የመታለፋቸው ምስጢር ካልገባቸው አንዱ ብሆንም፤ የኢፌዴሪ መንግስት እንዳላየና እንዳልሰማ መሆን የመረጠው ሰላማዊ ተቃውሞ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች እንዳይሸማቀቁ በማሰብ ይመስለኛል።
ያም ሆነ ይህ፤ ዶ/ር መረራ አሁን በቁጥጥር ስር ውለዋል፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ ወንጀል ተጠርጠረው፤ ኮማንድ ፖስቱ ዶ/ር መረራ በቁጥጥር ስር የዋሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ መመሪያ ቁጥር አንድ አንቀጽ 2 ላይ የተመለከተውን መመሪያ ተላልፈዋል በሚል ተጠርጥረው መሆኑን አስታውቋል። 
ይህ አንቀጽ፤ 
ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግ
በሽብር ከተሰየሙ ድርጅቶችና ከፀረ ሰላም ቡድኖች ጋር ማናቸውንም ግንኙነት ማድረግ፣
የአሽባሪ ድርጅቶችን የተለያዩ ጽሑፎች መያዝ፤ ማሰራጨት፣ ዓርማቸውን መያዝ ወይም ማስተዋወቅ፣
የቴሌቪዥን ወይም የሬድዮ ፕሮግራምን መከታተል፣ የኢሳት፣ የኦ.ኤም.ኤን. እና የመሳሰሉትን የሽብርተኛ ድርጅቶች ሚዲያዎችን ማሳየት፣ መከታተልና ሪፖርት ማድረግ የተከለከለ ነው። ይላል።
ዶ/ር መረራ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጁ ቡድኖች ጋር በመገናኘት ወንጀል እንዲጠረጠሩ ያደረጋቸው በቤልጂየም ብራስልስ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል የሆኑት አና ጎሜዝ ኢትዮጵያን በተመለከተ ተወያይቶ ሎቢ ማድረግ የሚያስችላቸው አቋም ለመያዝ በጠሩት ስብሰባ ላይ በሽብርተኝነት ከተፈረጀውና ከኤርትራ መንግስት ጋር በመተባበር በይፋ በኢትዮጵያ ላይ የጦርነትና የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ካወጀው የግንቦተ 7 መስራችና መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ተገናኝተው በመምከራቸው ነው።
ዶ/ር መረራ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ በምክትል ሊቀ መንበርነት የሚመሩት መድረክ መግለጫ አውጥቷል፤ ህዳር 29/ 2009 ዓ.ም. የዚህ ጽሁፍ ትኩረት መድረክ በመግለጫው ላይ ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል አንኳር በሆኑት ላይ አስተያየት መስጠት ነው። የመድረክ መግለጫ፣ 
ዶ/ር መረራ በቅርቡ ከአውሮፓ ህብረት ፓርላማ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ለፓርቲያቸው የዲፕሎማሲ ስራ ወደቤልጂየም ብራስልስ ተጉዘው ነበር። በዚያም ለአውሮፓ ፓርላማ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ገለጻ ማድረጋቸውን እንደወንጀል በመቁጠር ‘ከሽብርተኞች ጋር ተገናኙ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጣሱ ወዘተ’ በሚሉ ሰንካላ ሰበቦች መንግስት ለእስር ዳርጓቸዋል። በመድረክ ግንዛቤ አንድ የህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ በሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ገለጻ ማድረግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ክልከላ አይጥልበትም። መድረክ ከሽብርተኞች ጋር ተገናኘ ስለተባለውም አንድ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ቀርቶ፣ በሰንበቴ ማህበር ስብሰባዎች እንኳን መቀመጫ ለእንግዳ የሚሰጠው በአዘጋጁ እንጂ በተጠራው እንግዳ አግባብ አለመሆኑ ይታወቃል። ይላል።
የመድረክ መግለጫ ዶ/ር መረራ በብራስልስ የተገኙት በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ጥሪ ተደርጎላቸው መሆኑን ይናገራል። ይህ ግን ስህተት ነው። በቅድሚያ የአውሮፓ ህብረት የመንግስታት ማህበር ነው። ይፋዊ ግንኙነት የሚያደርገው ከመንግስታት ጋር ነው። ምንም እንኳን የአውሮፓ ህብረት፤ የአውሮፓ አገራት መንግስታትን በአባልነት ያቀፈ ቢሆንም ከዚህ ውጭ ካሉ መንግስታትም ጋር ግንኙነት መስርቷል። ኢትዮጵያ ከህብረቱ ጋር ግንኙነት ከመሰረቱ አገራት አንዷ ነች። የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ በኤምባሲ ደረጃ ተጠሪ አለው። ኢትዮጵያም በአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ወክላለች። የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያን በተመለከተ ግንኙነት የሚያደርገው ከመንግስትና መንግስት ከወከለው አምባሳደር ጋር ነው። የህብረቱ ፓርላማም የህብረቱ አካል በመሆኑ ከዚህ ውጭ አይደለም።
የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ግን ለሚወግኑለት ወይም በገንዘብ ለቀጠራቸው አካል የሎቢ ስራ ለመስራት ከተለያዩ አካላት ጋር የሚገናኙበት አግባብ አለ። ዶ/ር መረራ የተገኙበት ስብሰባ በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ የተጠራ ሳይሆን፤ በኢፌዴሪ መንግስት ላይ የመረረ ጥላቻ ያላቸው የህብረቱ ፓርላማ አባል የሆኑት አና ጎሜዝ በኢፌደሬ መንግስት ላይ የተቃውሞ ሎቢ ለማሰማት የጠሩት ነው። እናም መድረክ ዶ/ር መረራ የአውሮፓ ህብረት በጠራው ስብሰባ ላይ ስለተገኙ . . . ብሎ ያወራው የተሳሳተ ነው።
በዚህ በአና ጎሜዝ ስብሰባ ላይ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የፈረጀው ግንቦት 7 የተባለ ቡድን መስራችና መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ተገኝተዋል። ስብሰባው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ፤ በተለይ በስልጣን ላይ ያለው የሕዝብ ውክልና ያለው መንግስት ተወግዶ የሽግግር መንግስት በሚመሰረትበት ጉዳይ ላይ የመከረና ውሳኔ ያሳለፈ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። እናም ዶ/ር መረራ የተጠረጠሩት በአሸባሪነት ከተፈረጀ ቡድን ጋር በአንድ ሸንጎ ተቀምጠው የሕዝብ ውክልና ያለው መንግስት በሚወገድበት ሁኔታ ላይ መክረዋል በሚል ነው።
አና ጎመዝ የተባሉት ፖርቹጋላዊት የኢፌዴሪን መንግስት ሊያናጋ ይችላል ብለው የገመቱትን ነገር ሲያገኙ በአሸባሪነት የተፈረጁ ቡድኖችን እየጠሩ ሲያወያዩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።  ዲስምብር 1 ቀን 2015  በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ላይ ለመወያየት በሚል የግንቦት 7 መሪ ብርሃኑ ነጋና ጥቂት ወዳጆቻቸው የተገኙበት ስብሰባ ጠርተው ነበር። ታዲያ በወቅቱ  ኢሳት የተሰኘው የኤርትራ ቴሌቪዥን እና የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም ይህን ስብሰባ መድረክ በሰሞኑ መግለጫው እንዳለው ሁሉ “የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ የጠራው ስብሰባ” እያሉ ነበር የዘገቡት። 
ይሁን እንጂ፤ ይህ ስብሰባ  የአውሮፓ ህብረት እውቅና ያልነበረው አና ጎሜዝ በግል ያዘጋጁት ነበር። ይህንንም የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ወዲያውኑ ባወጣው መግለጫ  አረጋግጧል። የአውሮፓ ህብረት ቃል አቀባይና  የፕሬስ ክፍል ዋና ኃላፊ ማርጆሪያ ቫን ዳም ባሮክ በወቅቱ በአሜሪካ ለሚገኝ አንድ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ በጠረጴዛ ዙሪያ የተካሄደው ውይይት፤ አና ጎሜዝ በተሰኘች የአወሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል በግል የተዘጋጀ፤ ይፋዊ የፓርላማው ሁነት ያልሆነ ነው። ስብሰባውን የማካሄድ ተነሳሸነት የአና ጎሜዘ የግል ጉዳይ ነው ብለው እንደነበረ ይታወሳል። መድረክ በሰሞኑ መግለጫው የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ስብሰባ ብሎ የጠቀሰው ዶ/ር መረራ የተገኙበትም ስብሰባ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው።
የመድረክ መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ገለጻ ማድረግን አይከለክልም ይላል። እርግጥ ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይህን አይከለክል ይሆናል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከወጣ በኋላ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በተካሄደና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባዘጋጀው፤ ዶ/ር መረራም በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ላይ አንዱ የውይይት ጽሁፍ አቅራቢ የአንጋፋው ተቃዋሚ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) አመራር የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው መሆናቸው ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል። ዶ/ር መረራ የተገኙበት አና ጎሜዝ የጠሩት ስብሰባ ግን አሸባሪዎች የተሳተፉበትና የሕዝብ ውክልና ያለውን የኢፌዴሪን መንግስት በማስወገድ የሽግግር መንግስት ስለመመስረት የተዶለተበት መሆኑ ነው የሚታወቀው፤ ይህ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ባይኖር በጸረ ሽብርተኝነት ሕጉ በወንጀል የሚያስጠረጥር ነው። እናም ጉዳዩ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ገለጻ የማድረግ ያለማድረግ ጉዳይ አይደለም። ከአሸባሪ ጋር ተወያይቶ አቋም የመያዝ ጉዳይ ነው። 
የመድረክ መግለጫ ዶ/ር መረራ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ከብርሃኑ ነጋ ጋር እንዳጋጣሚ ጎን ለጎን መቀመጣቸውን መነሻ ያደረገ ብቻ እንደሆነ አድርጎ ነው ያቀረበው፤ ይህም ትክክል አይደለም። መረጃዎች የሚጠቁሙት ተወያይተው ውሳኔ ማሳለፋቸውን ነው። በዚህ ላይ ዶ/ር መረራ ሸንጎው ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀ ቡድን መሪ ወይም ተወካይ መኖሩን ሲያውቁ ከአሸባሪ ጋር ተወያይቶ የጋራ አቋም መያዝ በጸረ ሽብርተኝነት ሕጉ፤ እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተከለከለ በመሆኑ፤ ሕግ ደግሞ በማንኛውም ሁኔታ መከበር ስላለበት ራሳቸውን ከስብሰባው ማግለል ነበረባቸው። ሕጎቹን ባያምኑባቸውም ሕግ የሚያደርጋቸው የእርሳቸው መቀበል ወይም አለመቀበል ስላልሆነ የህግ የበላይነትን መርህ ማክበር ነበረባቸው።
መድረክ በመግለጫው ያነሳው ሌላው ጉዳይ፤-
መድረክ ከኢህአዴግ ጋር በተደጋጋሚ ባካሄዳቸው ድርድሮች ‘መንግስት ሽብርተኛ ከሚላቸው ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግ ማለት ስምምነት ተፈራርሞ ድርጅታዊ ቁርጠኝነት መፍጠር ማለት ነው’ በሚል መግባባት ላይ ተደርሷል። ስለሆነም የዶ/ር መረራ እስራት በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ድንጋጌና መድረክ ከገዢው ፓርቲ ጋር ከደረሰበት የጋራ መግባባት ውጭ ነው። የሚል ነው።
ይህ በመድረክ መግለጫ ላይ የሰፈረው ጉዳይ ብዙዎችን አስገርሟል። አስገራሚ ያደረገው መድረክ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ አንዴም ሳያባራ መንግስት በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ እንወያይ ተብሎ እምቢ አለ በማለት ሲያብጠለጥለው መቆየቱ ነው። መድረክ ከመንግስት ጋር መወያያቱን ሲነግረን ይህ የመጀመሪያው ነው። ሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ጉዳይ ላይ ከሚመክሩበት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውጭ መንግስት መድረክን በተናጥል ማነጋጋሩ ሰበር ዜና ነው። መድረክ ከሌሎች በተለየ ይህን እድል እንዲያገኝ መደረጉ ተገቢ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ መንግስት የሰላማዊ ፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያለውን ልባዊ ፍላጎት ማመላከቱን ግን መካድ አይቻልም።
ያም ሆነ ይህ፤ በቅድሚያ መድረክ ከመንግስት ጋር ባካሄደው ውይይት የሚደርስበት ማንኛውም ስምምነት ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥቱን መሰረት በማድረግ የወጡ ሕጎችን የሚጻረር ከሆነ ተቀባይነት አይኖረውም። በሌላ በኩል፤ እስካሁን ባለው መረጃ ዶ/ር መረራ የተጠረጠሩት በአና ጎሜዝ ሰንበቴ ላይ ተጋብዘው  ከግንቦት 7 መሪ ጋር በአንድ አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጠዋል በሚል ሳይሆን፤ ተወያይተው በጋራ ውሳኔ አሳልፈዋል በሚል ወንጀል በመሆኑ ሁኔታው መድረክ ከመንግስት ጋር ተስማማሁበት የሚለውን ከሽብርተኝነት ጋር ግንኙነት ማድረግ ማለት ስምምነት ፈጽሞ ድርጅታዊ ቁርጠኝነት መፍጠር ነው፤ ከሚለው ጋር ይጣጣማል። የውይይቱን ይዘትና የስምምነቱን ምንነት በፍርድ ሂደቱ  የምናየው በመሆኑ እንጠብቅ፤ 
መድረክ ገና ያልተሰማውን የዶ/ር መረራ የፍርድ ሂደት ችላ በሎ በመግለጫው  ዶ/ር መረራ በአስቸኳይ ይፈቱ በሚል ያሳለፈው ማሳሰቢያም የሕግ የበላይነትን የሚጻረር ነው። እርግጥ የፍርድ ሂደቱ ለሕዝብ ግልጽ እንዲሆን መጠየቅ ይችላል። በወንጀል ተጠርጥሮ ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ላይ ያለን ሰው መንግስት በዳኝነት ስራ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ፍታ ወይም እሰር የማለት ስልጣን የሌለው መሆኑም መታወስ ነበረበት። ይህን ማድረግ የፍርድ ቤቶችን ገለልተኛነት እና የህግ የበላይነት መርህን ይጻረራል።
በአጠቃላይ መድረክ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፈ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉትን ዶ/ር መረራን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ከነባራዊው እውነታ ጋር አራምባና ቆቦ ነው። የሕግ የበላይነትን መርህም ይጻረራል። እናም ከእውነታ የተጣላ አቋም ነው ማለት ይቻላል።