በመተከል ዞን የሚፈጠሩ ግጭቶች በሌሎች የጥፋት ሃይሎች ሴራ እንጂ በማህበረሰቡ መካከል ምንም ዓይነት ቅራኔና ልዩነት የለም-  የአካባቢው ነዋሪዎች

ሚያዝያ 13/2013 (ዋልታ) – በመተከል ዞን የሚፈጠሩ ግጭቶች መንስኤው የሌሎች የጥፋት ሃይሎች ሴራ እንጂ በማህበረሰቡ መካከል ምንም አይነት ቅራኔና ልዩነት የለም ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።

የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት አመራሮች ከአዊ ዞን ጃዊ ወረዳ የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዳሉት በመተከልና አካባቢው በማህበረሰቡ መካከል አብሮነት፣ የባህልና ማንነት ጥብቅ ቁርኝት ዘመናትን ተሻግሮ አሁንም ቀጥሏል።

ሆኖም በመተከል ዞን የሚፈጠሩ ግጭቶች መንስኤ ሁሉ የሌሎች የጥፋት ሃይሎች ሴራ እንጂ በማህበረሰቡ መካከል ቅራኔና ልዩነት የለም ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ችግሩን በዘለቂነት ለመፍታት በዞኑ ከተቋቋመው ግብረ ሃይል በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

የፓዊ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ አሰፋ እና የጃዊ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አንዷለም አብዩ በማህበረሰቡ ዘንድ ከጥንት ጀምሮ የዘለቀ አብሮነት የጋራ ባህልና እሴት መኖሩን ገልጸው፣ በህዝቦች መካከል ልዩነት እና ግጭት እንዲፈጠር የሚሰሩ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አንዳንድ አመራሮች ጭምር መኖራቸውን አንስተዋል።

አሁን ላይ በሁለቱም ወረዳዎች ነዋሪው ጠላቶቹን በመለየት አብሮነቱን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ወንጀለኞችን በማጋለጥ በኩል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ በመተከል ዞን የፀጥታ ችግር እጃቸው ያለበት ከተጠያቂነት አያመልጡም ብለዋል።

በተለይም በችግሩ ውስጥ ተሳታፊ ሆነው የሚገኙ ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ የአመራር መዋቅር አባላትን የማጥራትና ተጠያቂ የማድረግ አሰራር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኮማንድ ፖስቱ አስተባበሪ ሌትናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ እና የኮማንድ ፖስቱ አባል ብርጋዴል ጄነራል አለማየሁ ወልዴ በበኩላቸው፣ ለዞኑ ችግሮች መነሻው ሁሉ የወያኔ ሴራ መሆኑን ጠቅሰው፣ የውጭ ሃይሎች እጅ እንዳለበትም አብራርተዋል።

ሆኖም በዞኑ ኮማንድ ፖስት ከተቋቋመ በኋላ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት መፈጠሩን በመግለጽ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውንም አንስተዋል።

በመተከል ዞን አጎራባች የጃዊ ወረዳ የሚስተዋሉ ህገ ወጥ ጦር መሳሪያ ንግድን ጨምሮ ሌሎች ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን በጋራ መከላከል እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።