ሙስናና ኪራይ ሰባሳቢነት ለሀገር ሰላምና ለብሄራዊ ደህንነት ትልቅ አደጋ ነው፡፡ የሕዝብን ሰላማዊ ኑሮና መረጋጋት ያናጋል፡፡ ሕዝባዊ ቁጣና ተቃውሞ ያስነሳል፡፡ የፍትህ መረገጥ የዜጎች መበደል የመንግስትና የህዝብ ሀብት ዘረፋ በስልጣን መባለግና ብልሹነት እያደር እያገነገነ ሲሄድ ለህብም ለመንግስትም አስቸጋሪ የሆነ ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ ኢህአዴግ ይህን ደረቅ እውነት በውል በመረዳቱ ነው በሙሰኞችና በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ ምህረት የለሽ ትግልና እርምጃ የጀመረው፡፡
ኢሕአዴግ አስቀድሞ በለየውና ውሳኔ ባሳረፈበት ስር የሰደደሬሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ላይ ፈጥኖ እርምጃ አለመውሰዱ ያስከተለውን ያልታሰበ መጠነ ሰፊ ችግር የሰላም መደፍረስና መናጋት አይቶታል፡፡ ይህ አይነቱ አደገኛ ክስተት ዳግም ተመልሶ እንዳይመጣ ያለው ብቸኛ አማራጭ በሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ በተጨባጭ ማስረጃና መረጃ ተመርኩዞ ለሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ተገቢ አርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩ ይበረታታል፡፡
የተሰጣቸውን ሕዝባዊና መንግስታዊ የኃላፊነት ወንበር በመጠቀም ከታችኛው ቀበሌና ወረዳ በመጀመር ክፍለከተማና ክልል እስከ ፌደራሉ መንግስት ቢሮ ድረስ የኪራይ ሰብሳቢውና የሙሰኛው መረብ ተዘርግቶ በጥቅም ትስስር ተቆራኝተው በማን አለብኝነት ሕዝብን ያስመረሩና ያንገፈገፉትን ግለሰቦች በየመንግስታዊ መዋቅሩ ጭምር ሰፊ ግምገማ እየተደረገ እንደጥፋታቸው ቅለትና ክብደት እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ናቸው፡፡
የዘንድሮው ግምገማ መራርና ከባድ መሆኑን ተሳታፊዎቹ ይናገራሉ፡፡አባሉን የማበጠር ዘመቻም ነው የተያዘው፡፡ ኢህአዴግ የተተቸው የተነቀፈው የተወቀሰው ሀላፊነት በሰጣቸውና በአባልነት ባቀፋቸው ሰዎች አማካኝነት የተነሳ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ነው አባላቱ ላይ መረር ያለ ግምገማ በማካሄድ ላይ የሚገኘው፡፡ገና በገፍ የሰበሰበውን ማራገፍና በጥራት ላይ የተመሰረተ ብቃትን ሕዝባዊ አገልጋነትን መርህ ያደረገ አባልነትን አስገዳኝ ቢያደርግ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል፡፡
ከሕዝቡ ጋር የሚገናኘው ዋናው ሀይል ታች ያለው አባል ነው፡፡ የአባላት ዲሲፕሊን፤ የስነምግባርና የእውቀት ብቃት ድርጅቱን የሚያስመሰግን የሚያስከብር መሆን ሲገባው ክፉኛ የሚያስወቅስ ሁኖ የተገኘው፡፡ ኢህአዴግ ይህን በመሰረታዊ ደረጃ ያለ ግድፈት ለማረም መንቀሳቀሱ ተገቢና የሚደገፍ ነው፡፡በአባላቱ ዘንድ የፖለቲካ እውቀትና ብስለት ችግርም ገዝፎ ይታያል፡፡ ይህንንም በአዲስ መልክ መገንባት ማነጽ ማስተማር ይጠበቅበታል፡፡ አባሉ ሙሰኛነትንና ኪራይ ሰብሳቢነትን አድርባይነትን በጥቅም መደለልን ጸንቶ ሊዋጋ የሚችለው የጸና ፖለቲካዊ ብቃትና እውቀት ሲኖረው ብቻ ነው፡፡
የጥልቀታዊው ተሀድሶ የእርምትና የማስተካከያ እርምጃዎች ጅምር በየደረጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡መሰረታዊ አላማና ግቡ የሕዝብ ጥያቄዎችን መመለስና በመንግስታዊ አገልግሎቱ እርካታ የሚያገኝበትን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ ጥልቀታዊው ተሀድሶ ዋና አላማው በሀገሪቱ የተጀመረውን ልማት ስርነቀል በሆነ ለውጥ ማስቀጠል የላቀ የኢኮኖሚ እድገት ማማ ላይ እንድትደርስ ማድረግ ነው፡፡
የተጀመረው ጥልቀታዊ ተሀድሶ የህዝቡን ጥያቄ የሚመልስ ሲሆን ባለቤቱም ህዝቡ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር መንግስት ጥልቀታዊ ተሀድሶ በማድረግ ብዙ ነገሮችን እንደሚለውጥ የገባውን ቃል በተግባር እያሳየ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡በእርግጥ ማንኛውም አይነት ለውጥ በአንድ ግዜ በአንድ ጀምበር የተፈለገበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ለማለት አይቻልም፡፡ግዜና ሂደት አመቺ ሁኔታንም ይጠይቃል፡፡የስኬቱ ፍጥነትና ግለት የሚወሰነው ሕዝቡ በሚያደርገው ንቁ ተሳትፎ ብቻ ነው፡፡
የተሀድሶው መድረክ ሕዝቡን በሰፊው በሙሉ ነጻነት ሀሳቡን በሚገልጽበት ሁኔታ አሳታፊ መሆኑ በየቦታው በተዘጋጁት መድረኮች ዲሞክራሲያዊነት ግልጽነትና ነጻነት ማረጋገጥ ተችሎአል፡፡በጥልቀት መታደስ የዲሞክራሲ እሴቶችና ባህል ግንባታ አካል ሲሆን የበለጠና የደረጀ ልማትና እድገትን ለማስቀጠል የሚያስችል አቅም በጎለበተ መልኩ መገንባት መሆኑም መታወቅ አለበት፡፡
ዋነኛው የጥልቀታዊው ተሀድሶ ሞተር ሁኖ የሚያገለግለው የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ በተጨባጭ ማምጣት መቻል ነው፡፡ፈጣን ሕዝባዊ አገልግሎት መስጠት መልካም አስተዳደርን ማስፈን ሕዝባዊ እምነትን መገንባት መቻልና መብቃት ነው፡፡የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ከሁሉም ወገን ይጠበቃል፡፡ በኃላፊነት ተሰማርተው ከሚገኙትም ሆነ ከሕብረተሰቡ በሰፊው ይጠበቃል፡፡
በተግባር የተሻለ ስራ ለመስራት መብቃት ሕዝባዊ አገልጋይነትን በቅንነትና በታማኝነት መንፈስ ማስፈን የሚቻለው ከፍተኛ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ሲደረስ ብቻ ነው፡፡የመንግስትና ፓርቲ አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ ሰራተኛውም በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ሲያልፍ ብርቱና ታታሪ የሆነ ሕዛባዊ አገልጋይነትን በመላበስ የሚጠበቅበትን ድርሻና ሀላፊነት በብቃት ለመወጣት ያስችለዋል፡፡
በየቦታው በሰፊው የተዘረጉት መድረኮች ግልጽነት ዲሞክራሲያዊነት የሰፈነባቸው በመሆኑ ሰራተኛው በእስከአሁኑ እንደታየው በግልጽ ሀሳቡን በነጻነት በማንሸራሸር ላይ ይገኛል፡፡ይሀው ጠንካራ መንፈስ ጎልብቶ መቀጠል እንዳለበት ይታመናል፡፡
ሰራተኛው የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ሰፊና የተለያዩ ናቸው፡፡ጥያቄአችንን ሰምታችሁ ትወስዳላችሁ፤ተናገሩም ትሉናላችሁ ነገር ግን በበርካታ አመታት ተሞክሮ እንዳየነው ምንም ተጨባጭ ውጤት የሚያስገኝ ለውጥ አላመጣችሁም፡፡ለተወሰነ ግዜ ቅሬታ የቀረበበትን ሰው አንስታችሁ በቦታው ሌላ ሰው በማስቀመጥ የቀደመውን ወደ ሌላ ቦታ ታዛውራላችሁ ሌላ ቦታ ሄዶ ተመሳሳይ ችግር እንዲፈጥር ማበረታታት ነው፡፡በዚህ መልኩ ተሀድሶ ሊሆን አይችልም፡፡
ተናገሩ እያላችሁ የተናገሩትን በተለያየ ደረጃ የመኮርኮም የማስፈራራት ወይም ምክንያት ተፈልጎ ከስራ እንዲፈናቀሉ ሲደረጉ በተለያዩ አመታት አይተናል፡፡አንናገርም፡፡ተናገሩ እያላችሁ አታስጨንቁን፤ዝምታ ራሱ ከመናገር በላይ መሆኑን ማወቅ አለባችሁ፡፡ ተናጋሪዎች እየተለዩ የጥቃት ሰለባ ሲሆኑ በብዙ አጋጣሚ አስተውለናል፡፡ችግሩን ለግዜው ለማስተንፈስ የምትጠቀሙበት ዘዴና መንገድ ነው፡፡ማን ተናገረ፤ሰራተኛውን ማን ነው የሚያሳምጸው፤ወዘተ የሚሉ ክትትሎች በሰፊው ስላሉ ከመናገር ዝምታ ወርቅ መሆኑን ተምረናል የሚሉ የስጋትና የጥርጣሬ ሀሳቦችም በብዙ መድረኮች ተደምጠዋል፡፡እነዚህ ሀሳቦች ከስጋት የመነጩ ናቸው፡፡ተቀባይነትም የላቸውም፡፡መናገር ሀሳብን መግለጽ ለችግሮች መፍትሄ የማስገኘት አቅምም አለው፡፡
አብዛኛው ሰራተኛ በየመስሪያ ቤቱ የቀበሌ ነዋሪውም ቤቀበሌው ስብሰባ የተሀድሶ ወይይት መድረኮቹን በከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ እያደረገባቸው ይገኛል፡፡ችግሮችን በግልጽ ከማንሳትም አልፎ መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን ሀሳቦችም ይሰጣል፡፡
የተሀድሶው ንቅናቄ በኢህአዴግ ይጀመር እንጂ አራማጁ ከዳር የሚያደርሰው ባለቤቱ ሕዝብ ነው፡፡ሲነሱ የቆዩትን የተለያዩ ጥያቄዎች በተመለከተ በሰከነ ሁኔታ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መንግስትና ህዝብ በሂደት መልስ እንደሚያስገኙላቸው ይታመናል፡፡
ሁሉንም ጥያቄ በአንድ ግዜ ለመመለስ የማይቻል ሲሆን በግዜ ሂደት ግን ምላሽ ያገኛሉ፡፡ ሙስናን በተመለከተ መንግስት በተጠርጣሪዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ይሄንኑ ጉዳይ ብቻ የሚከታተል የሚመረምር በፖሊስ ኮሚሽን ስር የሆነ ልዩ የምርመራ ቢሮ የአሜሪካውን ኤፍቢአይ የመሰለ መቋቋሙን ለመገናኛ ብዙሀን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙስናን ለመዋጋት የተቋቋመው የምርመራ ቢሮ በሰው ኃይልና በቁሳቁስ እንዲጠናከር መደረጉን፤ጥቆማ ሲኖር በቂ ምርመራ ለማካሄድ የሚያስችል ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑን፤ሕዝቡ በመረጃ ቴክኖሎጂ ጥቆማ ለማቅረብ የሚያስችለው አሰራር መዘርጋቱንም ገልጸዋል፡፡ማንኛውም ዜጋ ወይም ሚዲያ በቂ መረጃ ይዞ ከቀረበ በየትኛውም የስልጣን እርከን ያለ ግለሰብ ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል፡፡
ጥፋት በፈጸመ ሰው ላይ ከስልጣን የማስወገድ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ በቂ ማስረጃ ከተገኘም በህግ ተጠያቂ ይሆናል ሲሉ የተናገሩት ጠ/ሚር ኃይለማርያም ኢህአዴግ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ መለኮሱን የመንግስት ስልጣን በሌብነትና በሙስና መልክ የሚገለጽ የላይኛው ጫፍ የሆነ አተያይ መኖሩን አስምረውበታል፡፡አመራሩ የያዘውን ስልጣን ለሕዝብ ጥቅም ማዋል ሲገባው የግል ኑሮን ለማሻሻል የተንደላቀቀ ኑሮ ለመኖር የመሞከር ሁኔታ መታየቱንም አረጋግጠዋል፡፡
አመራሩ ለስራ ከመትጋት ይልቅ ባለጉዳይን በአግባቡ አለማስተናገድ፤ ቢሮ ክፍት ያለማድረግ የተለያዩ ጉዞዎችን የማብዛት የመሳሰሉ ችግሮች እንደሚታዩበት፤በቅርቡ ከስልጣን የተነሱት ሰዎች ከነዚህ ባንዱ ተገምግመው እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙስና ውስብስብ ቢሆንም ከስልጣን የወጡና አሁንም በስልጣን ላይ ባሉ አመራሮች ጥናትን መሰረት ያደረገ ክስ እንደሚመሰረት አስገንዝበዋል ፡፡,
ሕዝቡ በጸረ- ሙስና ትግሉ በስፋትና በጥልቀት የሚሳተፍበትን ሁኔታ ማመቻቸት ማስረጃዎችን ለማግኘት ወሳኝ መሆኑን፤የመንግስት ሀብትና ንብረት ይፋ የሚሆንበት ሁኔታ በመመቻቸቱ ማንኛውም ግለሰብ በሙስና ያፈራው በቤተሰብ በዘመድ የተያዘ ንብረትና ሀብት ካለ እንዲጠቁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡
በመላው ሀገሪቱ በመካሄድ ላይ በሚገኘው ጥልቀታዊ የተሀድሶ እርምጃና ንቅናቄ በአማራ ክልል በተደረገው ሰፊ ግምገማ 997 አመራሮችን ከኃላፊነታቸው የማንሳትና የማስጠንቀቂያ እርምጃ መሰጠቱን የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ ይፋ አድርገዋል፡፡
በጥልቅ ተሃድሶው ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ አመራሮች ተገምግመው ተለይተዋል፡፡ በተደረገው የማጥራት ግምገማ 748ቱ ከነበሩበት የኃላፊነት ቦታ ተነስተው ዝቅ ብለው ሲመደቡ 249ኙ አመራሮች በማስጠንቀቂያ ታልፈዋል፡፡በተጨማሪም በሙስና፣ በኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርና በብልሹ አሰራር ተሳትፈዋል በሚል ከሕብረተሰቡ ጥቆማ የቀረበባቸው 15 ከፍተኛ አመራሮች የሚገኝባቸው 240 አመራሮች በአጣሪ ኮሚቴዎች ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከሰጡት መግለጫ ለመረዳት ተችሎአል፡፡
ጉዳያቸው ተጣርቶ ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙት አመራሮች ወደ ሕግ ቀርበው የሚጠየቁ ሲሆን በመልሶ የማደራጀት ስራ ከ700 በላይ አዲስ አመራሮች ተተክተዋል፡፡ብቃት ውጤታማነት ተገቢነትን መሰረት አድርጎ አዲስ የተዋቀረው አመራር የክልሉን ልማት ለማፋጠንና ለመስቀጠል ጠንክሮ መስራት ያለበት መሆኑን ሀላፊው ተናግረዋል፡፡ የተሃድሶው ግምገማ ሂደት አባላቱንና ሕብረተሰቡን በማሳተፍ መካሄዱ ጥንካሬና ድክመትን ለይቶ በማንሳት የበለጠ ተግቶ ሳያሰልስ እንዲታገል ጉልህ ድርሻ ማበርከቱም ተገልጾአል፡፡
በግምገማው ሂደት የአስተሳሰብ ግልፅነትና የገጠሙ ችግሮችን በልካቸው በመረዳት፤ የችግሮች መነሻ ምን እንደሆነም የጋራ መግባባት እንዲፈጠር ማስቻሉን አብራርተዋል፡፡ በክልሉ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ድህነትን ለመቅረፍ መንግስትና ሕዝብ እጅና ጓንት ሆነው እንደሚሰሩም አስታውቀዋል፡፡'
በቀጣይ ስድስት ወራት የሕዝቡን አንገብጋቢ ችግሮች ለይቶ ለመፍታት ለተፈጥሮ ሃብት፤ ለትምህርት፤ለጤናና ሌሎች የልማት ስራዎች ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ አቅጣጫ መቀመጡን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡በጥልቀት የመታደስ ሂደቱ በቀበሌ ደረጃ የሚቀጥል መሆኑን በአማራ ክልል ባለፉት ወራት ከ7ሺህ 100 በላይ አመራሮች የማጥራት ስራ ከተከናወነባቸው ውስጥ 5ሺህ 595ቱ ባሉበት እንዲቀጥሉ መደረጉን ለማወቅ ተችሎአል፡፡