ርዕሰ መስተዳደሮቹ በጅግጅጋ ከተማ በኦሮሚያ ክልል የተገነባ ትምህር ቤት አስመረቁ

መጋቢት 19/2015 (ዋልታ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመለስ አብዲሳ በጅግጅጋ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት በዘመናዊ መልኩ የተገነባና “ካህ” የተሰኘ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በጋራ አስመረቁ።

በዚህም ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ ትምህርት ቤቱ ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ባሉበት አካባቢ በመገንባቱ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸውን የሶማሌና የኦሮሞ ወንድማማቾች ህዝቦች ትብብር፣ ትስስርና ግንኙነትን ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመለስ አብዲሳ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለሶማሌ ክልል ህዝብ የተበረከተ መሆኑን ገልጸው የሁለቱ ክልሎች ወንድማማቾች ህዝቦች በእውቀት ለማስተሳሰር እና የክልሎቹን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አመላክተዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይም የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች፣ ሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች እንግዶችም መገኘታቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።