6ኛው ዙር ታላቁ ሩጫ በወላይታ ተካሄደ

ሰኔ 05/2013(ዋልታ) – 6ኛው ዙር ታላቁ ሩጫ በወላይታ ሲካሄድ በአትሌትክስ ስፖርት ወላይታን ብሎም ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተገልጿል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ አቶ መርክኔ ማለዳ እንደገለጹት ስፖርት ለአንድነት፣ ለወዳጅነትና ለሁለንተናዊ ብልጽግና ጉልህ ሚና አለው። ከተማ አስተዳደሩ ለአትለቲክስ ስፖርት ዘርፍ እድገት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የማህበረሰብ ስፖርትን አጠናክሮ በመቀጠልና የስፖርቱ መልካም እሴት በሆነው ወዳጅነት ለሶዶ ከተማ እና አጠቃላይ ለዞኑ ሰላምና ልማት ሀሉም የስፖርት ቤተሰብ በጋራ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንጠናቀቅ የስፖርቱ ቤተሰብ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የደቡብ ክልል አትሌቲክስ ምክር ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ጣባ እንዳሉት በወላይታ ዞን በአትሌቲክሱ ዘርፍ የተሻሉ ወጣቶች  ያሉበት በመሆኑ   እንደ ወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ሰፖርት ክሌብ በሀገር ደረጃ አካባቢውን የሚያስጠሩ ሯጮች እንዲወጡ ትኩረት ተሰጥት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በደቡብ ክል ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ብሩክ ቡናሮ በበኩላቸው የክልሉ ስስፖርት ኮሚሽን ለህብረተሰብ አሳታፊ ስፖርት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝና ወላይታም በዘርፉ አመርቂ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የወላይታ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ምክትል ኃላፊና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አኮየ ገካ አንደገለጹት ታላቁ ሩጫ በወላይታ ለወላይታ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ይህ ሩጫ ከአላማው አንጻር በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በአዕምሮና በአካል ያደገ አምራችና ጤናማ ማህበረሰብ  ለመፍጠር በዞኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ አኮየ ሀሉም ህብረተሰብ በስፖርቱ እንዲሳተፍና አጋር አካላትም ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥር አቅርበዋል።

በውድድሩ ከሴቶች ድንቅነሽ ኦርሳንጎ፣ ይፍቱስራ ባልቻ እና ፅዮን ኃ/ሚካኤል ከ1ኛ አስከ 3ኛ ደረጃ የወጡ ሲሆን  መክሊት መኮንን፣ ሳሙኤል ባልጣ እና ታደሰ አማኑ ደግሞ ከወንዶች ከ1ኛ እስከ ሦሥተኛ በመውጣት የዕውቅና ሽልማት አግኝተዋል፡፡

ዘገባዉ የወላይታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነዉ፡፡