ክብር ለዴሞክራሲ ተቋሞቻችን!

በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየጎለበተ የመጣበት ሁኔታ አሁን…አሁን በግልጽ ይታያል። ሆኖም ይህንን በተገቢው መንገድ የመገንዘብ ችግር አሁን ላይ መንፀባረቁ አልቀረም፡፡ ዴሞክራሲያዊ አሠራርን የኢ ዴሞክራሲያዊ ካባ ደርበው የሚንቀሳቀሱት ተቃዋሚዎች ይህን በህዝቡ የማይደገፍ እኩይ ሴራቸውን ተወት ቢያደርጉት መልካም ይሆናል።  

 

ይህን ሀሳብ ያለምክንያት አላነሳሁም። ምክንያቱም ህዝብን እንደ ህዝብ የሚንቅ ማንኛውም አካል የመጨረሻ ዕጣ ፈንታው የአገሬ ሰው እንደሚለው "ጨው ለራስህ ስትል…" እንደሚለው ተብሎ መወርወሩ አይቀርም። እዚህ ላይ አንድ እውነታን ማንሳት ፈቀድሁ። ይኸውም መልካም አስተዳደር የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ካልታከለበት በስተቀር በመንግሥት ጥረት ብቻ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል መሆኑ ነው። ማንኛውም ህዝብ ያልተሳተፈበት ጉዳይ ተፈፃሚ ወይም ስኬታማ ሊሆን አይችልምና።

 

በመሆኑም በመንግሥት በኩል መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉና በሂደት የሚከናወኑ ቁርጠኛ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው መላው ህዝብ ዛሬም እንደ ትናንቱ ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይኖርበታል። በተለይም ቁልፍ የዴሞክራሲ ማስፈኛ ተቋማት በሚባሉት እንደ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዓይነቶችን በአግባቡ በመጠቀምና የሚፈጠሩ ችግሮችን ተከታትሎ በማሳወቅ ለመልካም አስተዳደር እመርታ መትጋት ከማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው።

 

መንግሥት ምንም እንኳን ግዴታው ቢሆንም ህገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት ብሎም ራሱም ለዴሞክራሲ ሥር መስደድ ካለው ቀናዒ ፍላጎት በመነሳት፤ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የዜጎች አቤቱታ የሚደመጥበት እንዲሁም ተገቢው ምላሽ የሚሰጥበት የእንባ ጠባቂ ተቋምን አቋቁሟል።

 

ለዴሞክራሲው ግንባታ እውን መሆንና ላሳየው የማይናወጥ ቁርጠኝነት "ጎሽ! በጎ ተግባር ከወንክ" ብሎ ማመስገን ሲገባ ያለ አንዳች በቂ ማስረጃ በመንግሥትና በዴሞክራሲ ተቋማቱ ላይ በደፈና ጥላቻ እየታገዙ የውርጅብኝ መዓት ማውረድ ተገቢ አይሆንም። ክንዋኔዎችን በአንክሮና በሰከነ አዕምሮ ከሚያይ ተፎካካሪ ፓርቲም አይጠበቅም።

 

ከነዚህ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት መካከል አንዱ የህዝብ እንባ ጠባቂ ነው። ይህ ተቋም በዜጎች ላይ የሚፈፀም አስተዳደራዊ በደል ተገቢው ምላሽ እንዲያገኝ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ውጤት ማስመዝገቡ ይታወቃል። በስሜት ብቻ እየተገፋፉ የተቋሙን ስም ለማጥፋት መሯሯጥ ብሎም መንግሥት በዘርፉ እያደረገ ያለውን ጥረት በፀረ ዴሞክራሲያዊነት ታውሮ ለማጠልሸት መጣር በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት አይኖረውም። ራሱ ተቃዋሚ ነኝ ባዩ አካልም ቢሆን አመለካከቱ ገንቢና ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑ በእንዲህ ዓይነቱ ጭፍን እሳቤ ጉዞው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱ አሜኬላ እሾህ መሆኑ አይቀርም።

 

መልካም አስተዳደር የሚታሰበው ሥርዓቱ ተግባሩን ለማከናወን ካለው በጎ ምልከታ አኳያ መሆኑ እርግጥ ነው። ታዲያ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሥርዓትም መልካም አስተዳደርን በሂደት ለመፈፀም ቁርጠኝነት ያለው ብቻ ሳይሆን፤ መልካምና የተመቻቸ ምህዳር ጭምርም የነገሰበት ነው። ለምን ቢሉ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ሥልጣን የህዝብና የህዝብ ብቻ መሆኑን በግልፅ በማስቀመጡ ነው። ሥልጣን የተገልጋዩ ህዝብ መሆኑ ደግሞ ለመልካም አስተዳደር እመርታ የራሱ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አይካድምና።

 

እንደሚታወቀው መልካም አስተዳደር የተግባር እንጂ የንድፈ ሐሳብ ጉዳይ አይደለም። ተግባሩ ከዜጎች የዕለት ተዕለት የኑሮ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ፤ በአተገባበሩ ላይ የሥልጣኑ ባለቤት የሆነው ህዝብ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን አለበት። ህዝቡ በህገ መንግሥቱ የተጎናፀፈውን ሥልጣን በአግባቡ እንዲጠቀምበት ዕድል ይፈጥራል።

 

ታዲያ የአገሪቱ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ይህ ሁኔታ እንዲተገበር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። ቀደም ሲል የጠቀስኩት የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ችግሮችን እየተከታተሉ በማረም ለመልካም አስተዳደር ግንባታው የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ከተቋቋሙት ገለልተኛ አካላት ውስጥ ለአብነት ያህል የሚጠቀሱ ናቸው።

 

ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እነዚህ አካላት እንዲቋቋሙ በአዋጅ ከማፅደቅ ጀምሮ ተግባራቸውንም የመልካም አስተዳደር እመርታን በሚያረጋግጥ አኳኋን እንዲፈፅሙ እስከ ማድረግ ድረስ አመቺ የሆኑ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።

 

እነዚህ ገለልተኛ አካላት ህዝቡ በህገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡለት መሠረታዊ መብቶቹ ተግባራዊ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። እስካሁንም ድረስ በርካታ ህዝባዊ ጉዳዮችን በመመልከት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት እየተወጡ ነው – አቅም በፈቀደ መጠን።

የመልካም አስተዳደር ሥራ በርካታ ዓመታትን የሚጠብቅ ከመሆኑም በላይ አገሪቱ ካለባት የማስፈፀም አቅም ውስንነት አኳያም ተያይዞ የሚታይ ነው። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ያለው የመልካም አስተዳደር ትግበራ አፈፃፀም የአቅም ውስንነትን ተሻግሮ መሻሻል እያሳየ ነው።

 

ይህ ማለት ግን አገሪቱ ውስጥ ፈፅሞ የመልካም አስተዳደር ችግር የለም ማለት አይደለም። በአስቸኳይ መፈታት ያለባቸው ችግሮች በአፋጣኝ መፍትሄ እየተሰጣቸው ነው። ሌሎችም እየታዩ በሂደት ምላሽ ያገኛሉ። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ማንኛውም የመልካም አስተዳደር ችግር በሂደት መስተካከሉ አይቀሬ ነው።

 

ሆኖም እንደ ተቃዋሚዎቹ ሁሉንም ነገር ከመደፍጠጥና ከማጥቆር አባዜ ውስጥ ያልወጡ ጭፍን መንገደኞች የአሉባልታ ዲስኩር ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም በተጨባጭ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ህያው ምስክሮች ናቸውና።

 

ተቃዋሚ ተብዬዎች በተለያዩ ህጋዊ አግባቦች አለመሟላት ምክንያት ምላሽ ያልተሰጠውን አንድ ነጠላ ጉዳይ በመምዘዝ እንዲሁም እነ ሂዩማን ራይትስ ዎችን የመሳሰሉ በክቡር የሰው ልጅ ስም የሚነግዱ አክራሪ ኒዩ ሊበራሎችን በመጥቀስ የዴሞክራሲ ተቋማቱን መልካም የሥራ ውጤት ለማጣጣል ሲጥሩ ይስተዋላሉ።

 

ይህ ደግሞ ሀቁን ለሚረዳው ህዝብ አሁንም ቢሆን እነዚህ ወገኖች ካለፈው ድርጊታቸው አለመማራቸውን የሚያረጋግጥ እውነታ። በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች  አንዴም እንኳን ቢሆን የተከናወኑ በጎ ተግባራትን ልባቸውን ከፍተውና ዓይናቸውን ገልጠው ቢመለከቱ መልካም በሆነ ነበር። የተፎካካሪ ቡድን ወግና ባህል ይኸው ነበርና።

 

በመሆኑም የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ የሆነውና የሥልጣን ባለቤትነቱን ያረጋገጠው ህዝብ፤ ሥልጣኑ በእርሱ እጅ መሆኑን ዛሬም ቢሆን ነገ አምነው መቀበል ይኖርባቸዋል።

እነዚህ ወገኖች የመልካም አስተዳደር አስፈፃሚ የሆኑትን የሲቪል ሰርቪሱን አወቃቀርና አሠራር እንዲሁም የዳኝነት ሥርዓቱን ለመኮነንም ተወዳዳሪ አልተገኘላቸውም። ያለ አንዳች የነጠረ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሲውተረተሩ ይስተዋላሉ።

 

በቅድሚያ ለመተቸትም ሆነ ለማንቆለጳጰስ ስለ ጉዳዮቹ በቂ ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል። በማያውቁት ጉዳይ ውስጥ ገብቶ መፈትፈት ግምት ላይ ይጥላልና ረጋ ብሎ ሁሉንም ጉዳይ ማጤን ታላቅነት ነው። ካልሆነ አሳፋሪ ነው። ክብር ለዴሞክራሲ ተቋሞቻችን!