የዴሞክራሲያዊ መንገዱን ጥርጊያ የሚያመቻች ተግባር

በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና በተቃዋሚዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውይይት ሁሉም ፓርቲዎች ምንም ዓይነት የውጭ አደራዳሪ እንደማያስፈልጋቸው በመተማመን መስማማታቸው ተዘግቧል። ይህም በተለያዩ ጊዜያት በአደራዳሪ ጉዳይ እንዲሁ ጊዜያቸውን ያሳልፉ የነበሩ ፓርቲዎቹ በስተመጨረሻ በመተማመን ላይ መድረሳቸው የሚደነቅ ነው። እንዲህ ዓይነቱ በመቀራረብ፣ በመከራከርና ሃሳብን በልዩነት በማቅረብ በስተመጨረሻም ወደ ጋራ ስምምነት ላይ መድረስ የዴሞክራሲያዊ መንገዱን ጥርጊያ ይበልጥ የሚያመቻች ይመስለኛል። 

እርግጥ የትኛውም ፓርቲ በዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ውስጥ የሚያከናውናቸው ተግባራት በቅድሚያ መመልከት ያለበት ህዝቡን ነው። የውይይቱ ዓላማ ፓርቲዎች የሚወክሏቸውን ህዝብ ድምፅ እንዲሰማ ማድረግ በመሆኑ በቅድሚያ የዚያን ህዝብ ይሁንታ አግኝቶ፣ ፓርቲው ለዴሞክራሲያዊው ስርዓት ምን ዓይነት ሚና ሊወጣ እንደሚችል ማወቅ አለበት። እናም የፓርቲዎቹ ውይይት ሲጀመር የውይይቱን ዓላማ ከማሳካት አኳያ መታየት አለበት።

እንደሚታወቀው ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ የሀገራችንን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያጎለብትና የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ የሚያሰፋ ነው። ውይይቱ ገና በቅድመ ሁኔታ ደረጃ ያለ ቢሆንም ቅሉ፤ እዚህ ሀገር ውስጥ በመገንባት ላይ ያለውን የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲሁም የሁሉንም ህዝቦች ውክልና የሚያጠናክር ነው። ስለሆነም ከጅምሩ ሊፈጠሩ የሚችሉ ክፍተቶችን የማጥበብና በሚያግባቡ ጉዳዩች ላይ ለሀገር ጥቅም ሲባል አንድ ላይ መስራት የግድ ይላል። ምክንያቱም ማናቸውም ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች በመቻቻል መርህ መከናወን ስላለበት ነው።

የዚህ ሀገር ፖለቲካዊ አጀንዳ ህዝቡን የሚወክሉትና በሀገራችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ ነው። ሌላ የማንም አይደለም። ስለሆነም በአንዳንድ ፅንፈኛ ወገኖችና የውጭ ተላላኪ ሃይሎች አማካኝነት ‘ህገ መንግስቱ ይቀየር፣ የታሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ይፈቱ፣ ድርድሩ ውጤት አያመጣም፣ እኩል ሜዳ አይኖርም…ወዘተ.’ የሚሉ የራሳቸው አጀንዳዎች በጥንቃቄ መታየት ያለባቸው ይመስለኛል። ምክንያቱም እነዚህ ከክርክሩና ከድርድሩ ዓላማዎች ጋር ፈፅሞ የማይሄዱት አስተሳሰቦች ጤናማ ያልሆኑና የዴሞክራሲያ ስርዓታችንን አንድም ስንዝር ወደፊት ፈቅ የሚያደርጉት ስላልሆኑ ነው። በመሆኑም ለፅንፈኞችና ለተላላኪዎች ኢ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች ምንም ዓይነት ጆሮ መስጠት አይገባም። በእነርሱ ተገቢ ያልሆኑ አጀንዳዎች ላለመጠለፍ የክርክሩንና የድርድሩን ዓላማዎች ማወቅ ይገባል።

አዎ! ሁሉም ተወያይ ፓርቲዎች የክርክሩንና የድርድሩን ዓላማዎች በተገቢው መንገድ ሊገነዘቡ ይገባል። እንደሚታወቀው ኢህአዴግን ጨምሮ በቀጣይ ለመከራከርና ለመደራደር ውይይት እያካሄዱ ያሉት 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ዓላማዎቻቸው ዴሞክራሲን ማስፋት፣ ሰላምን አስተማማኝ ማድረግና ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ናቸው።

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ መንግስትም እንዲሆን የሚፈልገው በእነዚህ ዓላማዎች መንፈስ ነው።  ከዚህ ውጭ ፅንፈኞችና የውጭ ሃይሎች ተላላኪዎች የሚያነሷቸው አደናቃፊ ሃሳቦች አንድም ስንዝር ዕውን እንዲሆኑ የሚፈለጉ ሃሳቦችን የሚያመጡ አይደሉም። እናም በክርክሩና በድርድሩ ወቅት ሁሉምወገኖች ማሰብ ያለባቸው የሀገራችን ዴሞክራሲ እንደምን እንደሚሰፋ፣ ሀገራችን ውስጥ የተገኘውን ፈጣንና ተከታታይ ልማት እንደምን በአስተማማኝ ሰላም ማጠናከር እንደሚቻል ብሎም በአብዛኛዎቹ ሀገራዊ ጉዳዩች ዙሪያ እንደምን ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር እንደሚቻል ነው።

እንደሚታወቀው ዴሞክራሲን ለማስፋት ጊዜን ይጠይቃል። እንኳንስ እኛ ቀርቶ ተግባሩን ዕውን ካደረጉ ከ200 ዓመት በላይ ያስቆጠሩት ያደጉት ምዕራባዊያን ሀገራትም ቢሆኑ በተሟላ የዴሞክራሲ ቁመና ላይ ነው ያሉት ማለት አይቻልም። ዴሞክራሲ ከህብረተሰብ የአስተሳሰብ ልህቀት ብሎም ጥልቅ ግንዛቤ ጋር በጊዜ ሂደት ውስጥ የሚጎለብት ነው።

ከዚህ አኳያ በሀገራችን የዴሞክራሲ ምንነት መሰማት ከጀመረ ገና 25 ዓመታት ብቻ ናቸው የተቆጠሩት። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የተወሰነ ርቀት መጓዝ ቢቻልም፤ ያን ያክል የሚያስመካ አይመስለኝም። ለዚህም ሁለት ምክንያቶች በተግዳሮትነት መጠቀስ ያለባቸው ይመስለኛል—ለዴሞክራሲ ጀማሪ መሆናችንና ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አመለካከቶች በተገቢው ሁኔታ አለመቀረፋቸው ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸውና።

ሀገራችን ለዴሞክራሲ አዲስ ናት። በዚህም ሳቢያ ስለ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳቦች የሚነሱ ጉዳዩች በሁሉም ወኖች በኩል ህፀፆችን መፍጠራቸው አይቀርም። በዚህም ግልፅነትና ተጠያቂነት ብሎም መቻቻልን የመሳሰሉ የዴሞክራሲ እሴቶችን በተገቢውና በፈጠነ ሁኔታ ገቢራዊ ማድረግ ያስቸግራል። ፅንሰ ሃሳቦች አዲስ በመሆናቸውም በአስተማማኝ ሁኔታ ይተገበሩ ዘንድ ጊዜን ምርኩዝ ያደርጋሉ። ብዥታምን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ሆኖም ለተግባራዊነታቸው ከሂደት መማር ይቻላል።

በሌላ በኩልም ያለፉት ስርዓቶች በሀገራችን ህዝቦች መካከል ፈጥረውት ያለፉት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች በቀላሉ የሚሽሩ አይደሉም። ፀረ-ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎችን በዴሞክራሲያዊነት ለመቀየርም አስተሳሰብንና ስለ ዴሞክራሲ ያለንን አመለካከት መለወጥ ይገባል። በህዝቦች ውስጥ ለዘመናት ሲፈጠሩ የነበሩትን የተዛቡ ግንኙነቶች በጥቂት ዓመታት ውስጥ መቀየርም አይቻልም። ቀደም ሲል እንዳልኩት ጊዜንና የአስተሳሰብ ልህቀትን ይጠይቃል። ይህ ሁኔታም ምናምባትም ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ሊያሰናክል ይችላል።

እናም ዴሞክራሲው እንዲሰፋ እነዚህን ሁለት ተግዳሮቶች መፍታት ይገባል። ይህን ዕውን ለማድረግም የህዝቡ ወኪሎች የሆኑት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል። በመሆኑም ፓርቲዎቹ በክርክሩና በድርድሩ ሂደት ውስጥ ‘እነዚህን የዴሞክራሲ ተግዳሮቶች ለመፍታት ከእኔ ምን ይጠበቃል?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ይገባቸዋል። ይህን ሲያደርጉም ለሀገራቸው ዴሞክራሲ መስፋት የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ።

ፓርቲዎቹ ሌላው ሊያነሱት የሚገባው ጉዳይ ክርክሩና ድርድሩ ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያ ሊኖረው የሚገባውን ፋይዳ ነው። እንደሚታወቀው የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ሁከት ተፈጥሮ ነበር። የሁከቱ አነሳሽ ምክንያት ምንም ይሁን ምን፤ ፓርቲዎች እንዲያ ያለው ሁከት ዳግም እንዳይፈጠር መስራት ይኖርባቸዋል።

ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ክርክርና ድርድር መቋጫው ጥርጣሬንና ግጭትን በማስወገድ ሰላምን ማምጣት ነው። ሰላም ካለ ሁሉም ነገር አለ። ያለ ሰላም ልማትን ማሰብ አይቻልም። ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱንም ስር እንዲሰድ ማድረግ አይቻልም። ዴሞክራሲ ስር ባልሰደደበት ሀገር ውስጥ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ልባቸው ሃሳባቸውን ለህዝባቸው ሊያስተዋውቁና በህዝቡ ይሁንታ በሚካሄድ ምርጫ ሀገር ሊመሩ አይችሉም።

እናም ከክርክርጨሩና ከድርድሩ ዴሞክራሲንና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የራሳቸውን ህልውና ጭምር የሚያረጋግጡ መሆናቸውም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊገነዘቡት የሚገባ ይመስለኛል። እናም እንደ ሰሞነኛው ዓይነት ሁሉም ፓርቲዎች የጋራ አቋም የሚይዙበት አጀንዳዎች ሊበራከቱ ይገባል። ዴሞክራሲ ማለት ሁሌም የራስን ሃሳብ ብቻ ቅቡል እንዲሆን ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ የሌላውንም አድምጦ ለሀገርና ለህዝብ ሲባል ከግማሽ መንገድ በላይ መጓዝ መሆኑ መታወቅ አለበት። አበቃሁ።