ለአብረኆት መጽሐፍ በመለገስ ሀገር እንገንባ

ግንቦት 11/2014 (ዋልታ) ድረ ገጽ ተኮር ማኅበራዊ ሚዲያዎችና የትስስር ገጾች ዓለማችን ካገኘቻቸው የቴክኖሎጂ ትሩፋቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የማኅበራዊ ሚድያ ገጸ ድሮች በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎችን ማፍራትም ችለዋል፡፡

አነዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጸ ድሮች በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች የሚተሳሰሩበት፣ ሀሳብና አስተያየት የሚጋሩበት፣ ከዚያ አለፍ ሲልም ስለሚኖሩበት ዓለም ሁኔታ የተለያዩ መረጃዎችን የሚጋሩነትን እድል ፈጥረዋል፡፡

ይህ የማኅበራዊ የትስስር ገጸ ድሮች መልካም ጎኑ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ከልክ ያለፈ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ውስጥ ተዘፍቀው በመግባት ሱሰኛ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ የማኅበራዊ የትስስር ገጸ ድሮች አሉታዊ ገጽታው በመነሳት የሚለቀቁ የሀሰት መረጃዎች እንደ ወረደ የመቀበል አዝማሚያ እየተበራከተ መጥቷል፡፡ ይህ እየተበራከተ እና አየተወሳሰበ የመጣው የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት የትውልዱ ፈተና ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በማኅበራዊ ትስስር ገፆች የሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎች እየተወሳሰቡ በመምጣታቸው ወጣቱ በስሜታዊነት ተነሳስቶ ወዳልሆነ ድርጊት ሲገባ እየተስተዋለ ነው፡፡

ይህንን የዘመናችን ፈተና በአግባቡ ለመወጣት ደግሞ ታዳጊ ወጣቶች ምክንያታዊ እንዲሆኑ ማስቻል ዋነኛው መሳሪያ ነው፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ ያልተጣሩ መረጃዎችን በማንበብ ትውልዱ ጊዜውን ከሚያባክን ከጊዜው ጥቂቱን ለመጻሕፍት ቢሰጥ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅም አስተሳሰብ እና የግንዛቤ አድማስን የሚያሰፋ እውቀት እንደሚጨብጥ ይታመናል፡፡

ለዚህም ይረዳ ዘንድና የንባብ ባህልን ለማጎልበት የንባብ ማዕከላት መስፋፋት ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱ በመሆናቸው አራት ሚሊዮን መጻሕፍትን መያዝ የሚችል አብርኆት ቤተ-መጽሐፍ እውን ሆኗል፡፡

ለአብርኆት ቤተ-መጽሐፍ እንደ ሀገር ለአንድ ወር በሚቆየው የአንድ ሚሊዮን የመጻሕፍት ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር በርካቶች አሻራቸውን ለማስቀመጥ እየጣሩ ሲሆን የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ሰራተኞችም በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

መጻሕፍት በስክነትና በጥሞና በማንበብ መረጃን ከምንጩ ለማወቅ እድል ሲፈጥሩ በአንጻሩ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎች ተዓማኒነት እና ምሉዕነት የሚጎድላቸው በመሆናቸው ትውልዱ ማንበብን፣ መጠየቅንና መመርመርን እንዲለምድ ቤተ መጻሕፍት መገንባት ፋይዳቸው የጎላ ነው፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያ ገጸ ድሮች የሚሰራጩ መረጃዎች ቁንጽል ከመሆናቸው የተነሳ አሉታዊ አጀንዳ በመፍጠር ትውልዱን በስሜታዊነት ወዳልሆነ ድርጊት እንዲገባ ምንክንያት ሲሆኑ ይታያሉ ሲሉ የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ሰራተኞች ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የቤተ መጻሕፍት ግንባታ በንባብ ባህል የተቃኘ ትውልድ ከመፍጠር በሻገር ለጥናትና ምርምር መሰረት ይሆናሉ ነው ያሉት፡፡

በሀገር ዐቀፍ ደረጃ በንባብ ባህል የተቃኘ ትውልድ መፍጠር የሀገር ግንባታ አንደኛው መሰረት በመሆኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በማሰባሰቡ መርኃ ግብሩ ላይ ተሳታፊ እንዲሆን  ጥሪ አቅርበዋል፡፡