ለጉራጌ ዞን ነዋሪዎች የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በቅንጅት ይሰራል – ጠ/ሚ ዐቢይ

መጋቢት 16/2015 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግስት የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ለሚያነሷቸው የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት በቅንጅት እንደሚሰራ አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ጋር በተለያዩ የልማት ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን የውይይቱ ተሳታፊዎች የሰላም፣ የልማትና አስተዳደራዊ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

ነዋሪዎቹ በጥያቄዎቻቸው በዞኑ የውሃ፣ የመንገድ፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት ተደራሽነት ችግር መኖሩን ተናግረዋል።

ይህም በዞኑ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና መፍጠሩን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

በመሆኑም የጉራጌ ዞን ራሱን ችሎ በክልልነት በመደራጀት የልማት ጥያቄዎቹን ለመፍታት ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል የሚል ጥያቄ ተነስቷል።

ነገር ግን የክልልነት ጥያቄን እንደሽፋን በመውሰድ በዞኑ አብረው በጋራ የኖሩ ህዝቦችን ለማጋጨት የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን የጠቀሱት ነዋሪዎቹ፣ እነዚህ አካላት ተለይተው ለህግ እንዲያቀርቡም ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በምላሻቸው በሁሉም አካባቢዎች በርካታ የመልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን ገልፀው፤ መንግስት ያሉትን አቅሞች በማሰባሰብ ለጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ መንግስት የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ላነሷቸው የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

ከህዝቡ ለተነሱት የልማት ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ረገድ ባለሃብቶችም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

አስተዳደራዊ አደረጃጀት ለጥያቄዎች ሁሉ መልስ መስጫ መፍትሔ አለመሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ከአጎራባች ዞኖች ጋር ያላቸውን አብሮነት በማጠናከር በጋራ ለመልማት መስራት አለባቸው ብለዋል።