ጥቂት ነጥቦች ስለ ህገ መንግስቱ መሻሻል

የአንድ ሀገር ህገ መንግስት የወጣበት መንገድ የመኖሩን ያህል፤ የሚሻሻልበት መንገድም እውን የሚሆንበት አሰራር አለው። ከዚህ አኳያ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀፅ 104 እና 105 ላይ የተገለፁ ፍሬ ነገሮችን ይዟል። በህገ-መንግስት አንቀፅ 104 ላይ የሚገኘውና “የህገ-መንግስት ማሻሻያ ሃሳብን ስለማመንጨት” በሚለው ርዕስ ስር፤ የማሻሻያ ሃሳቡን የህዝብና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲደግፉት እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ውስጥ አንድ ሶስተኛው የክልል ምክር ቤቶች በድምፅ ብልጫ የደገፉት ከሆነ፤ የማሻሻያ ሃሳቡ ለመላው ህዝብና የህገ- መንግስቱ መሻሻል ለሚመለከታቸው ክፍሎች እንደሚቀርብ ይገልፃል።

ከዚህ ጎን ለጎንም “ህገ-መንግስቱን ስለማሻሻል” በሚያወሳው አንቀፅ 105 ስር፤ ህገ- መንግስቱን የማሻሻል ጉዳይ ንዑስ አንቀፅ አንድ እስከ ንዑስ አንቀፅ ሁለት ድረስ ባሉት የድንጋጌ ማዕቀፎች ውስጥ ብቻ እንደሚከናወን ተብራርቷል። በዚህ መሰረትም በአንቀፅ 105 (1) ላይ፤ በህገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት የተዘረዘሩት መብቶችና ነፃነቶች በሙሉ፣ ይህ አንቀፅና አንቀፅ 104 ሊሻሻሉ የሚችሉት፤ ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምፅ ብልጫ ሲያፀድቁት፣ የፌዴራሉ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የቀረበውን ማሻሻያ በሁለት ሶስተኛ ሲፀድቀውና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲፀድቀው ብቻ እንደሚሆን ተደንግጓል።

በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ ሁለት ላይም፤ ከላይ የጠቀስኩት የአንቀፁ ንዑስ አንቀፅ አንድ ከተዘረዘሩት ውጭ ያሉት የህገ-መንግስቱ ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት፦ (ሀ) የህዝብ ተወካዩችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባቸው የቀረበውን ማሻሻያ በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲያጸድቁት እና (ለ) ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤቶች ውስጥ የሁለት ሶስተኛ ክልሎች ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምፅ ብልጫ ሲያፀድቁት ብቻ እንደሆነ በግልፅ ተደንግጓል። እነዚህ ህገ-መንግስቱን ስለማሻሻል የሚያወሱት አንቀፆች የህገ-መንግስቱ ዴሞክራሲያዊነት ትክክለኛ መገለጫዎች ናቸው።

የህገ- መንግስቱ ባለቤት ገዥው ፓርቲ አይደለም። ምከንያቱም ዋነኛው ባለቤቶች መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ናቸውና። ለዚህም ህገ- መንግስቱ በመግቢያው ላይ “እኛ የኢትዮጱያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች… በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት…ህገ- መንግስቱን በተወካዮቻችን አማካኝነት አፅድቀነዋል” የሚለውን አባባል መጥቀስ የሚቻለ ይመስለኛል።

ለነገሩ እዚህ ላይ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ አሁን በስራ ላይ ላለው ህገ- መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ስርዓት እውን መሆን መታገሉ፤ ማታገሉና በሂደቱም መስዋዕትነት መክፈሉ የሚካድ አይደለም። በዚህም ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከአምባገነኑ ፀረ- ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የአፈና አገዛዝ አላቋል። በሀገራችን የፀረ- ዴሞክራሲ ኢኮኖሚያዊ መሰረትን ንዷል፣ የብሔራዊ ጭቆናን ተቋማዊና መዋቅራዊ እንዲሁም ድርጅታዊና ርእዮተ ዓለማዊ መሰረቶች ከመሰረታቸው እንዲመነገሉ  አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪ፤ የግልና የቡድን መብቶችን ያጣመረ ዴሞክራሲን መገንባት ችሏል። እነዚህና ሌሎች ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲያዊና የሰብአዊ መብት እምነቶች ለህዝብ ቀርበው እስከ ታች ድረስ የወረደ ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸው ማሻሻያ ከተደረገባቸው በኋላ፤ በህገ- መንግስትነት እንዲፀድቁና ህዝቡ “የእኔ ናቸው” ብሎ እንዲቀበላቸው አድርጓል። ይህም ዴሞክራሲያዊው ስርዓት እንዲፈጠር ገዥው ፓርቲ የመሪነት ሚናውን በብቃት ቢወጣም፤ በስተመጨረሻም የህገ- መንግስቱ ባለቤት ህዝቡ መሆኑን በግልፅ የሚያስረዳ ዕውነታ ይመስለኛል።

ይህ ብቻ አይደለም። ለህገ- መንግስቱ መሰረት በሚካሄዱ ምርጫዎች ህዝቡ ድምፅ የሚሰጠው ህገ- መንግስቱን ለሚንከባከብለትና ለሚጠብቀው ኃይል መሆኑ ለአምስት ለተከታታይ የምርጫ ጊዜያት ታይቷል። ይህም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አምነውበትና ተስማምተውበት ያፀደቁትን ዴሞክራሲያዊ ህገ- መንግስት የትኛውም ኃይል እንዲነካባቸው የማይፈልጉ መሆኑን የሚያሳይ ሃቅ ነው።

ከህገ- መንግስቱ ውስጥ አንቀፆችን መሰረዝም ይሁን ማሻሻል የሚችሉት የሀገራችን ህዝቦች ወይም ስልጣናቸውን በውክልና በመስጠት የመረጡት አካል እንጂ የትኛውም አካል አለመሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። ከዚህ በተጨማሪም የህገ መንግስቱን ምሶሶዎች ማፍረስ የሚቻል አይመስለኝም።

የህገ-መንግስቱ ምሶሶዎች ተብለው በመሰረታዊነት ከሚጠቀሱት ውስጥ፤ የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት፣ የቡድንና የግለሰብ መብቶች የተከበሩበት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ስርዓት፣ ራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት፣ የነፃ ገበያ መርህና በዚሁ ማዕቀፍ የመሬት አስተዳደር  በመንግስትና በህዝብ ስር እንዲሆን ማድረግ የሚሉት ዋነኛዎቹ ናቸው።

እነዚህን የህገ-መንግስቱን የማዕዘን ድንጋዩች መቃወም አሊያም ከህገ-መንግስቱ ውስጥ እንዲወጡ ማለም ማለት፤ እንደ አፄው ስርዓት ወቅት “ስዩመ-እግዚሐብሔር” እየተባለ መንግስትና ሃይማኖት አንድ እንዲሆኑ መመኘት፣ የቡድንና የግለሰብ መብቶችን የሚጨፈልቁት ያለፉት ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች ተመልሰው እንዲመጡ መሻት፣ የሌሎች ፍላጎቶችን ለማሟላት ሲባል የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቶችን እንዲታፈኑ መፍቀድ አሊያም ያለፈውን የሶሻሊስት ስርዓትን በመናፈቅ የነፃ ገበያ ስርዓት መርህ እንዳይኖር መፈለግ እንዲሁም የአርሶ አደሩን መሬት በመሸጥና በመለወጥ ጭሰኛ ሆኖ እንዲቀር መፈለግ ማለት ነው።

እነዚህን ፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊና ፀረ-ልማታዊ አስተሳሰቦችን ጫንቃው ላይ ጭኖ ለመሸከም የሚፈቅድ ማህበረሰብ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር አይመስለኝም። የለምም። የሀገራችን ህዝቦች እነዚህን ፀረ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ልማታዊ እሳቤዎችን አምርሮ የሚጠላቸውና ከጫንቃው ላይም እንዲወገዱ በፅናት የታገላቸው ናቸው። በመሆኑም እነዚህን ያለፉ ስርዓቶች ተግባራትን ማለም ህገ-መንግስቱን ዕውን ለማድረግ ውድ ህይወቱን ከከፈለው የሀገራችን ህዝብ ጋር መጋጨት ይመስለኛል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች የህገ-መንግስቱ ምሶሶዎች በሌሉበት ሁኔታ ውስጥ መኖርን በምንም መንገድ ሊፈቅዱት አይችሉም። ከሁሉም በላይ ደግሞ በህገ-መንግስታዊ ዓመታት የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን በሚገባ ማጣጣማቸው፣ የጀመሩት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲያድግላቸውና እንዲመነደግላቸው ይሻሉ እንጂ፤ ዳግም ተመልሰው በኢ-ሰብዓዊና አምባገነናዊ ስርዓቶች ውስጥ መዳከርን አይመኙም፤ ሊያስቡትም የሚፈልጉ አይመስለኝም። እናም በርካታ መስዕዋትነት የከፈሉበትንና የቃል ኪዳን ሰነዳቸው የሆነውን ህገ-መንግስት እንደ ዓይናቸው ብሌን ይንከባከቡታል።

ህገ-መንግስቱ በራሳቸው የደም ጠብታ የፃፉት የጋራ ሰምምነት ሰነዳቸው በመሆኑም፤ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ባልተገባ ሁኔታ ሊቆርሱት እንዲመኙ ዕድል የሚሰጧቸው አይመስለኝም። ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች ላለፉት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የተጎናፀፉትን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሳጧቸው መሆኑን ስለሚያውቁም፤ ለሰነቁት ራዕይና የህዳሴ ጉዞ ደንቃራ እንዲሆኑባቸው ይፈቅዳሉ ተብሎ አይታሰብም። ያም ሆነ ይህ ግን ህገ መንግስቱን ማሻሻልም ይሁን በዋነኛ የህገ መንግስቱ አውታሮች ላይ ውሳኔ የመስጠት መብት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብቻ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ሰላም!