የየትኛውም ሀገር ሥር ነቀል የማኅበራዊ ለውጥ እና የምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት የታሪክ ሂደት ውስጥ መላው ኅብረተሰብ እንደ የቁርጥ ቀን ልጆቹ ቆጥሮ ‹‹ኑሩልኝ ክበሩልኝ ›› የሚሏቸው ጥቂት ብቅዬ ዜጎች ይፈጠራሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ ለአብነት ያህል የምዕራብ አውሮፓ አብዛኛዎቹ ሀገራት እነርሱ ‹‹የጨለማው ዘመን ›› ብለው ከሚጠሩት ፈርጀ ብዙ የድህነት እና የኋላቀርነት ታሪካቸው ለመውጣት ያስቻላቸውን የኢንደስትሪ አብዮት በማካሄድ ረገድ እጅጉን የላቀ የፋና ወጊነት ሚና ለተጫወቱ ዜጎቻቸው ‹‹ ማን ኦፍ ዘ ሬነይሰንስ ›› ወይም ደግሞ ‹‹የህዳሴው ዘመን ሰው›› የሚል የክብር ስም እየሰጡ ያንቆለጳጵሷቸው እንደነበር ነው ድርሳት ከመዘገቡት መረጃ ላይ መረዳት የሚቻለው፡፡
ከዚሁ የምዕራቡ ዓለም ባለፀጋ ሀገራት ሕዝቦች አንድ ወቅት ላይ የሞት ሽረት ትግል በጠየቃቸው ውጣውረድ ተጋፍጠው እንዳለፉት ከሚነገርለት እና በተለይም ደግሞ “የአውሮፓውያን ወርቃማ ዘመን መባቻ” እየተባለ ከሚጠቀሰው የታሪክ ምዕራፍ ጋር በተያያዘ መልኩ ስማቸው ተደጋግሞ የሚወሳ የአህጉሩ የህዳሴ ጉዞ ግንባር ቀደም ሊቃውንት (የለውጥ ሐዋሪያት) እነማን እንደሆኑ ለአሁኑ የፌስቡክ ዘመን ትውልድ መናገር አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም፤ እነ ጎልጉል (ጎግል)ን እና መሳል የመረጃ ምንጮችን ከፍቶ በማየት ብቻ ማረጋገጥ ይቻላልና ነው፡፡ ለማንኛውም ግን አንድ ቁልፍ ነጥብ ላይ ብንስማማ ጠቃሚ መስሎ ይሰማኛል፡፡
ስለዚህም፤በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኝ ሀገርን ሕዝቦች እንዲህ እንደኛ ሥር በሰደደ ድህነት እና ኋላቀርነት ምክንያት ከሚማቅቁበት የችጋር አዘቅት ለማውጣት ሲባል፤ በተካሄደ የማኅበራዊ ዕድገት እና ብልፅግና ንቅናቄ ውስጥ፤የፊተኛውን ረድፍ ይዘው በመሰለፍ ታሪክ የማይዘነጋው አዎንታዊ ሚና የሚጫወቱ ግንባር ቀደም የለውጥ ሐዋሪያት መኖናቸው እንደማይቀር ተገቢውን የጋራ ግንዛቤ መውሰድ ይጠበቅብናል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ ይህን ስልም ደግሞ፤እኛ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ብሔሮች፤ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አሁን ላይ እንደ አንድ ኅብረተሰብ እጅ ለእጅ ተያይዘን የምናካሂደውን ፈርጀ ብዙ የፀረ ድህነት ትግል፤ወይም የሕዳሴ ጉዞ በሚፈለገው ስፋትና ጥልቀት አጠናክረን እናስቀጥል ዘንድ፤እንደ ሀገር የቁርጥ ቀን ልጆቻችን አድርገን የምንወስዳቸው ጀግኖች አትሌቶቻችን፤ልማታዊ ጉዞውን በመሪ ተዋናይነት የማስተባበር ታሪካዊ ሚና በመጫወት ረገድ እያሳዩ ያሉትን ጅምር እንቅስቃሴ ሊገፉበት ይገባል ለማለት ፈልጌ ነው፡፡
ምክንያቱም፤የአትሌቲክስ ስፓርታችን፣ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በመላው የዓለም ኅብረተሰብ ዘንድ ይታወቁበት የነበረውን ከአስከፊው የድህነት ታሪካችን የሚመነጭ የረሀብ እና የተመፅዋችነት መጥፎ ገፅታ በመቀየር ረገድ ትርጉም ያለው አዎንታዊ ተፅእኖ ማሳደር የቻሉ ጀግኖችን፤ ወይም ደግሞ ብርቅዬ የቁርጥ ቀን ልጆቻችንን ያፈራንበት እንደ መሆኑ መጠን፤ እነዚሁ የዘርፉ ከዋክብት ዜጎቻችን፤ በስፓርታዊ ሙያቸው ካጎናፀፉን ክብር ባሻገር፤ የሀገራችንን የሕዳሴ ጉዞ ዳር ለማድረስ ሲባል የሚደረገውን ፈረጀ ብዙ ርብረብ ከማስተባበር አኳያም አሁን የጀመሩትን ጥረት ይበልጥ አጠናክረው ቢቀጥሉበት፤ የሀገር ወገናቸው ባለውለታነታቸውን የሚጨምር ተግባር ይሆናል ማለቴ ነው፡፡
ይልቁንም ደግሞ፤ በሀገራችን የአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ ውስጥ የተለየ ሥፍራ የሚያሳጣቸውን አዲስ ምዕራፍ በመክፈት እጅግ በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን የረጅም ርቀት ሯጮችን ለማፍራት ያስቻለንን አስገራሚ የመነቃቃት መንፈስ እንዲፈጠር እንዳደረጉ የተመሰከረላቸው፤ ሁለቱ የባርሴሎና ኦሎፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ጀግኖቻችን (ሻለቃ ኃይለ ገ/ስላሴ እና ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ) መጋቢት 24 ቀን 2009 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በሚገነባበት በጉባ ሸለቆ ተገኝተው፤ ለግድቡ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን 6ተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀውን በዓል ያከበሩበት አግባብ፤ታሪካዊ ሚናቸውን የሚመጥን ይዘት ያለው ሆኖ እንደተሰማኝ ነው በዚህ አጋጣሚ ልገልፅላቸው የምወደው፡፡ የሕዳሴ ጉዟችንን ፈርጀ ብዙ ገፅታ በሚወክል ግዝፈቱ ምክንያት ዓለም አቀፋዊ አድናቆትን ያተረፈልን ታላቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድባችን በሚገነባበት እጅግ በጣም ሞቃማታማ ሥፋራ የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድር እንዲካሄድ መደረጉም ለዚህ አስተያየቴ ሁነኛ ምክንያት እንደሆነኝ ይሰመርበት፡፡
በአጠቃላይ እኔ እንደምረዳው ከሆነ፤ በተለይም ጀግናው አትሌታችን ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን በፕሬዘዳንትነት እንዲመራው የተወሰነበት ምርጫ ምን ያህል ተገቢ እና ትክክለኛ እርምጃ የተወሰደበት እንደነበር ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ እንዴት ቢባልም፤ዘርፉ ያፈራቸው የአትሌቲክስ ስፓርት ታላላቅ ጀግኖቻችን በሙያቸው ያተረፉትን ዓለም አቀፋዊ ክብር እና ዝና እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፤ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ ከድህነት እና ከኋላቀርነት ጋር የሞት ሽረት ትግል የገጠመችበትን ፈርጀ ብዙ የሕዳሴ ጉዞ ዳር በማድረስ ረገድ ትርጉም ያለው አዎንታዊ ተፅእኖ እንዲያሳድሩ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርላቸው የአመራር አካል ያስፈልጋቸው እንደነበር ይታመናልና ነው፡፡
ስለሆነም፤ከዚህ አኳያ ሲታይ ብርቅየው የአትሌቲክስ ስፖርት ግንባር ቀደም ጀግናችን፤ሻለቃ ሃይሌ ገ/ስላሴ ፌዴሬሽኑን በፕሬዘዳንትነት የመምራት ዕድል እንዲገጥመው የተደረገበት ምርጫ ላይ ድምፅ የሰጡ ወገኖችን ጭምር የሚያስመሰግናቸውን ተገቢ ውሳኔ መወሰናቸው ነው ለኔ የሚሰማኝ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሃይሌ እንኳንስ የአትሌቲክስ ስፓርት ፌዴሬሽኑን በበላይነት እንዲመራ ዕድል ተሰጥቶትና እንደ አንድ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅናን ያተረፈ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለዚች ሀገር የልማት ጉዞ መፋጠን ይበጃል ያለውን ቅን ሃሳብ ከመለገስ ቦዝኖ እንደማያውቅ ስለሚታመን ነው፡፡
እንዲያውም እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፤ኃይሌ ገ/ስላሴን ያህል መላው የዓለም ማኅበረሰብ ጭምር “ኖር ክበር” የሚለው የኦሎፒክ እና የበርካታ ሀገር አቋራጭ ሩጫ ሪከርዶችን ሲሰባብር የኖረ የአትሌቲክስ ስፓርት ጀግና ፤ ፅንፈኝነት የተጠናወተውን የተቃውሞ ጎራ ፓለቲከኞችን አስተሳሰብ የሚያቀነቅኑ ወገኖች የሚያሳድሩት አሉታዊ ተፅዕኖ ምክንያት፤ የሚስተዋለውን ጭፍን ፍረጃ ከዕቁብ ሳይቆጥር፤ ለመላው የሀገሩ ብሔሮች፤ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣ ፈንታ ይበጃል ብሎ ያመነበትን የለውጥ ሂደት እንደሚደግፍ በግልፅ አቋሙን ከማንፀባረቅ አለመቆጠቡ፤በእርግጥም የታላቅ ስብዕና ባለቤት መሆኑን አጉልቶ የሚያመለክት ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳን ከባህር ማዶው አክራሪ ዲያስፖራዎች በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን የሳተላይት ሥርጭት አማካኝነት የሚዛመት አሸማቃቂ ፕሮፖጋንዳ፤ እስከ የሀገር ቤቱ የፌስቡክ ዘመን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ስም የማጥፋት ደባ በሚስተዋለው ጎጠኝነትን መሠረት ያደረገ ፍረጃ አቋም የማስቀየር ሙከራ ከሚቃጣባቸው ምግባረ መልካም ኢትዮጵያውያን ታዋቂ ሰዎች መካከል ኃይሌ አንዱ ቢሆንም፤ እርሱ ግን ለእጅ ጥምዘዛው የሚያመች ሰው አይመስልም፡፡
ስለዚህም በእኔ እምነት፤ ተወዳጁ የአትሌቲክ ስፖርት ጀግናችን ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ፤ ለትምክህት እና ለጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ አቀንቃኝ ፅንፈኛ ተቃዋሚ ቡድኖች ፈርጀ ብዙ ተፅዕኖ ሳይበገር፤ የሕዳሴው ዘመን ኢትዮጵያዊነትን ለማስቀጠል የሚደረገውን አጠቃላይ ጥረት ከልብ ሲደግፍ የሚስተዋል የቁርጥ ቀን ልጃችን ስለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ይህን ስል ግን ሌሎቹ የአትሌቲክስ ስፖርት ጀግኖቻችን ከእርሱ ጋር በሕዳሴ ጉዟችን የፊት ረድፍ ተሰልፈው፤ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የሚያሰኛቸውን አዎንታዊ ሚና በመጫወት ላይ መሆናቸውን ለመዘንጋት እየቃጣኝ አይደለም፡፡
ይልቅስ አትሌቲክስ ብቻም ሳይሆን፤ የእግር ኳስ እና የሌላው የስፖርት ዘርፍ ቤተሰብ ጭምር ለሀገራችን የሕዳሴ ጉዞ መሳካት ማሳየት የሚጠበቅበትን ግልፅ እና የማያሻማ አቋም በተለይም ከኃይሌ ገ/ስላሴ ሊማር ቢችል የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ፈልጌ ነው እርሱን በአርአያነት ማቅረቤ፡፡ እንጅማ ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉን እና አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያምን ጨምሮ፤ ሌሎችም ወጣት እና አንጋፋ የረጅም ርቀት ሯጮች ከኃይሌ ጎን ቆመው የየራሳቸውን ታሪካዊ ድርሻ በመወጣት ላይ እንደሚገኙ የሚካድ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለማንኛውም ግን፤ ሁሉም የአትሌቲክስ ስፖርት ጀግኖቻችን በሕዳሴው ጉዞ የፊት ረድፍ መሰለፋቸው የሚያከራክር ጉዳይ እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ በርካታ ተጨማሪ አስተዋፅዋቸውን ማንሳት አያዳግትም፡፡
ጀግኖቹ አትሌቶቻችን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የጥሮ ግሮ ማትረፍ ጉዞ ፈር የቀደዱ ባለውለታዎቻችን ተደርገው የሚወሰዱበት ዋነኛው ምክያት ደግሞ፤ ካለፈው የጨለማ ዘመን ታሪካችን የወረስነው ሥር የሰደደ ድህነት እና ኋላቀርነት ለተመፅዋችነት ዳርጎን አንገት በደፋንበት አጋጣሚ፤ የበለፀገውን ዓለም ሩጠው እየቀደሙ በማስደመም እና እንዲሁም የሀገራችን ሰንደቅ ዓላማም በየኦሎምፒኩ አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረገ ተደጋጋሚ ድል በመቀዳጀት ረገድ የተጫወቱት አዎንታዊ ሚና ነው ቢባል ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ከወንዶቹ ‹‹ይቻላል›› የሚል መርሕ እንዳለው የሚነገርለት ኃይሌ ገ/ስላሴ፤ ከሴቶቹ ደግሞ ፍልቅልቋ ደራርቱ ቱሉ በ1994ዓ.ም ስፔን ባርሴሎና ላይ በተካሄደው ኦሎምፒክ የከፈቱት የአዲሱ ኢትዮጵያዊ ትውልድ የአትሌቲክስ ስፖርት የድል ምዕራፍ፤ በእርግጥም ለዚች ሀገር ሕዝቦች ትርጉም ያለውን የመነቃቃት መንፈስ የፈጠረ እንደነበር ማስታወስ የሚከብድ አይመስለኝምና ነው ይህን ማለቴ፡፡
ሁለቱ አንጋፋ የአትሌቲክስ ስፖርት ግንባር ቀደም ጀግኖቻችን እነሆ አሁንም በኢትዮጵያ የሕዳሴ ጉዞ ከፊተኛው ረድፍ ተሰልፈው የፀረ ድህነት ትግሉን የድል አድራጊነት ችቦ ለተተኪዎቻቸው ሲያቀብሉ እያየናቸው ነው፡፡ ስለዚህ እኔም የመጣጥፌን ሃተታ የማጠቃልለው፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የወቅቱ ፕሬዘዳንት የሆነው ጀግናው አትሌታችን ኃይሌ ገ/ስላሴ መጋቢት 24 ቀን 2009ዓ.ም ጉባ ሸለቆ ላይ ተገኝቶ ለመገናኛ ብዙሃን ከሰጠው አስተያየት መካከል ቀንጭቤ በመጥቀስ ይሆናል፡፡ በነገራችን ላይ፤ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆነው ሌላው ጀግና አትሌታችን ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም እና ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉም በዕለቱ ጉባ ሸለቆ ለተገኙት የኢ.ብ.ኮ ጋዜጠኞች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሰጡት አስተያየት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ እኔ ለአብነት ያህል አንስቼ ለማስታወስ እና ለዚህ ጽሑፌ እንደግብዓት ለመጠቀም የፈለግሁት ከኃይሌ አስተያየት መካከል ጥቂት ነጥቦችን ነው…
ስለዚህ እርሱ ‹‹…እውነት ለመናገር እዚህ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እየተገነባበት ባለው ቦታ ሻይ ለማፍላት የሚያስችል ዓይነት በጣም ከባድ ሙቀት ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የፕሮጀክቱን ግንባታ ዳር ለማድረስ በመረባረብ ላይ የሚገኙት ወገኖቻችን ምን ያህል መስዋትነትን መክፈል የሚጠይቅ ታሪክ በመሥራት ላይ እንደሆኑ ይበልጥ የገባኝም አሁን ነው ማለት ይቻላል›› ሲል ጀምሮ ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ጋዜጠኞች በሰጠው ሰሞነኛ አስተያየት በተለይ ጉባ ሸለቆ ውስጥ ያለውን ኃይለኛ ሙቀት ተቋቁመው የግድቡን የግንባታ ሂደት ወደ መገባደጃው ምዕራፍ ሊያደርሱት የቻሉትን የልማት አርበኞች ከልቡ እንደሚያደንቅ ገልጿል፡፡
‹‹ይቅርታ አድግልኝና እኔ በግሌ የፕሮጀክቱ ግንባታ በሚካሄድበት ቦታ ያለውን በጣም ከባድ ሙቀት ተቋቁመው ግድቡን እዚህ ደረጃ ካደረሱ ሰዎች ጋር እራሴን ለማነፃፀር ስሞክር ባዶነት ነው የሚሰማኝ›› የሚል ከተለመደ ትህትናው የሚመነጭ ሀሳብ ያከለው ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ ምልዓተ ሕዝቡም የጉዳዩን አስፈላጊነት በዚያው ልክ እንዲገነዘብ እና ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ነው በአፅንዖት ያሳሰበው፡፡
‹‹ይሄን ግድብ ገንብቶ የማጠናቀቅ ጉዳይ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በዕኩል የኃላፊነት መጠን የሚመለከት እንጂ የኔ ወይም ደግሞ ያንተ ነው ልንባባልበት የሚገባ አይደለም›› ያለው ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ ‹‹ስለዚህ እኔ አሁንም በዚህ አጋጣሚ ደግሜ ለመናገር የምፈልገው ነገር ቢኖር ጉዳዩን ልክ በሁለት የስፖርት ክለብ ደጋፊዎች መካከል እንደሚስተዋለው ዓይነት የኔና ያንተ ብለን ልንከፋለው እንደማንችል አውቀን ሁላችንም እንደ ዜጋ የየራሳችንን ታሪካዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ይጠበቅብናል የሚለውን ነው›› ሲልም መልክቱን አስተላልፏል፡፡ ታዲያ ይህን ቅን መካሪ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ስፖርት ግንባር ቀደም ጀግናችንን የኢትዮጵያ እና የመላው ሕዝቦቿ የቁርጥ ቀን ልጅ አድርገን ብንወስደው ይበዛበታልን? እንደኔ እንደኔ ለኃይሌ ይገባዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ ስለዚህም ኃይሌ፤ በሀገራችን ፈርጀ ብዙ የሕዳሴ ጉዞ የመጀመሪያውን ረድፍ ይዘው ከተሰለፉ ብርቅዬ የፀረ ድህነት ትግሉ አርበኞቻችን መካከል አንዱ ስለመሆኑ ከወዲሁ ተገንዝቦ ገንቢ ሚናውን በላቀ ስፋት እና ጥልቀት አጠንክሮ ይገፋበት ዘንድ እጠብቃለሁ!፡፡