በለውጡ ማግስት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ስኬት

በለውጡ ማግስት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ስኬት

በአድማሱ አራጋው

መጋቢት 15/2015 (ዋልታ) በሀገራችን ዓይንን በሚማርኩ እጽዋት ተውበው የነበሩ ተራሮች ተፈጥሯዊ ጋቢያቸውን በጉያቸው ሸሽገው የያዙ ደኖች ታሪክ ከሆኑ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ሸንተረሮችም ዕለት ተዕለት ከሚፈሱ የውሃ ጅረቶችና ፏፏቴዎች ከተራራቁ ውለው አድረዋል፡፡

ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ከሚዘልቀው የሀገሪቷ ቆዳ ስፋት ውስጥ 40 በመቶው በደን የተሸፈነ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ሕዝቡን ለመመገብ የእርሻ ቦታዎች ተደጋግመው ከመታረሳቸው በተጨማሪ አዲስ መሬት እየተመነጠረ ለእርሻ ሥራ እንዲውል ሁኔታው አስገድዷል፡፡ በዚህም መሬቱ በተደጋጋሚ ጊዜ በመታረሱ ለምነቱን እንዲያጣ ብቻ ሳይሆን ለመሬት መሸርሸር ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአየር ለውጥ በማስከተል ዜጎች በተደጋጋሚ ጊዜ ለድርቅ እንዲጋለጡ አድርጓል፡፡

በመሆኑም የደን መመናመንን ለመከላከልና በአየር ለውጥ የሚከሰተዉን ጫና የሚቋቋም አካባቢ ለመፍጠር መንግስት ህዝብን በማስተባበር የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያስጀመረ ሲሆን ለአየር ንብረት ለዉጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በተደረገው የደንና አካባቢ ጥበቃ ስራ የሀገሪቱ የደን ሀብት እንዲንያሰራራ ምክንያት ሆኗል፡፡

ይሁን እንጂ የተጀመረው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አዝጋሚ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት ከለውጡ (ሪፎርም) ማግስት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሃሳብ አመንጭነት  የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በየአከባቢው ዉጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ዘመቻ 20 ቢሊዮን ዛፎችን ለመትከል ዕቅዷን ይፋ አድርጋ በጀመረችበት ጊዜ በዓለም ደረጃ መነጋገሪያ ሆና እንደነበር የሚታወስ ነው። ሀገሪቱ ግን የተያያዘችውን ዕቅድ በእስከአሁኑ ከታሰበው በላይ ውጥኗን ማሳካት እንደቻለች መረጃዎች ያመለክታሉ።

በዚህም በመጀመያሪው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በአንድ ቀን ብቻ በሀገር ደረጃ 350 ሚሊዮን የዛፍ ችግኞች መተከል መቻሉ የታለመው ዕቀድ ከስኬት መድረሱን ያሳየን የቅርብ ጊዜ ትዉስታ ነው።

ይህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሃሳብ አመንጭነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የችግኝ ተከላው የአገሪቱን የአረንጓዴ እጽዋት ሽፋንን እንዳሳደገ፣ የአየር ንብረት ለውጥን እያስተካከለ እንደሚገኝ እና የሰዎች ሕይወትን እየቀየረ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል።

ዘመቻው በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ የመጣውን አጠቃላይ የደን ሽፋንን ለማስተካከል እንዲሁም ዘላቂነት ያለውን ሀገራዊ ልማት ለማረጋገጥ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዳለውም ይታመናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የደን መመናመን የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤን በመጨመር የተለያዩ የማህብረሰብ ክፍሎች ዓላማውን በመቀበል የበኩላቸውን ሚና እንደተጫወቱ የእስካሁኑ የተግባራት ሂደት ይመሰክራሉ፡፡

ይህ ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እንቅስቃሴ ከራሷ አልፎ ለጎረቤት አገራት ልምዷን በማካፈልና ችግኞችን በማቅረብ የበኩሏን ሚና የተጫወተችበት ፕሮጀክት ጭምር ሆኗል።

ይህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አመንጭነት ተግባራዊ የሆነው ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበሱ ትልም በተቀናጀ መንገድ እንዲካሄድ ለማስቻል ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ ችግኝ የሚተከልበትን ጉድጓድ ቁፋሮን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናውን እንዲወጣ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

የመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በ2011 ዓ.ም ሲጀምር ብዙዎች ሥራው የአንድ ወቅት ዘመቻ አድርገው አይተውት የነበረ ቢሆንም ቀጣይነቱን ግን ዛሬም አላቆመም፡፡

በመጀመሪያው ዙር መርኃ ግብር አራት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ሥራው መገባቱ የሚታወስ ሲሆን ወደ መሬት ሲወርድም ከእቅድ በላይ በመሆን 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል። ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በዚሁ በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ 23 ሚሊዮን ሕዝብ ተሳትፈዋል።

“40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ” በሚል መሪ ቃል ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከ353 ሚሊዮን 633 ሺሕ በላይ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያ የዓለም ክብረ ወሰን እንድትይዝ ማድረግ እንደተቻለም መረጃው ያሳያል፡፡

በሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ደግሞ በ2012 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ ስድስት ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል በዕቅድ ተይዞ ከዕቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል፡፡ በሁለተኛው ዙር ከሀገር በቀል ዛፎች በተጨማሪ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ተክሎች እና ቡና ትኩረት የተሰጣቸው ሲሆን 80 በመቶ የሚሆኑ ችግኞች መጽደቃቸውም ታውቋል።

ሦስተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ሀሳብ በ2013 ዓ.ም ተተግብሯል፡፡ በዚህም ስድስት ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 6 ነጥብ 7 ቢሊየን ችግኝ መትከል መቻሉ የሚታወስ ነው፡፡ ይህንንም ዙር ልዩ የሚያደርገው ነገር ቢኖር ሀገሪቱን አረንጓዴ ካባ የማልበሱ አብዮት ከሀገር አልፎ ወደ ጎረቤት ሀገራት መስፋፋቱ ሲሆን በወቅቱ አንድ ቢሊየን ችግኝ በጎረቤት ሀገራት እንዲተከል ተደርጓል።

በአጭር ግዜ ውስጥ ውጤት ያስመዘገበውና የመንግስት ትኩረት የሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከኢትዮጵያውያን አልፎ የሌሎች ሀገራት ዜጎች ተስፋ ወደመሆን የተሸጋገረው የአራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በሰኔ 14/2014 ዓ.ም በይፋ በጠቅላይ ሚኒስተሩ መጀመሩ ይታወሳል።

በዚህ በአራተኛው ዙር ከ6 ነጥብ 7 ቢሊየን በላይ የተለያዩ ችግኞች ተዘጋጅተው የነበረ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ ለደን የሚሆኑ፤ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮኑ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡና ለጥምር ደን የሚውሉ ችግኖች መሆናቸው ይታወሳል፡፡

ቀሪዎቹ 518 ሚሊዮኑ የፍራፍሬ ችግኝ፣ 35 ሚሊዮን ቀርከሃ፣ 800 ሚሊዮን ለእንስሳት መኖ ጥቅም የሚሰጡ፤ ቁጥቋጦዎች እና ለከተማ ውበት የሚሆኑ ችግኞች መሆናቸውንም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የነዚህ የችግኞች መፅደቅን አስመልክቶም የ2014 ዓ.ም ሳይጨምር በቀደሙት ሦስት ዙሮች የተተከሉ ችግኞች አማካኝ የመጽደቅ ደረጃ ከ80 በመቶ በላይ እንደሆነም የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡

ይህ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በተጀመረው ፍጥነት ከቀጠለ የደን መመናመንን በማስወገድና የተራቆተውን መሬት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ በኢትዮጵያዊያን ላይ ያንዣበበውን ድርቅና የመሬት መሸርሸርን በመመከት የትውልድ ቀጣይነት ማረጋገጥ ያስችላል፡፡

በተደጋጋሚ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚከሰተውን የድርቅ አደጋን በማስወገድ ረገድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ ሁሉም የባለድርሻ አካላት ሚናቸውን በመወጣት የዜግነት ግዴታቸውን ሊጫወቱ ይገባል እንላለን፡፡